ከሶማሌላንድና የመን የመጣው አንበጣ በአምስት ክልሎች ተከስቷል

አንበጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወደ ኢትዮጵያ የተንቀሳቀሰው አንበጣ የመንና ሶማሌላንድ እድገቱን የጨረሰ ነው። ይሁንና ይህ አንበጣ በራሱ ጉዳት የማያደርስ ሲሆን ነገር ግን እንቁላል ጥሎ በእንቁላሉ አማካኝነት ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት በግብርና ሚኒስቴር የዕጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሰላቶ ገልጸዋል።

"እድገቱን የጨረሰ አንበጣ ብዙም አይመገብም" የሚሉት ዳይሬክተሩ እድገቱን ያልጨረሰው ግን አዝዕርትን ያለ ዕረፍት በመመገብ ጉዳት ስለሚያደርስ እንቁላሉ እንዳይፈጠር ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አቶ ዘብዲዎስ ይህንን ለመከላከል ቅድም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀው በአሁኑ ወቅት በሶማሌ፣ በኦሮሚያ ምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ፣ በአፋር፣ ድሬዳዋና ሰሜን ምስራቅ አማራ አንበጣው የደረሰባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በእነዚህ አንበጣው በተንቀሳቀሰባቸው የተወሰኑት አካባቢዎችም ቅድመ መከላከል ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል። ቦታውን በትክክል መለየትና የሚረጩት ኬሚካሎች ጉዳት ስለሚያደርሱ ነዋሪው ከብቶቹንና ልጆቹን እንዲጠብቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። ርጭቱን ለሚያከናውኑ ሰዎችም በተመሳሳይ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ አንበጣው እድገቱን የጨረሰ በመሆኑ በሰብል ላይ ጉዳት የማድረስ ዕድል እንደሌለው ገልጸው ነገር ግን አሁንም ከየመንና ሶማሌላንድ ሊመጣ የሚችል የአንበጣ መንጋ ሊኖር እንደሚችል አለም አቀፍ ትንበያ መኖሩን አስረድተዋል።

ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የመርጫ መሳሪያዎችን ወደ አካባቢዎቹ የማንቀሳቀሱ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ዳእሬክተሩ እንደሚሉት አንበጣው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው እርጥበትና አረንጓዴ ዕጽዋትን ለማግኘት የነፋስን አቅጣጫ በመከተል ነው። የአንበጣ እንቁላል ምቹ የአየር ሁኔታ ከገጠመው እስከ አስር ቀን ይፈለፈላል።

እርጥበት ካለ እስከ 17 ቀን የሚቆይ ሲሆን አልፎ አልፎ እስከ 60 ቀን የሚቆይበትም ጊዜ አለ። በመሆኑም እስከ 50 ቀን ድረስ ክንፍ ስለማያወጣ በዚህ ጊዜ ውስጥ መከላከል እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ዳይሬክተሩ ይህ ካልሆነ ግን በርሮ ወደ ሌላ አካባቢ በመዛመት በርካታ አካባቢዎችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ብለዋል።

እንደዚህ አይነት ሁኔታዎችን ህብረተሰቡ ሲያይም ከ24 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለየአካባቢው የግብርና ሞያተኛ ማስረዳት መቻል አለበት ብለዋል።።

እስከዛሬ የተደረጉ ጥናቶችን መሰረት በማድረግም ነገ በ17/12/11 አፋር አንድ ቦታ ላይ ለርጭት የበቃ የአንበጣ እንቁላል መኖሩ ስለተረጋገጠ ርጭት እንደሚጀመር አቶ ዘብዴወስ ተናግረዋል።

በአምስት ክልሎች አንበጣው የደረሰ ቢሆንም እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን ምንም ስጋት የሚያደርስ ነገር አለመኖሩንና ለርጭትም ከተባለው ቦታ ውጭ ልየታ የተደረገለት ቦታ አለመኖሩንም ገልጸዋል።

ይሁንና ይህ አንበጣ በራሱ ጉዳት የማያደርስ ሲሆን ነገር ግን እንቁላል ጥሎ በእንቁላሉ አማካኝነት ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት በግብርና ሚኒስቴር የዕጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሰላቶ ገልጸዋል።