አከራካሪው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ

ጥምህርት ሚኒስቴር Image copyright Ministry of Education

ለሁለት ዓመታት ጥናት ሲደረግበት የቆየው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ነሐሴ 14፣ 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ይፋ ተደርጓል። የቀረበውን ጥናት መሠረት በማድረግም ውይይት ሲካሄድበት መቆየቱ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ቀናት የአገሪቱን የትምህርት ሥርዓት በሚመለከት እየተላለፉ ያሉ ምክረ ሃሳቦች በርካቶችን እያነጋገሩ ይገኛሉ።

የዛሬ ዓመት የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ረቂቅ ይፋ በሆነበት ወቅት በተለይ እንደ ቋንቋ ያሉ ጉዳዮች አሁንም ድረስ እያከራከሩ ነው።

ፍኖተ ካርታው ወደ ቀድሞ የትምህርት ፖሊሲ ሊመልሰን ይሆን ?

ብሔራዊ ፈተናዎች ምን ያህል ከስርቆትና ከስህተት የተጠበቁ ናቸው?

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ትናንት ባወጣው መግለጫ በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የአማርኛ ቋንቋ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ መደረጉና የ8ኛ ክፍል ፈተና ሃገራዊ መሆኑን እንደማይቀበለው ማስታወቁን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።

የ8ኛ ክፍል ፈተናን ሃገራዊ ማድረግም የክልሉን ሥልጣን የሚጋፋ ነው ሲል ተችቶታል።

መግለጫው አክሎም "ፍኖተ ካርታው በምሁራን የተጠና ነው በሚል ለተነሱ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ሳይሰጥ ወደ ተግባር እየተለወጠ ነው" ሲል ይኮንናል።

ፍኖተ ካርታው የተለያዩ የትምህርት ፖሊሲውን የሚነካ ሆኖ ሳለ የሃገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮችና የፖሊሲ ለውጥ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ውሳኔ ሳያሳልፉና አስተያየት ሳይሰጡበት ወደተግባር መግባታቸው ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጫው ተመልክቷል።

ከዚህ ባሻገርም ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ደረጃውን 6-2-4 ብሎ መግለጫ ከማውጣቱ በፊት በቂ ማብራሪያ መሰጠት ነበረበት ይላል።

"ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ትምህርት የሚሰጠው በአፍ መፍቻ ቋንቋ ሆኖ ሳለ የ8ኛ ክፍልን ፈተና ሃገራዊ ማድረግ ምን አመጣው?" ሲልም ይጠይቃል።

"የትግርኛ ቋንቋ ከአማርኛ ቋንቋ ጋር ይወራረሳል" የሚለው መግለጫው፤ የሰባት ዓመት ሕፃን እነዚህን ቋንቋዎች በአንድ ላይ መስጠት ማደናገር ነው ብሏል።

በመሆኑም የአማርኛ ቋንቋን ከአንደኛ ክፍል መጀመርና የ8ኛ ክፍልን ፈተና ሃገራዊ ማድረግን የክልሉ ትምህርት ቢሮ እንደማይቀበለው አስታውቋል።

ትምህርት ዕድሜን እንደሚያስረዝም በጥናት ተረጋገጠ

የፍኖተ ካርታው አካል የሆኑት ውሳኔዎች ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቶላ በርሶም በበኩላቸው ሕፃናት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውንና እንግሊዝኛ እንደሚማሩ ገልጸው፤ ፍኖተ ካርታው በተማሪዎች ቋንቋ ላይ ተፅዕኖ ማድረግ የለበትም" ሲሉ ይቃወማሉ።

"የማስተማሪያ ቋንቋን በተመለከተ የተለወጠ ነገር የለም። ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉትን የትምህርት ዓይነቶች የሚማሩት በአፋን ኦሮሞ ነው" ይላሉ።

አማርኛን በተመለከተ፤ ሕፃናት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ሦስት ቋንቋዎችን መማር ስለማይችሉ አማርኛን መማር ያለባቸው ከፍ እያሉ ሲሄዱ መሆኑንም ይገልጻሉ።

ከስድስተኛ ክፍል የክልል ፈተና በተጨማሪ ክልሎች የስምንተኛ ክፍል ፈተናን እንደሚሰጡም ያክላሉ።

ባለፈው ዓመት የፍኖተ ካርታው ረቂቅ ቀርቦለት የነበረው የምሁራን ቡድን አባል የነበሩት የሥርዓተ ትምህርት ባለሙያው ዶ/ር ፍርዲሳ ጀቤሳ "መዋቅር አትንኩ፣ የነበረው ሥርዓተ ትምህርት ችግር አይደለም፤ የትምህርት ጥራቱን እንዲወድቅ ያደረገው የግብዓት፣ የትግበራ፣ የብቃትና የአመራር ችግር ነው" የሚል ሃሳብ ተነስቶ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ዶ/ር ፍርዲሳ እንደሚሉት በወቅቱም ሌሎች አከራካሪ ጉዳዮች ተነስተው ነበር፤ በመሆኑም መግባባት ላይ ሳይደርሱ ውይይቱን እንዳጠናቀቁ ይናገራሉ።

ይሄው ሐሳብ ዛሬም እንደ አዲስ መምጣቱን ያስረዳሉ።

"የአማርኛ ቋንቋ ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲሰጥ ሚንስትሩ መግለጫ ሲሰጡ ሰምቻለሁ፤ በጽሑፍ ላይ የተቀመጠው ደግሞ ከአንደኛ ክፍል ይጀምራል ይላል" ሲሉ በጽሑፍ ላይ ያለውና በመግለጫ የተሰጠው ሐሳብ ተጣርሷል ይላሉ- ዶ/ር ፍርዲሳ።

የተለያዩ ሳይንሳዊ የትምህርት ጥናቶችን የሚያጣቅሱት ዶ/ር ፍርዲሳ፤ በተጠቀሰው የክፍል ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎች ከሁለት ቋንቋ በላይ አዕምሯቸው መሸከም ስለማይችል ግርታ ሊፈጠርባቸው ይችላል በማለት ይሞግታሉ። በዚህም ላይ መግባባት እንዳልነበር ያስታውሳሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ለ10ኛ ክፍል የሚሰጠው ብሔራዊ ፈተና እንዲቀር መደረጉም የራሱ ችግር እንዳለው ዶ/ር ፍርዲሳ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም "የክልል ቋንቋዎች ያለማጠቃለያ ፈተና ሊቆሙ አይችሉም፤ በመሆኑም የክልል ቋንቋዎች እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ይቀጥሉ ይባላል፤ ይህም አልተወሰነም፤ ግልፅም አይደለም" ይላሉ።

በክልል ደረጃ ሲሰጥ የነበረው የስምንተኛ ክፍል ፈተናን ብሔራዊ ፈተና ማድረግም ሕጋዊ አይደለም ሲሉ ተችተውታል።

በዋግ ኸምራ አስተዳደር 7 የዳስ ት/ቤቶች አሉ

የስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ፈተና ውጤትን የሚያጣራ ኮሚቴ ተዋቀረ

"ሕገ መንግሥቱ 'ክልል አንደኛ ደረጃን ይመራል' ይላል፤ ይሁን እንጂ የተነሳው ሐሳብ የክልሉን ሥልጣን እስከ ስድስተኛ ያወርደዋል፤ የክልል ቋንቋ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ይቀጥላል ይላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እኛ የምንሰጣችሁን ፈተናው ተርጉማችሁ ነው የምትፈትኑት ይላል" ሲሉ እርስ በርሱ የሚጋጭ እና ወጥነት የሌለው ሐሳብ እንደሆነ በምሳሌ ያስረዳሉ።

ዶ/ር ፍርዲሳ እንደሚሉት ክልሎች የአንደኛ ደረጃ ያለውን ትምህርት ያቅዳሉ፣ ይዘት ይመርጣሉ፣ ያደራጃሉ፣ ይተገብራሉ፣ ይፈትናሉ፣ ሪፖርት ያደርጋል እንጂ፤ እዚያ ውስጥ መግባት አልነበረባቸውም።

የተነሱትን ሐሳቦች አንስተን ያነጋገርናቸው የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ገረመው ሁሉቃ፤ ከቋንቋ ጋር በተያያዘ የክልልና የፌደራል መንግሥት ሥልጣንን በሚመለከት አሁንም መጣራት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ በማንሳት ፍኖተ ካርታው ገና እየተሠራበት ያለ ሰነድ እንደሆነ ተናግረዋል።

"የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጣል ይላል፤ በሌላም በኩል የ8ኛ ክፍል ፈተና ብሔራዊ ፈተና ሆኖ ተተርጉሞ ለክልሎች ይሰጣሉ ይላል፤ በመሆኑም እነዚህ ጉዳዮች የክልል መንግሥታትን ሥልጣን ይነካሉ" በማለት ሕገ መንግሥቱ ከ1- 8ኛ ክፍል ያለውን ትምህርት መስጫ ቋንቋ የሚወስነው የክልሉ መንግሥት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም መታየት ያለበት ጉዳይ ስለሆነ ትምህርት ሚኒስቴር እየሠራበት ይገኛል ብለዋል።

ታዲያ ውሳኔ ያላገኘ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠት ለምን አስፈለገ?

ሚንስትር ዲኤታው የትናንት በስቲያ መግለጫ በ2012 ዓ.ም ፍኖተ ካርታው ተግባራዊ እንደሚሆን ለማስተዋወቅ እንጂ አከራካሪ ተብለው የተያዙና ውሳኔ ያልተሰጠባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ያነሳሉ።

"ፍኖተ ካርታው ገና እየተጠና ያለ ጉዳይ ነው፤ የመጨረሻው ውሳኔ አይደለም" ብለዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት በጅግጅጋ በሚደረገው የትምህርት ኮንፈረንስ ፍኖተ ካርታው ውይይት ይደረግበታል፤ በውይይቱ ላይ ክልሎችም ስለሚሳተፉ እነዚህ ጉዳዮች መፍትሔ ያገኛሉ ሲሉ ሚንስትር ዲኤታው ዶ/ር ገረመው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ትምህርት ሚኒስቴርም በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ በትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ምክረ ሃሳብ መሠረት ውሳኔ የሚሹ 36 ጉዳዮች መለየታቸውን አስታውቋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ