አባታቸውን የገደሉት እህትማማቾች እንዲለቀቁ ሩስያውያን ፊርማ እያሰባሰቡ ነው

አባታቸውን የገደሉት እህትማማቾች እንዲለቀቁ ፊርማ እየተሰበሰበ ነው Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ አባታቸው በሞተ ጊዜ አንጀሊና [ግራ] ዕድሜ 18፣ ማሪያ [መሃል] ዕድሜ 17 እና ክሬስቲና [ቀኝ] ዕድሜ 19 ነበሩ

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ነበር ሶስት ሩስያውያን እህትማማቾች አባታቸውን በተኛበት በቢላ ወግተው የገደሉት።

እህትማማቾቹ ከተያዙ በኋላ ምርመራ ሲያከናውኑ የከሩመት ግለሰቦች ሴቶቹ በአባታቸው አካላዊ እና ስነ-ልቡናዊ በደል ሲደርስባቸው ነበር ብለዋል።

በግድያ ወንጀል የተከሰሱት እኒህ እህትማማቾች በሩስያ በሰፊው መነጋገሪያ ከሆኑ ሰነባብተዋል። አልፎም 3 መቶ ሺህ ገደማ ሩስያውያን እህትማማቾቹ እንዲለቀቁ የሚወተውት ፊርማ ማሰባሰብ ጀምረዋል።

ያልተዘጋው ዶሴው ምን ያሳያል?

ሐምሌ 20/2010 ዓመተ ምሕረት፤ ሚካይል ካቻቱርያን የተሰኘው የእህትማማቾቹ አባት ክሬስቲና፣ ማሪያ እና አንጀሊናን ወደ መኝታ ክፍሉ ይጠራቸውና መኖሪያ ቤታቸውን በወጉ ባለማፅዳታቸው ሊቀጣቸው ይፈልጋል።

ከዚያም የተበጠበጠ በርበሬ የሞላው መንፊያ [ፔፐር ስፕሬይ] ያነሳና የገዛ ልጆቹ ፊት ላይ ይረጫል። ከዚያም ወደ መኝታው ያመራል።

አባታቸው እንቅልፍ እንደጣለው የተረዱት ልጆቹ በተኛበት በቢላ፣ መዶሻና 'ፔፐር ስፕሬይ' ጥቃት ያደርሱበታል። ጭንቅላቱ፣ አንገቱና ደረቱ አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት አባት እስከወዲያኛው ያሸልባል።

እህትማማቾቹ ወዲያው ፖሊስ ጠርተው እጃቸውን ይሰጣሉ። ፖሊስ በወቅቱ ሰውየውን 30 ቦታ በቢላ ተወግቶ ነበር ያገኘው።

የወንጀሉን መንስዔ ለማጣራት ሥራ የጀመረው ፖሊስ ሶስቱ ወጣት ሴቶች ለዓመታት በአባታቸው ሲሰቃዩ እንደነበር ይደርስበታል። ካቻቱርያን፤ ሶስት ሴት ልጆቹን ቤት ዘግቶባቸው ሲያሰቃያቸው ወሲባዊ ጥቃት ሲያደርስባቸው እንደነበር ፖሊስ ይረዳል።

ፖሊስ፤ የወንጀሉ መንስዔ የአባት ግፍ እንደሆነ ደርሼበታለሁ የሚል የማስረጃ መዝገብ ለፍርድ ቤት አቅርቧል።

የቤት ውስጥ ጥቃት

የእህትማማቾቹ ጉዳይ ሩስያውያን ስለቤት ውስጥ ጥቃት በሰፊው እንዲወያዩ ያስገደደ ነበር። የመብት ተሟጋቾች እህትማማቾቹ ወንጀለኛ ሳይሆኑ ተበዳይ ናቸው በማለት መመገት ያዙ።

ሩስያ ለቤት ውስጥ ጥቃት ተደባዮች ሽፋን የሚሰጥ ህግ የላትም። የቤተሰብ አባል ላይ ጥቃት የሚሰነዝር ቢበዛ የገንዘብ ቅጣት ካልሆነም የሁለት ሳምንት እሥር ቢያጋጥመው ነው።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ እናት ጥቃት እየደረሰባት እንደሆነ ለፖሊስ ብታመለክትም ጆሮ የሰጣት አልነበረም።

የእህትማማቾቹ እናት በባለቤቷ ጥቃት እየደረሰባት እንደሆነ ለፖሊስ ብታመለክትም ጆሮ የሰጣት አልነበረም። ጎረቤቶቿም ቢሆኑ ግለሰቡን ስለሚፈሩት ለፖሊስ ምስክርነታቸውን መስጠት አልፈቀዱም።

እናት በባለቤቷ መኖሪያ ቤታቸውን ለቃ እንድትወጣ ተደርጋለች፤ ልጆቹም እናታቸውን እንዲያገኙ አልተፈቀደላቸውም።

ሶስቱ እህትማማቾች ላይ የስነ-ልቡና ምርመራ ያከናወኑ ባለሙያዎች ልጆቹ ድህረ-ሰቆቃ ጭንቀት [ፖስት ትራውማቲክ ስትረስ] እንዳለባቸው ማረጋገጥ ችለዋል።

ሶስቱ ሴቶች አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ባይሆኑም እርስ በርስ እንዳይነጋገሩና ጋዜጠኞች ጋር ድርሽ እንዳይሉ ተከልክለዋል።

አቃቤ ሕግ እህትማማቾቹ ወንጀሉን አቅደው እና ተልመው በመፈፀማቸው ቅጣት ይገባቸዋል፤ ምክንያቱም በቀል ነው የፈፀሙት ሲሉ ይከራከራሉ።

እህትማማቾቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 20 ዓመት እሥር ይጠብቃቸዋል። ጠበቃዎቻቸው ግን ሴቶቹ ራሳቸውን ተከላከሉ እንጂ በቀል አልፈፀሙም ሲሉ እየተከራከሩ ይገኛሉ።

በሩስያ ሕግ ራስን መከላከል በደንገተኛ ወቅት ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ለሚከሰት እና እንደሚመጣ ለሚታወቅ አደጋም የሚሰራ ነው። ይህ ደግሞ ለእህትማማቾቹ ተስፋ የሚሰጥ ነው ተብሏል። ምክንያቱም አባታቸው አሰቃቂ ስቃይ ለዓመታት ሲያደርስባቸው የሚያሳይ ማስረጃ ተገኝቷልና።

የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች እና በርካታ ሩስያዊያን የቤት ውስጥ ጥቃትን የሚመለከተው ሕግ እንዲከለስ በመወትወት ላይ ይገኛሉ።

ሩስያ ውስጥ የቤት ውስጥ ጥቃት ትኩረት የተነፈገ ጉዳይ እንደሆነ ይነገርለታል። የዘርፉ አጥኚዎች በሩስያ እሥር ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ ሴቶች 80 በመቶ ያክሉ ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ የቤት ውስጥ ጥቃት ፈፃሚዎችን የገደሉ ናቸው ይላሉ።

ታድያ እንዲህም ሆኖ ሶስቱ እህትማማቾች ከርቸሌ ይወርዱ ዘንድ የሚወትውቱ አልጠፉም። አንድ አባታዊ ቡድን 'ገዳዮች ከፍርግርግ ጀርባ' የሚል ቅስቀሳ ጀምሯል።

ነገር ግን ሴቶች ከርቸሌ ይወርዱ ዘንድ ከሚደራደሩቱ በበለጠ ይለቀቁ ዘንድ የሚወተውቱ ሩስያውያን ቁጥር ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ተቃውሞ ሰልፎች፣ የግጥም ምሽቶች እና ቲያትሮች ሴቶች እንዲለቀቁና የቤት ውስጥ ጥቃት ትኩረት እንዲያገኝ መዘከር ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ