"አትግደሉን!"፡ የቱርክ ሴቶች

ኢስታንቡል ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል Image copyright Getty Images

ነሐሴ 8 ቀን ቱርክ ውስጥ ኤሚን ቡሊት የተባለች ሴት በቀድሞ ባለቤቷ መገደሏ በመላው አገሪቱ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።

የ38 ዓመቷ ኤሚን ከልጇ ጋር ካፍቴሪያ ውስጥ ሳለች ነበር የቀድሞ ባለቤቷ በስለት ወግቶ የገደላት።

ሕይወቷ ከማለፉ በፊት አንገቷን ይዛ ስትጮህ፤ የ10 ዓመት ልጇ እንዳትሞት ስትማጸናት የሚያሳይ አሳዛኝ ቪድዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቷል። ቪድዮው ላይ ኤሚን ለልጇ "መሞት አልፈልግም" ትላትም ነበር።

ኤሚን ልጇን ይዛ ወደ ካፍቴሪያው የሄደችው ልጇን ከቀድሞ ባለቤቷ ጋር ለማስተዋወቅ ነበር።

'ዊ ዊል ስቶፕ ፌሚሳይድ' የተባለው የሴቶች መብት ተሟጋች ቡድን እንደሚለው፤ ቱርክ ውስጥ በዚህ ዓመት 245 ሴቶች ተገድለዋል። ከሴቶቹ 32ቱ የተገደሉት ባለፈው ወር ነበር።

"በወንድሜ ለአምስት ዓመታት ተደፍሬአለሁ"

የኤሚን የቀድሞ ባለቤት ፍርድ ቤት ቀርቦ፤ "ልጃችን ከማን ጋር መኖር እንዳለባት እያወራን ሳለ ስለሰደበችኝ፤ ይዤው በሄድኩት ቢላ ወግቻታለሁ" ሲል ቃሉን ሰጥቷል።

ጥቃቱን ካደረሰ በኋላ ከአካባቢው የተሰወረ ሲሆን፤ በስተመጨሻ ሆስፒታል ውስጥ ሳለ ሞቷል።

ኤሚን ሕይወቷ ከማለፉ በፊት "መሞት አልፈልግም" ስትል የተናገረችውን ቃል በመጠቀም ቱርክ ውስጥ የሴቶች መብት እንዲከበር የሚያሳስብ ማኅበራዊ ሚድያ ንቅናቄ እየተካሄደ ይገኛል።

"ሌሎች ሴቶች ላይ የአሲድ ጥቃት ሳይ ይረብሸኛል፤ ህመሜን ያስታውሰኛል" ካሚላት መህዲ

የቱርክ መዲና ኢስታንቡል ከንቲባ፤ "ኤሚን ቡሉትን ያጣነው ወንዶች በሚሰነዝሩት ጥቃት ሳቢያ ነው፤ የሴቶችና የህጻናትን መብት በማስከበር ከጎናቸው ነበርን፤ ለወደፊትም እንገፋበታለን" ብለው በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።

የቱርክ እግር ኳስ ቡድን (በስኪታስ) "ይህን የጭካኔ ተግባር በዝምታ አናልፍም። የሴቶች ግድያ እንዲቆም፤ ጥቃት አድራሾቹ ከባድ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እንፈልጋለን" የሚል መልዕክት አስተላልፏል።

'ዊ ዊል ስቶፕ ፌሚሳይድ' የተባለው የሴቶች መብት ተሟጋች ቡድን ተወካይ ጉሉሱም ካቭ ለቢቢሲ "የመጨረሻ ቃሏ፤ 'መሞት አልፈልግም'፣ ጥያቄዋም አትግደለኝ መሆኑ፤ ቱርክ ውስጥ ያለነው ሴቶች ትንሹ ጥያቄያችን አለመሞት መሆኑን ያመላክታል፤ መሞት አንፈልግም" ብላለች።

የኤሚን የ10 ዓመት ልጅ "እናቴ አትሙቺብኝ" ማለቷን በማስታወስም፤ "ማንም ሰው በቀላሉ የሚያልፈው ነገር አይመስለኝም" ስትል ተናግራለች።

ዩክሬናዊቷ የምክር ቤት አባል ከደረሰባት የአሲድ ጥቃት በኋላ ሕይወቷ አለፈ

ጉሉሱም እንደምትናገረው፤ ቱርካዊያን ሴቶች ሴት በመሆናቸው ብቻ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ መገንዘብ ጀምረዋል። ብዙ ቱርካውያን የንቅናቄው አካል እየሆኑም መጥተዋል።

ሄክተፒ ዩኒዘርስቲ በሠራው ጥናት መሰረት፤ በትዳር ውስጥ ካሉ ወይም ከትዳር ከወጡ ሴቶች 36 በመቶ የሚሆኑት በሕይወታቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል።