እስራኤል 'የኢራንን ሰው አልባ አውሮፕላን ጣቢያ ከጥቅም ውጭ አድርግያለሁ' እያለች ነው

እስራኤል 'የኢራንን ድሮን ጣቢያ ከጥቅም ውጭ አድርግያለሁ' እያለች ነው Image copyright AFP

እስራኤል፤ ሶሪያ ውስጥ የሚገኝ አንድ የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጣቢያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት መፈፀሟን አስታውቃለች።

በሶሪያ ስላላት ተሳትፎ ብዙም መረጃ የማትሰጠው እስራኤል 'ሰው አልባ አውሮፕላን ጣቢያው የቴል-አቪቭ መንግሥት ላይ ጥቃት ለመፈፀም እየተዘጋጀ ነበር' ብላለች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የወታደራዊ ኃይላቸውን እርምጃ 'አብይ እና ስኬታማ ኦፕሬሽን' ሲሉ ገልፀውታል።

የሶሪያ የእርስ በርስ ግጭት ከተቀሰቀሰበት 2011 [እ.አ.አ.] ጀምሮ እስራኤል በርካታ ወታደራዊ እርምጃዎችን ስትወስድ ነበር። ዋነኛ ዓላማዋም ኢራን በሶሪያ ያላትን ቦታ መጋፋት ነው።

የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ቃል-አቀባይ የሆኑ ሰው ቅዳሜ ዕለት የተካሄደው ኦፕሬሽን፤ ደቡብ ምስራቅ ደማስቆ የከተሙት በኢራን የሚደገፉት ኩርድስ የተሰኙ ታጣቂዎችን ዒላማ ያደረገ ነው።

'ሰንዓ ኒውስ ኤጀንሲ' የተባለ አንድ የሶሪያ ዜና ወኪል የእስራኤል ፀረ-አየር ኃይል አባላት የጠላት ይዞታን ዒላማ አድርገዋል ሲል ዘግቧል። ነገር ግን የእስራኤል ሚሳዔሎች ዒላማቻውን ከመምታቸው በፊት ከጥቅም ውጭ ሆነዋል ሲል ነው ወኪሉ ያተተው።

ጠ/ሚ ኔታኒያሁ ግን በትዊተር ገፃቸው ድል ማስመዝገባቸውን የሚናገር መልዕክት ነው ያስተላለፉት፤ 'ኢራን ሁሉም ቦታ መከላከያ የላትም። የኛ ኃይሎች የኢራንን ወረራ ለመመከት ሁሉም ቦታ ይገኛሉ። አንድ ኃይል ሊገልህ ከተነሳ ቀድመህ ግድለው' ሲሉ።

ሌላኛው በኢራን የሚደገፈው 'ሄዝቦላህ' ሁለት የሌባኖስ ዜጎች በእስራኤል ጥቃት መሞታቸውን ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ የእስራኤል ንብረት ናቸው ያላቸውን ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላኖች መትቶ መጣሉንም አስታውቋል።

ምንም እንኳ ስለጥቃቱ ጥርት ያለ መረጃ ሊገኝ ባይቻልም እስራኤል ትቃት ፈፅሜያለሁ ከማለት አልቦዘነችም፤ ኢራን በጉዳዩ ላይ እስካሁን መግለጫ አልሰጠችም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ