ኢትዮጵያ፡ ፖሊስ አንድን ወጣት ሲደበድብ በተንቃሳቃሽ ምስል ያስቀረው የዐይን እማኝ

ፖሊስ አንድን ወጣት ሲደበድብ የሚያሳየው ምስል Image copyright @Officially_Abel

ትናንት ነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ፖሊስ እጁ በእጀ ሙቅ [ካቴና] የታሰረን ወጣት ሲደበድብ፤ አብሮት የነበረው ሌላኛው ፖሊስ ወደላይ ሲተኩስ፤ አንዲት እናት ለመገላገል ሲሉ ሲገፈተሩ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል መነጋጋሪያ ሆኗል።

ሕግ በሚያስከብሩ የፖሊስ አባላት ድብደባው መፈፀሙ ደግሞ ብዙዎችን አስቆጥቷል።

የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ የማን ነው?

“በአሁኗ ኢትዮጵያ በፀረ ሽብር ሕጉ ክስ መኖር የለበትም” ዳንኤል በቀለ

አዲስ አበባ ቄራ ጎፋ ማዞሪያ አካባቢ ተቀረፀ የተባለው ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል እንዲሁም ከዚህ ቀደም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ተመሳሳይ ድርጊቶች ፖሊስ ዜጎች ላይ እየፈፀመ ስላለው የጭካኔ ድርጊት ምስክር ነው ሲሉ በርካቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይህንን ተንቀሳቃሽ ምስል የቀረፀውንና አቤል በሚል ስም በትዊተር ገፁ ያጋራውን ወጣት ቢቢሲ አነጋግሮት ነበር።

አቤል እንደሚለው በወቅቱ ከጎፋ ገብርዔል ወደ ቄራ በሚወስደው መንገድ አካባቢ ሲደርስ ሰው መበታተን እና መሮጥ ጀመረ። ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን የቀጠለው አቤል "ሲደበደብ የነበረው ልጅ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ከሚታዩት እናት ኋላ ሲሄድ ነበር" ይላል።

እየሄዱ ሳሉም ወጣቱና ፖሊሱ መገፋፋት ጀመሩ። ከዚያም ሲደበድበው የነበረው ፖሊስ ጠመንጃውን አብሮት ለነበረው ፖሊስ ይሰጠዋል።

ፖሊሱ ጠመንጃውን አቀባብሎ መተኮስ ጀመረ [የመጀመሪያውን ተኩስ በቪዲዮው አላስቀረውም]።

ከዚያም ወጣቱ እጁን ሰጠ። አሰሩት። ልክ እንዳሰሩት መምታት ጀመሩት። በአካባቢው በርካታ ሰው ቢኖርም ማንም ሰው ሊገላግል የደፈረ አልነበረም። ሁሉም ሰው ፈርቶ እየሸሸ ነበር። በዚህ መሃል መሳሪያ የያዘው ፖሊስ "ዞር በሉ" እያለ ሁለተኛ ጥይት ይተኩስ ነበር።

'እናቱ ናቸው መሰል' ያላቸው ሴትም በተደጋጋሚ ሊገላግሉ ሞከሩ። ይሁን እንጂ በደብዳቢው ፖሊስ ያለምንም ርህራሄ ሲገፈተሩና በአካባቢው ያለ ሰው እንዳይጠጉ ሲይዛቸው አቤል አስተውሏል።

አቤል እንደሚለው በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ምንም ማድረግ አልቻሉም ነበር። መሳሪያ የያዘው አንደኛው ፖሊስ እየተኮሰ "እንዳትጠጉ" እያለ እያስፈራራ ስለነበር ማንም ደፍሮ ሊገላግል የሞከረ አልነበረም።

"በወቅቱ ማንም የተጠጋው ሰው አልነበረም፤ በፍርሃት ይመስለኛል የተኮሰው። እጁ ላይ መገናኛ ራዲዮ ይዞ ነበር፤ ደውሎ እርዳታ መጥራት ይችል ነበር ከአቅሙ በላይ ከሆነም" ሲል ፖሊሱ ለምን መተኮስ እንዳስፈለገው እንዳልገባው ይናገራል።

"በአንድ ሀገር ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ክልሎች ሊኖሩ አይገባም" ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ

ከዚያ በኋላ መኪናው መንቀሳቀስ ስለ ጀመረ አቤል ቪዲዮውን መቅረፅ አልቻለም። ተንቀሳቃሽ ምስሉ አጭር የሆነውም ለዚያ ነው ይላል።

የዐይን እማኙ እንደሚለው እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎችን በቪዲዮ እየቀረፀ በማህበራዊ ሚዲያ ሲያጋራ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ያጋጥማሉ የሚለው አቤል "ፖሊሶችን ለምንድን ነው የምትማቱት? ስንላቸው 'ምን አገባችሁ እናንተንም እነርሱ ጋር እንዳንቀላቅላችሁ' ይሉን ነበር" ሲል የማን አለብኝነት ምላሽ እንደሰጡት ያስታውሳል።

የህግ ባለሙያዋ ብሌን ሳህሉ በአንድ ወቅት 'ሃሽታግ ነግበኔ' ብላ ትዊት አደረገች። ከዚያም የእርሷን ተቀብሎ የራሱን ጽሁፍ መፃፍ እንደጀመረ ይናገራል።

"ፖሊስ ያልተገባ ኃይል ሲጠቀም ማንም የሚናገራቸው ሰው የለም፤ ሲቀጡ አናያቸውም፤ አንሰማም፤ በመሆኑም መረጃው ሰዎች ጋር እንዲደርስ ነው የቀረፅኩት" ሲሉ ምክንያቱን ያስረዳል።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን የጠየቅናችን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር "ስብሰባ ላይ ነኝ" በማለታቸው ሃሳባቸውን ማካተት አልቻልንም። ለኮሚሽነሩና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጋር ያደረግነው የስልክ ጥሪም ምላሽ አላገኘም።

ይሁንና ዛሬ ጠዋት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በይፋዊ ፌስቡክ ገፁ ላይ የፖሊስ አባላቱ የፈፀሙትን ድርጊት እያጣራ መሆኑን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ትናንት ከረፋዱ 5 ሰዓት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ስሙ ቄራ ጎፋ ማዞሪያ በድለላ የተሰማሩ ሁለት ቡድኖች መካከል የተፈጠረን አለመግባባት ለማብረድ ፖሊሶቹ ጣልቃ እንደገቡ ያስረዳል።

ፖሊሶቹ ግለሰቦቹን ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሄዱ በሚያደርጉበት ጊዜም አለመግባባቱ በመካረሩ የፖሊስ አባላቱ ድብደባ እንደፈፀሙና እንደተኮሱ ኮሚሽኑ ይገልፃል።

የፖሊስ አባላቱ አዲስና በቅርቡ የተቀላቀሉ መሆናቸውን የገለፀው ኮሚሽኑ የፈፀሙት ድርጊት ግን ያልተገባ በመሆኑ ጉዳያቸው በወንጀልና በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት እየተጣራ መሆኑን አስታውቋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ