የዓለም ጤና ድርጅት፡ «የታሸገ ውሃ ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር ለጊዜው ጎጂ አይደለም»

«የታሸገ ውሃ ውስጥ የሚገኘው ንጥረ-ነገር ብዙም ጎጂ አይደለም፤ ለጊዜው» Image copyright AFP

የዓለም የጤና ድርጅት፤ የምንጠጣው ውሃ ውስጥ የሚገኘው ማይክሮፕላስቲክ ብዙም ጎጂ አይደለም እያለ ነው።

ጉዳዩን በተመለከተ ድርጅቱ ባሳተመው አምድ መጠናቸው ይብዛም ይነስም ንጥረ-ነገሮቹ ይህን ያህል ጉዳት ያደርሳሉ የሚል ውጤት በጥናት አልተደረሰበትም ሲል አስታውቋል።

ቢሆንም ይላል ዓለም አቀፉ ድርጅት፤ ጠለቅ ያለ ጥናት የሚጠይቅ መሆኑ አያጠራጥርም፤ አሁን ያደርግነው ጥናት ስፋትና ጥልቀት ይጎድለዋልና።

«በፍጥነት ጥናት ማካሄድ ይጠበቅብናል» ይላል ድርጅቱ።

ማይክሮፕላስቲክ የተሰኙት ንጥረ-ነገሮች በወንዞች፣ ሐይቆች፣ በታሸጉ እና ባልታሸጉ የመጠጥ ውሃዎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

የፕላስቲክ ንጥረ-ነገር የያዘው ይህ ደቂቅ ቁስ ለጊዜው ብዙም ጉዳት እንደማያደርስ ቢረጋገጥም ወደፊት የከፋ አደጋ አያመጣም ማለት አይደለም ተብሎለታል።

ጥናቱን እንዲያካሂዱ በዓለም ጤና ድርጅት ይሁንታ የተሳጣቸው ድርጅቶች የተለያዩ ማጥኛ መንገዶች መጠቀማቸው ውል ያለው መረጃ እንዳይገኝ አድርጎታል።

«አንድ አጥኚ አንድ በአንድ ኮዳ ውስጥ 1000 ማይክሮፕላስቲክ አለ ይላል፤ ሌላኛው ደግሞ 1 ብቻ ነው የሚል ጥናት ይፋ አድርጓል። ስለዚህ የሆነ ያልተጣጣመ ነገር አለ ማለት ነው» ይላሉ የድርጅቱ ሠራተኛ የሆኑት ዶ/ር ብሩስ ጎርደን።

ባለሙያው ዓለም ላይ ሁለት ቢሊዮን ሰዎች የተበከለ ውሃ እንደሚጠጡ አልሸሸጉም። ይህም በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ሰዎችን ይቀጥፋል። «ትኩረታችን ሊሆን የሚገባው እዚህ ላይ ነው» ይላል ዶክተሩ።

ዓለማችን በፕላስቲክ መበከሏ ማይክሮፕላስቲክ የተሰኘው የምንጠጣው ውሃ ውስጥ እንዲገኝ የልብ ልብ ሆኖታል፤ የድርጅቱ መግለጫ መደምደሚያ ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ