ዘረኝነት ሽሽት ጋና የከተመው አሜሪካዊ

አቶ ካምቦን ከባለቤቱ እና ልጆቹ ጋር Image copyright OBADELE KAMBON

አፍሪቃ አሜሪካዊው ኦባዴሌ ካምቦን ጋና የገባው 2000 ዓ.ም. ላይ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ዞር ብሎ ወደ ትውልድ ሃገሩ አሜሪካ ማየት አላስፈለገውም።

ለዚህ ደግሞ ምክንያት የሆነኝ በቆዳ ቀለሜ ምክንያት ለእሥር መብቃቴ ነው ይላል ካምቦን።

አንድ ወቅት ከፍተኛ ባሪያዎች የተሸጡባትና የተለወጡባት ጋና አሁን ለካምቦን የነፃነት ምድሩ ነች፤ የተደላደለ ሕይወት እየመራም ይገኛል። ወደ ኋላ ማየት አይሻም፤ የአሜሪካ መንገዶች ላይ በፖሊስ መገላመጥን ጠልቷል፤ ልጆቹ በቀለማቸው ምክንያት ብቻ የፖሊስ ቀለሃ ሲሳይ እንዲሆኑም አይፈልግም።

ልጆቹን አሜሪካ ውስጥ ስለማሳደግ ሲያስብ ታሚር ራይስ ድቅን ይልበታል። ክሊቭላንድ በተሰኘችው ከተማ መጫወቻ ሽጉጥ ይዞ እንደወጣ የቀረው ራይስ፤ 'ትክክለኛ ሽጉጥ የያዘ መስሎን ነው ተኩስን የገደልነው' ባሉ ፖሊሶች በ14 ዓመቱ ምድርን የተሰናበተው ራይስ።

ገምዳላ ፍርድ

የ14 ዓመቱ ታዳጊ ሞት ተቃውሞን ቀስቅሶ ነበር፤ 'ብላክ ላይቭስ ማተር' የተሰኘው እንቅስቃሴም ጉዳዩን እጅጉን አጡዞት ፍትህ ፍለጋ ብዙ ጮኋል።

ካምቦን 'ሕይወቴን ቀያሪ' ያላት አጋጣሚ የዛሬ 12 ዓመት ገደማ ተከሰተች። በሚኖርባት ቺካጎ ያሉ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር አውለው ፍርድ ቤት ገተሩት። 'መኪናው ውስጥ የጦር መሣሪያ ይዞ አግኝተነዋል፤ ጥፋት ሊፈፅምም ነበር' ሲሉ ለዳኛው አቤት አሉ።

እርግጥ ነው ካምቦን የጦር መሣሪያ ይዞ ነበር። ጥይት ያልጎረሰ ፍቃድ ያለው ሽጉጥ። ፍርድ ቤት ቆሞ ክሱን ሲሰማ ግን ደነገጠ። «የዛኔ ነው ለራሴ አንድ ቃል የገባሁት። ሁለተኛ አእምሯቸው የሞሰነ ነጭ አሜሪካዊ ፖሊሶች ያሉበት ፍርድ ቤት መቆም አልፈልግም ያልኩት።»

ቺካጎ ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ትምህርት ቤቶች በማስተማር ሕይወቱን ይገፋ የነበረው ካምቦን በነፃ ተለቀቀ። አእምሮው ግን እረፍት አላገኘችም። ለአንድ ዓመት ያክል ያጠራቀማትን 30 ሺህ ዶላር [863 ሺህ ብር] ይዞ ጉዞ ወደ አክራ፤ ጋና።

ባለቤቱ ካላ አብራው ወደ ጋና መጣች። ጥንዶቹ አሁን የሶስት ልጆች ወላጅ ናቸው። አማ፣ ኩዋኩ እና አኮስዋ።

አፍሪቃዊ መንፈስ

ካምቦን፤ አሁን የዶክትሬት ድግሪውን በቋንቋ ጥናት ከጋና ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል። እዚያው ዩኒቨርሲቲ 'አፍሪቃን ስተዲስ' በተሰኘው ትምህርት ክፍል ውስጥ በአስተማሪነት ያገለግላል።

ወደ ጋና ከተመሰለ ወዲህ አንድም ቀን በቆዳው ቀለም ምክንያት የዘረኝነት ጥቃት ደርሶበት አያውቅም። «የሚገርም ነው! ነጭ አሜሪካውያን ዩኤስ ውስጥ እንዲህ ነው የሚኖሩት ማለት ነው። 'የሆነ ነገር ያጋጥመኝ ይሆን?' ሳይሉ በነፃነት መንቀሳቀስ።»

ነገር ግን ጋና ውስጥ ሕይወት ፍፁም ናት ማለት አይደለም ይላል ካምቦን።

«ስለ አፍሪቃዊ መንፈስ ስታወራ ሰዎች ራስታ ነው ብለው ያስባሉ፤ ነጮች ያስተቀዋወቁን እምነት ነው አሁንም ጎልቶ የሚታየው። አፍሪቃውያን የራሳቸው ኃይማኖት ሊኖራቸው እንደሚችል ብዙም አይንፀባረቅም።»

በሚኖርበት አፓርታማ ያሉ ጋናውያን ሕፃናት አንድም ሃገር አቀፍ ወይንም አፍሪቃዊ ቋንቋ መናገር አለመቻላቸው እንዳስደነቀው አይሸሽግም።

አቶ ካምቦን ወደ ጋና ከመጣ ወዲህ ሁለት የምስራቅ አፍሪቃ ቋንቋዎችን ለምዶ ቅኔ መዝረፍ ጀምሯል። አካን እና ዮሩባ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ ይናገራል። ዎሎፍ የተሰኘውን ቋንቋም ተክኖበታል። ስዋሂሊ እና ኪኮንጎ ቋንቋዎችንም በበቂ ሁኔታ ይረዳቸዋል።

Image copyright EMMANUEL DZIVENU/JOYNEWS

የጋንዲ ሃውልት ይረስ

ካምቦን፤ የቅኝ ግዛት አዳፋ አሻራዎች እንዲፋቁ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል። ባለፈው ዓመት የሕንድ ነፃነት መሪ የሚባለው ማሕትማ ጋንዲ ሃውልት ከጋና ዩኒቨርሲቲ እንዲወገድ ቅስቀሳ አካሂዷል፤ ተሳክቶለታልም።

ደቡብ አፍሪቃዊያንን ዘረኝነት በተጠናወተው ስድብ ያንቋሸሸና ሕንዶች ከጥቁር ሕዝቦች የተሻሉ ናቸው ሲል የተናገሩ ነው ይሉታል ጋንዲ።

«ለገዛ ጀግኖቻችን ክብር የሌለን እና ሌሎችን ከፍ ከፍ የምናደርግ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው።»

ወደ ሃገር ቤት

የጋናው ፕሬዝደንት ናና አኩፎ አዶ የያዝነው የጎርጎሮስውያን ዓመት 2019 'የመመለሻ ዓመት' ነው ሲሉ ይፋ አድርገዋል።

በባሪያ ንግድ ምክንያት እናት ሃገራቸውን ጥለው የሄዱ አፍሪቃውያን ሲመለሱ እጅ ዘርግቶ መቀበል ግዴታችን ነው ይላሉ ፕሬዚዳንቱ። የጋና ቱሪዝም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ ጋናን ለማስተዋወቅ ደፋ ቀና እያለ ነው።

ካምቦን እንቅስቃሴው የሚደገፍ ነው ይላል። ግን አትርሱ ሲል ያስጠነቅቃል. . . ውጭ ሃገራት የሚኖሩ አፍሪቃውያን 'ኤቲኤም' አይደሉም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ