የተጠለፈው ልዑል አለማየሁ አፅምና የተዘረፉ ቅርሶች በውሰት እንግሊዝ እመልሳለሁ አለች

ልዑል አለማየሁ Image copyright Julia Margaret Cameron

በእንግሊዝ መንግሥትና በኢትዮጵያው ንጉስ አፄ ቴዎድሮስ የተደረገውን የመቅደላ ውጊያ ተከትሎ እልፍ ቁጥር የሌለው ቅርስ፣ ሃብት፣ ንብረት ተዘርፏል።

መቅደላ ውጊያ ላይ የተመዘበሩት ቅርሶችና ንብረት ብቻ አልነበረም ከዚህም በላይ የሰባት ዓመት እድሜ ያለውን የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል አለማየሁ ተጠልፎ ተወስዷል።

ለዘመናትም ከኢትዮጵያ የተመዘበሩ ቅርሶች እንዲመለሱ የተለያዩ ምሁራንም ሆነ ግለሰቦች እንዲህም በሃገር ደረጃ ሲጥሩ ነበር። በቅርቡ የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ የተመለሰ ሲሆን ተጠልፎ የተወሰደውን የልጃቸውን አፅም ለማስመለስም ያለሰለሰ ጥረቱ እንደቀጠለ ነው።

የተዘረፉ ቅርሶች በውሰት መመለሳቸውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ምላሽ ምንድን ነው?

ኢትዮጵያውያን 'የሌሉበት' ስለ ኢትዮጵያ የሚዘክረው ሬድ ሲ ዳይቪንግ ሪዞርት ፊልም

የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሳው ልዑል አለማየሁ እናትና አባቱን ሲያጣ ለቅርብ ቤተሰቡ መሰጠት ሲገባው ህጋዊ ባልሆነ መልኩ ወደ እንግሊዝ እንደሄደ ገልፀው በወቅቱም ደስተኛ አልነበረም ብለዋል።

ሚኒስትሯ ለዚህ ማስረጃ ብለው የሚጠቅሱት ደግሞ ንግስት ቪክቶሪያ "በሰው ሃገር ባይተዋር ሆነህ ደስተኛ ሳትሆን በመሞትህ አዝናለሁ" በማለት ለልዑሉ ጸጸታቸውን የገለጹበትን የሃዘን መግለጫ ነው።

"የንግስቲቷን ጽሁፍ ስናነብ ልባችን ይደማል፤ እናዝናለንም። ልዑሉ ወደ ሃገሩ አለመመለሱም ሌላኛው ፀጸት ነው" የሚሉት ሚንስትሯ የልዑሉን አጽም እንግሊዞች እንደሚመልሱላቸው እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል

ይህንንም ለማሳካት "የሁለቱም ሃገራት ድልድይ በመሆናቸው በእንግሊዝ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያግዙናል ብለን እናስባለን" ብለዋል።

ልዑሉ በብቸኝነት ሲሰቃይ ቆይቶም በ18 ዓመቱ እንደሞተ የታሪክ መዛግብቶች ያወሳሉ። የመጨረሻ ጊዜውን አስመልክቶ ከልዑል አለማየሁ አንደበት የተወሰደውን አሉላ ፓንክረስት በፅሁፉ አስቀምጦታል ይህም " ተመርዣለሁ" የሚል ነው።

ተጠልፎ ተወስዶ ህይወቱ ያለፈው የልጅ ልዑል አለማየሁ ህይወት አሳዛኝ እንደሆነ ህይወቱ ላይ የወጡ ፅሁፎች ያሳያሉ።

ከሞተ በኋላ እንኳን አፅሙ ኃገሩ ይረፍ ተብሎም ለእንግሊዝ መንግሥት በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም እስካሁን ምላሽ የለም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የልዑል አለማየሁ አጽም መመለስ አስፈላጊ መሆኑን ለማወቅ የዓጼ ቴዎድርስ ቁንዳላ ሲመለስ ሕዝቡ ያሳየውን ስሜት መረዳት በቂ ነው ብለዋል ሚንስትሯ።

በተለይም ከቁንዳላው መመለስ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ስሜት ከፍ ያደረገ መሆኑን እንደ ትልቅ እመርታ ጠቅሰው ሕዝቡ ቅርሶቻችን ተወስዷል የሚለው ስሜት ተቀይሮ ማስመለስ ይቻላል የሚል ጥሩ ስሜትና ተስፋ እንዲፈጠርበት እንዳደረገ ሚኒስትሯ አስረድተዋል።

የንጉሰ ነገስቱም ቁንዳላ፣ የልዑሉ አፅምና ታቦታቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ክብርና ቦታ የሚሰጣቸውና ከአለማዊ ትርጉማቸው በዘለቀ ትርጉም አላቸው የሚሉት ሚኒስትሯ በተለይም ታቦታቱ ለእምነቱ ተከታዮች መንፈሳዊ ጠቀሜታ አላቸው።

"ለእነሱ ምንም ትርጉም የላቸውም፤ ለእኛ ግን መንፈሳዊ ሕይዎትም ናቸው። ስለዚህ እነዚህን በመመለሷ አንደኛ ሰብኣዊ መብትን ታከብራለች፣ ሁለተኛው ደግሞ ትልቋ ወዳጃችን እንግሊዝ ቅርሶቹን በመመለሷ ግንኙነታችንን ከወዳጅነት አልፎ ወደ ቤተሰብነት ያሳድገዋል። በሌሎች ሃገራት ዘንድም ትልቅ ተቀባይነት እንዲኖራት አስተዋጽኦ ያደርግላታል" ብለዋል ዶ/ር ሂሩት

እንግሊዝም ሆነ የተለያዩ ቅርሶችን የዘረፉ የአውሮፓ ሃገራት እንደሚመልሱ ሲጠየቁ ኢትዮጵያውያንም ሆነ አፍሪካውያን ቅርሶቹን የሚያስጠብቁበት አሰራር የላቸውም የሚሉ ምላሾችን ይሰጣሉ።

ኢትዮጵያ የሁሉም ነገር መገኛ የሆነችና በዓለም ላይ የሚገኙ ሁሉም የአየር ንብረት አይነቶችና ዝርያዎች ያሉባትና ብዙ ጥበቦችና የራሷ ፊደል ያላት ሃገር መሆኗን የሚናገሩት ሚኒስትረወ "የዓለም ሙዚየም ነች ብለን ስለምናምን ቅርስ ከኢትዮጵያ መወሰድ ሳይሆን ወደ ኢትዮጵያ ነው መምጣት ያለባቸው እንላለን" ብለዋል።

በመሆኑም የዓለም ሙዚየም በመሆኗ ዓለም ሊጠብቃት ይገባል፤ ከዚህ አንጻር የቅርጹ መመለስ ተገቢ ነው ይላሉ ሚንስትሯ።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ወደ ፅዮን ውሰዱን ተማፅኖ

ቅርሶቹም ሆነ የልዑሉ አፅም ቢመለስ የሚቀመጥበት ቦታ መዘጋጀቱንና ለዚህም ታላቁ ቤተ መንግሥትም እንደተመረጠ ዶ/ር ሂሩት ገልፀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶቹን ቅርሶች በሙዚየማቸው ለህዝብ እንዲጎበኙ ቢያደርጉም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው የተዘረፉት ታቦታት አንድ ቤት ተቆልፎባቸው ነው የሚገኙት።

ሚኒስትሯም ስለ ታቦታቱ ጉዳይ አንስተው የእንግሊዝ መንግሥት ለመመለስ ቃል እንደገባላቸው ጠቅሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ "እኛም የምናደርገውን አድርገናን" ብለዋል ሚንስትሯ።

ምንም እንኳን በሁለቱ መንግሥታት መካከል ቅርሶቹን ለማስመለስ ውይይቶች ቢጀመሩም አንዳንድ እክሎች አጋጥመዋል። እንደ ዋነኛ ችግር የሚያነሱት በእንግሊዝ ህግ መሰረት አንድ ወደ ሙዚየም የገባ ቅርስ ተመልሶ አይወጣም።

ከዚያም ጋር ተያይዞ በውሰት ውሰዱ የሚል አማራጭ እንዳቀረቡላቸው ሚኒስትሯ በአግራሞት ገልፀዋል። "እንዴት የራሳችንን ኃብት እንዋሳል? ሰጥተናቸው ሳይሆን ተዘርፎ ነው የተወሰደው። ስለዚህ በህጋዊ መንገድ ነው መመለስ ያለበት" ብለዋል።

''አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው"

ውሰቱም የመመለሻው ጊዘው ሳይገለፅ ላልተወሰነ ጊዜ ውሰዱ የሚል አማራጭ ያቀረቡ መሆቸውን ሚኒስትሯ ተናግረው ምን ማለትም እንደሆነ ያስረዳሉ።

"በዚህ አረዳድ እነሱ እንደሚሉት 'ላልተወሰነ ጊዜ' የሚለው ሕጋቸውን ላለመጣስ እንጅ 'ጊዜው ስላልተገለጸ ላትመልሱ ውሰዱ' ማለት እንደሆነ ነግረውናል" ይላሉ ዶ/ር ሂሩት።

ይህም ሆኖ ግን ችግሮች እንዳሉት ሚኒስትሯ አልደበቁም ቅርሶቹን በውሰት ለመስጠትም ኢንሹራን መግባትን እንደ መስፈርት ይጠይቃሉ።

ባህልን በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ የቀመመው ሮፍናን

"ግን እሱን ማድረግ አልቻልንም፤ ምክንያቱም የተጠየቀው ከፍተኛ ገንዘብ ነው እነሱም 'ለእናንተ መውሰድ ለእኛ ግን ውሰት የሆነ ቃል አምጡና ህጋችንን አክብረን እንስጣችሁ' ብለውናል" የሚሉት ሚንስትሯ ይህንን ስምምነት የሚያሟላ ቃል ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሕጋቸውን ማስተካከል ካለባቸው እንዲያስተካክሉ ግፊት ለማድረግ እንደሚሞክሩ ሚኒስተሯ ተናግረው በበለጠ ግን እንግሊዝ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሊረዷቸው እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።