ደቡብ አፍሪቃ የታንዛኒያ አውሮፕላንን ጆሃንስበርግ ውስጥ በቁጥጥር ሥር አዋለች

የታንዛኒያ አውሮፕላን Image copyright IKULU
አጭር የምስል መግለጫ የታንዛኒያ አየር መንገድ 2007 ዓ.ም. በአዲስ መልክ ሥራ ሲጀምር አንድ አውሮፕላን ብቻ ነበረው

የደቡብ አፍሪቃ ባለሥልጣናት የታንዛኒያ ብሔራዊ አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን በቁጥር ሥር ማዋላቸውን አስታውቀዋል።

ኤዬር ባስ 220-300 የተሰኘው የታንዛኒያ አውሮፕላን ዓርብ ዕለት ከጆሃንስበርግ ወደ ዳሬሳላም ሊበር ሲሰናዳ ነበር።

አውሮፕላኑ በቁጥጥር ሥር በዋለ ጊዜ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በውል የታወቀ ነገር አልነበረም። የደቡብ አፍሪቃ ባለሥልጣናትም 'በዚህ ምክንያት ነው' የሚል አስተያየት መስጠት አልሻቱም።

አንድ ጡረታ የወጡ አርሶ አደር ግን አውሮፕላኑ ሊታገት የቻለው የታንዛኒያ መንግሥት ሊከፍላቸው የሚገባውን 33 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ባለመቻሉ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠበቃ ሮጀር ዌክፊልድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ገንዘቡ ለደቡብ አፍሪቃዊው አርሶ አደር በካሳ መልክ እንዲሰጥ ያስፈለገው የታንዛኒያ መንግሥት የገበሬውን መሬት በሕገ-ወጥ መንገድ በመያዙ ነው።

የታንዛኒያ መንግሥት አፈ-ቀላጤ የሆኑ አንድ ግለሰብ ጉዳዩን የሚመረምሩ የሕግ ሰዎች ወደ ደቡብ አፍሪቃ እንዳቀኑ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አርብ ዕለት ከደቡብ ወደ ምስራቅ አፍሪቃ እንዲበር ቀጠሮ የተያዘለት አውሮፕላን ተጓዦች በሌሎች አውሮፕላኖች ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉን የታንዛኒያ አየር መንገድ ኃላፊ አሳውቀዋል።

የታንዛኒያ አየር መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪቃ መብረር ከጀመረ በቅጡ ሁለት ወር አልሞሉትም። አየር መንገዱ ከፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ ሥልጣን መያዝ በኋላ ሥራ ሲጀምር አንድ አውሮፕላን ብቻ ነበረው።

የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በተመሳሳይ የታንዛኒያ አውሮፕላን ካናዳ ውስጥ መያዟ አይዘነጋም። በወቅቱ አንድ የካናዳ የግንባታ ኩባንያ ካሳ አልተከፈለኝም ሲል አውሮፕላኗ እንድትታገት ያስደረገው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ