ልጃቸውን ወተትና እንቁላል የከለከሏት አውስትራሊያውያኖቹ ለከፍተኛ አደጋ በማጋለጥ ተከሰሱ

ህፃኗ Image copyright NSW District Court/ABC

አውስትራሊያውያን ወላጆች ህፃን ልጃቸውን የፆም ምግብ ብቻ እንደትመገብ በማድረግ በከፍተኛ ምግብ እጥረት በመሰቃየቷ ምክንያት ተከሰው ከሰሞኑ ተፈርዶባቸዋል።

በሰላሳዎቹ እድሜ የሚገኙት ባልና ሚስቶች ልጃቸውን ለምግብ እጥረት በማጋለጥ የአስራ ስምንት ወራት እስር ተፈርዶባቸው የነበረ ሲሆን ወደ ማህበረሰብ ግልጋሎትም ተቀይሮላቸዋል

የሶስት አመቷ ልጅ ከፍተኛ መቀንጨር ያሳየች ሲሆን የሶስት ወር ጨቅላ ትመስላለች ተብሏል።

ጋቦን፡ በሆስፒታል ክፍያ መያዣነት የቆየችው ህፃን ነፃ ሆነች

በህንድ ህፃኗን ደፍረው የገደሉ በእድሜ ልክ እስራት ተቀጡ

ህፃኗን አጃ፣ ድንችና ሩዝ ሲመግቧት የነበረ ሲሆን ስጋም ይሁን ወተትና እንቁላል የመሳሰሉ የእንስሳት ተዋፅኦ ምግቦችን እንዳትመገብ አድርገዋታል።

ጨቅላዋ እስካሁን ባለው እድገቷም ጥርስ ያላበቀለች ሲሆን ባለፈው አመትም ወደ መንከባከቢያ ቦታ ተወስዳለች።

ሲድኒ የሚገኘው ፍርድ ቤት ውሳኔውን ያስተላለፈው ሐሙስ እለት ሲሆን ዳኛዋ ሳራህ ሀጌት ወላጆቿ ህፃኗን ለምግብ እጥረት በማጋለጣቸው ወንጅለዋቸዋል።

ህፃኗ የከፋ ክሳት የሚታይባት ሲሆን እድገቷንም አስተጓጉለዋል ተብሏል።

በመጋቢት ወር ላይ ጨቅላዋ በከፍተኛ ሁኔታ ስትንቀጠቀጥ እናቷ የአደጋ ሰራተኞችን በመጥራቷ ነው ሁኔታዋ ሊታወቅ የቻለው።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ህፃኗን ባገኟትም ወቅት ከንፈሯ ሰማያዊ ቀለም፣ እጇና እግሯ ቀዝቃዛ እንዲሁም የሰውነቷ የስኳር መጠን በጣም ዝቅተኛና ጡንቻዋም ዝሎ እንደነበር የአውስትራሊያው አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

በፌስታል ተጥላ ለተገኘችው ልጅ የጉዲፈቻ ጥያቄዎች ጎረፉላት

ህፃኗ ለአሳዳጊዎች የተሰጠች ሲሆን፤ እድገቷ በጣም የዘገዬ እንደሆነ አዲሶቹ ወላጆቿ አስታውቀዋል።

"መቀመጥም ሆነ መናገር አትችልም፤ የሶስት አመት ልጅ ብትሆንም በራሷ መመገብ አትችልም። ከአሻንጉሊት ጋር መጫወት እንዲሁም በራሷ መዳህም ሆነ መንከባለል አትችልም" ብለዋል።

ዳኛዋ ሀጌት እንደተናገሩት ወላጆቿ የህፃኗ ሁኔታ ከአመጋገቧ ጋር የተያያዘ ነው የሚለውን መጀመሪያ ላይ መቀበል አዳግቷቸው እንደነበር ገልፀው፤ ከዚህ ቀደም ሁለት ልጆችን ያለምንም አደጋ ያሳደጉ ወላጆች ሲሆኑ የተማሩ ናቸውም ተብሏል።

በመኪናዋ ኮፈን ለሁለት አመት ያህል ልጇን የደበቀችው እናት ተከሰሰች

ዳኛዋ አክለው እንደገለፁት እናቲቱ በከፍተኛ የድብርት ሁኔታ እየተሰቃች የነበረ ሲሆን የፆም ምግብ (ቬጋን) ላይ የሙጥኝ ብላ ነበር ተብሏል።

አባትየውም የልጁን ሁኔታ እያየ ችላ ማለቱንም ዳኛዋ ተችተዋል።

"ልጆች የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው ማደጋቸውን መከታተል የቤተሰቦች ሃላፊነት ነው" ብለዋል ዳኛዋ

በባለፈው አመት ፍርድ ቤት የቀረቡት ወላጆቿ ልጃቸውን የምግብ እጥረትና ለከፉ አደጋዎች ማጋለጣቸውን በማመን ጥፋተኛ ነን ብለዋል።

ሁለቱም የአስራስምንት ወራት እስር ተፈርዶባቸው የነበረ ቢሆንም ያ ተቀይሮ እንዲስተካከሉ የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ ታዘዋል።