"የስብኀት ሥራዎች ለረዥም ዓመታት ተቀምጠው የተገኙትና የተረፉት በኔ ምክንያት ነው" ስንዱ አበበ

ስንዱ አበበ

አዲስ አበባ ነው ተወልዳ ያደገችው። ዘበኛ ሰፈር ብትወለድም ያደገችው አዲሱ ገበያ ነው። ከአምስት ልጆች መካከል ሦስተኛ ልጅ ናት። ጋዜጠኛና ደራሲ ስንዱ አበበ ፊት ለፊት የምትናገር፣ ላመነችበት ወደ ኋላ የማትልም ናት። ከፀሀፊነት፣ ጋዜጠኝነት እና ከአሳታሚነት በተጨማሪም በመንግሥታዊ መዋቅር ለመሳተፍ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነትም ተወዳድራ ነበር።

መኀልየ መኀልይ ዘ ካዛንቺስ፣ እብዱ፣ ራምቦ፣ ጠብታ ፍቅር፣ ከርቸሌ በውስጥ ዓይን፣ ወንድም ጌታ፣ ሲራኖ፣ የባለቅኔው ምህላ እና ዛዚ የተሰኙት መጻህፍት የታተሙት በስንዱ አበበ አሳታሚ በኩል ነው። እነዚህ ሥራዎች የታዋቂ ደራሲያንና የራሷ የስንዱ አበበም ጭምር ናቸው። መኀልየ መኀልየ የተድባበ ጥላሁን፣ ወንድም ጌታ እና ሲራኖ የባሴ ሐብቴ፣ ዛዚ የስብኀት ገብረ እግዚአብሔር ስራዎች ሲሆኑ፣ የዜማና ግጥም ደራሲው ሙሉጌታ ተስፋዬ የግጥም ስብስቦችን የያዘው መጽሐፍ ደግሞ የባለቅኔው ምህላ ይሰኛል። ስንዱ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር በስራዎቿ ዙሪያ ቆይታ አድርጋለች።

ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ፡ ያናገሩና ያነጋገሩ ድርሰቶቹ

ወደ አሳታሚነት ለመግባት የገፋሽ ምን ነበር?

አንደኛ ጋዜጠኝነት ወከባው ምኑም ምኑም ታከተኝ፤ አስጠላኝ። ሁለተኛው መኀልየ የሚለውን መጽሐፍ ሳየው በጣም ነው የተናደድኩት። እንዴት እንዲህ ዓይነት ነገር ይከናወናል? ይኼማ ታትሞ ሕዝቡ መፍረድ አለበት ብዬ የማሳተም ሥራዬን ተድባበ ጥላሁን[ደራሲውን] ጠይቄ በመኀልየ መኃልይ ዘ-ካዛንችስ ጀመርኩ።

በወቅቱ ትስሪ የነበረው ለየትኛው ጋዜጣ ነበር?

ኡ. . . እኔ በጣም ብዙ ጋዜጣ ላይ ነው የሰራሁት። ከኢህአዴግ ልሳኑ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጀምሮ፣ ኔሽን፣ ሪፖርተር. . . ብዙ ጋዜጣ ላይ ጽሑፎቼ ታትመዋል። አንዱ አላትምም ቢለኝ ወደ ሌላው ወስጄ እሰጣለሁ። በመስራት ደረጃ ግን ተቀጥሬ የሰራሁትና ረዥም ዓመታት የቆየሁባቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲና ሪፖርተር ጋዜጦች ናቸው።

አንቺ መኀልየ መኀልስታትሚ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሳታሚነት የሚሰሩ በርካታ ግለሰቦች ነበሩ?

ኡ. . . አልነበሩም። አንደኛ መጽሐፍ ማሳተም ውድም ነው። የሚጠይቀው ገንዘብም ብዙ ነው። በወቅቱ በግል የሚያሳትሙ የነበሩት ብሔራዊ አካባቢ እንደነ ዓይናለም፣ እነርሱም አሁን ነው ፌመስ [ዝነኛ] የሆኑት እንጂ፣ ያኔ አልፎ አልፎ ነበር የሚሞክሩት። እነ ክብሩ እንጂ ሌላ ብዙም አልነበረም።

ሴት አሳታሚዎችስ ነበሩ?

አይመስለኝም. . .

መኀልየ መኀል እንደታተመ በጣም ዝነኛ ነበር። ያለ ማጋነን እንደ ትኩስ ኬክ የተቸበቸበ መጽሐፍ ነበር።

አዎ!

ኢትዮጵያውያን 'የሌሉበት' ስለ ኢትዮጵያ የሚዘክረው ሬድ ሲ ዳይቪንግ ሪዞርት ፊልም

ከዚያም በኋላ በእርሱ የአጻጻፍ ዘይቤ እና የመጽሐፉን ርዕስ በተመሳሳይ መልኩ በመቅዳት ሌሎች መጻሕፍትም ታትመዋልበወቅቱ የነበረው የአንባቢዎች ምን ምላሽ ምን ነበር?

ምላሹ ሁለት ፅንፍ የያዘ ነበር። አንደኛው ወገን 'ባህላችን ተነካ፣ ተደፈርን፣ እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ መታተም የለበትም' በማለት አክርሮ የሚቃወም ሲሆን ሌላው ደግሞ 'ይኼ በጣም ጠቃሚ መጽሐፍ ነው' የሚል ነበር። ጥናት ላይ ተመስርቶ የተጻፈ መጽሐፍ ስለነበርም በተለይ ከጤና ቢሮ አካባቢ በጣም ድጋፍና አድናቆት ነበረው። እነዚህ ሁለት አስተያየቶች እንዳሉ ሆነው የግል የምትላቸው ሚዲያዎች ሆነ ብለው ነጌቲቭ [አሉታዊ] ጎኑ ላይ ያተኮሩ ፅሁፎች (አርቲክሎች) ነበር የሚያትሙት።

ካልተሳሳትኩ ያኔመጽሐፉ ገበያ ላይ በዋለበት ወቅት ስለ ኤችአይ ቪ በጣም ይወራ ነበር አይደል?

በጣም. . .

ምን ያህል ጊዜ ታተመ?

አምስት ጊዜ፣ ወዲያው ወዲያው ነው ያተምኩት። መጽሐፍ ላይ 'አምስተኛ፣ ስምንተኛ እትም' የሚል መጻፍ የጀመረው አሁን ነው። በዚያ ዘመን ተደጋግሞ የታተመ መጽሐፍ መኀልየ መኀልየ ነው።

"የኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ አልተጠናም" ዶክተር አሰፋ ባልቻ

ስንት ኮፒ ተሸጠ?

በኔ ሕትመት ሠላሳ ሺህ ግድም

መጽሐፉን ከአንቺ በላም ያሳተመው ሌላ አካል አለ ማለት ነው?

አዎ። እኔ እዚህ ከመጣሁ በኋላ አሳትመውታል።

በደራሲው ፈቃድ?

አዎ!. . . ደራሲውን ሲጠይቁት... የምልህ እኔ እንዲታተም እፈልጋለሁ። እንዲነበብ እፈልጋለሁ እናም ተድባበ ሲጠይቀኝ የሚያትመው ሰው ከተገኘ የግድ እኔ መጠበቅ የለብኝም ብዬ ፈቀድኩ። ተድባበ እንዳተሙት ነግሮኛል ... አላየሁትም፤ መታተሙን ግን ሰምቻለሁ።

መኀልየ እንዳልሽኝ የመጀመሪያ ሕትመትሽ ነው። ሁለተኛ ያሳተምሽው የማንን ሥራ ነው?

የመስፍን አሸብር 'ጠብታ ፍቅር' የሚል የግጥም መጽሐፍ ነው። መሥፍን አሸብር አብሮ አደግ ጓደኛዬ ነው። በጣም የምወደው ሰው ነው። ጋዜጠኛ ነው ለረዥም ዓመታት ሬዲዮ ፋና ሰርቷል። መስፍን ሲሞት፤ ሬዲዮ ፋና የመስፍንን ግጥሞች አትማለሁ ብሎ እኔ ጋርም የተወሰኑ ግጥሞች ስለነበሩት አምጪ ልናሳትም ነው ብለውኝ ሰጥቻቸዋለሁ። ያኔ ደግሞ ፎቶ ኮፒም ምንም የለም ኦሪጂናል [ዋናውን ቅጂ] ነው የሰጠኋቸው። እና ለስምንት ዓመታት ሳያትሙት መቅረታቸው በጣም ነበር የሚያብሰለስለኝ።

እና መኀልየን አትሜ ፍራንክ ሳገኝ ወዲያውኑ የመስፍንን ሥራ ነው ያሳተምኩት። ጓደኛዬም ስለሆነ ሐውልቱን የማቆም ያህል ማለት ነው።

"ኢትዮጵያዊ ታሪኮችን ወደ ዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ ማምጣት ፈታኝ ነው" ዘረሰናይ መሐሪ

የሙሉጌታ ተስፋዬን የግጥም ራዎች [የባለቅኔው ምህላ] ያሳተምሽው አንቺ ነሽ። የግጥም ስራዎችን ስለምታደንቂ ነው ወይስ ጓደኝነትን ስለምታስቀድሚ ነው እነዚህ ስራዎች ያሳተምሽው?

ጓደኝነት አንድ ነገር ነው። ነገር ግን እኔ ያተምኳቸው መጻህፍት ዋጋ (ቫልዩ) ስለምሰጣቸው ነው።ትውልዱ ሊያውቃቸው ሀገሪቱ ውስጥ ታትመው ሊኖሩ ይገባል [የምላቸውን ነው።]፣ ቢዝነስ አይደለም እንደሰዉ የምሰራው። ድሮ፣ ከኛ በፊት በነበረው ጊዜ ኩራዝ ነበር፤ ኩራዝ ዋጋ አላቸው፣ ሀገሪቱን ይመጥናሉ የሚባሉ ስራዎችን ያትም ነበር። ኩራዝ ከጠፋ በኋላ ግን ሥራው [አሳታሚነት] የነጋዴው ነው የሆነው። ነጋዴ ደግሞ የሚያዋጣውን ብቻ ቶሎ ቶሎ የሚሸጡትን 'ቤስት ሴለር' የሚባሉትን እንጂ ዋጋ (ቫሊዩ) ያላቸውን ማተም ተዉ። እና እኔ እርሱን ጋፕ [ክፍተት] ለመሙላት ነበር ሀሳቤ።

በርግጥ አሁን እንዳልሽኝ አንድን መጽሐፍ ለማሳተም አንቺ ዋጋ የምትሰጪያቸው መሆን አለባቸው። ነገር ግን ሌሎች መጽሐፍን ለማሳተም የምትመርጪበት መስፈርት አለሽ?

ዉይ. . . በጣም ብዙ። በእኔ የንባብ ባህልና ልማድ ያነበብኳቸውንና የወደድኳቸውን ነገሮች ኮፒ አድርጌ አስቀምጣለሁ። እና በጣም የብዙ ሰዎች ስራ ነው እጄ ላይ የነበረው። እና ሁሌም ነው የሚቆጨኝ አለመታተማቸው ነው። እና እሱ ቁጭት ነው ወደ ስራውም የገፋኝ።

ከዝነኛ ደራሲያን ጋር ትውይ ነበር። ጋሽ ስብ ገብረ እግዚአብሔር፣ ባሴ ሐብቴ ወዳጆችሽ ነበሩ። እንደነሱ ያሉ ወዳጆች በዙሪያሽ መኖራቸው ወደ አሳታሚነት ገፍቶሽ ይሆን?

አዎ። የጋሽ ስብኀት ስራዎች በጣም ብዙ አመታት እኔ እጅ ነው የነበሩት። 'ሌቱም አይነጋልኝ'፣ 'ትኩሳት'፣ 'ሰባተኛው መልዓክ'፣ በእሳቸው እጅ የተፃፉት እኔ ጋር ተቀምጠው ነበር። እና በጣም ነበር እነርሱም እንዲታተሙ እፈልግ የነበረው።

ሳይጠፉ ለረዥም ዓመታት ተቀምጠው የተገኙትና የተረፉት በኔ ምክንያት ነው ብዬ ነው የማስበው። ድሮ እንደውም 'ስብኀት ስራ ላይ ቆልፋ' ምናምን እያሉ፣ ይወቅሱኝ ነበር።

'ትኩሳትን'ና 'ሌቱም አይነጋልኝ'ን ታይፕ አስደርጌ (አስፅፌ) በኪራይ አሸናፊ መጻህፍት መደብር ለሚባል ሰጥቸው ነበር። እያከራየ ትንሽ ለአቦይም [ስብኀት] እንዲሰጣቸው እርሱም እንዲጠቀም አንባቢም አንዲያነባቸው በማሰብ።

ከዚያ በኋላ የመታተም እድል ሲመጣ መጀመሪያ 'ታድቶ' (በሳንሱር ምክንያት ተቆራርጦ) ታተመና በጣም አዘንኩ፤ ተናደድኩ። በኋላ ኖሮ ኖሮ እንደ ተጻፉ፣ እንደወረዱ ታትመዋል። በጣም ሀሪፍ ነው።

ሜጋ አሳታሚ ነበር አይደል 'አሳድቶ' ያሳተመው?

አዎ ሜጋ ነው ያሳተመው። የማይሆን ነገር እኮ ነው የሰሩት።

የሕዝቡን ባህል፣ አኗኗር ወግና ስርዓት ታውቂዋለሽ በጋዜጠኝነት ለረዥም ጊዜም ሰርተሻል። ታዲያ ለምንድን ነው የስብኀት ስራዎች መታደታቸው ያበሳጨሽ?

ጋዜጠኝነት ላይ ኤዲቲንግ የሚባል ነገር አለ። ያ ለጋዜጠኝነት ስራ ሊሰራ ይችላል። እንደነዚህ አይነት ስራዎች ላይ ግን እኔ አልቀበልም። ወይ ማተም ነው፤ ወይ አለማተም ነው፤ በቃ ተጽፏል። ለምንድን ነው እጁን ቆርጠህ፣ እግሩን ቆርጠህ የምታሳትመው? ምን ስለሆንክ ነው? እምልህ ልክ አይደለም። እኔ ያኔ ከነደምሴ [ደራሲ ደምሴ ጽጌ]ጋርም ተጣልተናል። ኤዲት እያደረግነው ሲሉ ሁሉ ኡኡ ብያለሁ። የሚሰማኝ ነበር የጠፋው። 'ኤዲት' ተደርጎ ከሚታተም አይታተም፤ ጊዜው ሲደርስ ይታተማል ብል ኖ . . . ኖ ብለው፣ ሜጋም ፍራንኩን ስለሚፈልገው ታተመ። ኤኒዌይ[ለማንኛውም] ለኔ 'ኤዲት' የተደረገው አልተመቸኝም። እግዜር የተመሰገነ ይሁን ጊዜው ሲደርስ ኦሪጂናሎቹ (ዋና ስራዎቹ) ታትመዋል።

መኀልየ መኀል ወደ ሌላ ቋንቋ መተርጎሙን ሰምቻለሁ ልበል?

ቆይቷል፤ ወደ ፈረንሳይኛ ከተተረጎመ ቆይቷል። ላርታዥ ሚኖተር የሚባል አንድ የፈረንሳይ አሳታሚ፣ መጽሐፉ በጣም ዝነኛ በነበረበትና ጋዜጦቹ ልክ አይደለም በማለት በሚጮሁበት ወቅት ሰማ። ያኔ ደግሞ ሌሎች ሰዎች መጽሐፉን መተርጎም ጀምረው ነበር። አንድ ወቅት አንድ ብሩክ የሚባል ልጅ መጥቶ 'መኀልየ መኀልየን እኮ እየተረጎምነው ነው' አለኝ። 'ወደ ምን ቋንቋ' ስለው 'ወደ ፈረንሳይኛ' 'ከማን ጋር' ስለው 'ሊሴ ከሚያስተምር መምህር ፋንስዋ ከሚባል ጋር' 'ለምን' ስለው 'ወደነው' አለኝ። 'ጥሩ ነው ተርጉሙት' ብዬው ረዥም ጊዜ ቆይቷል።

በኋላ ይኼኛው አሳታሚ መጥቶ 'ስለመጽሐፉ ምንነት እንድናውቅ ትንሽ ኤክስትራትክት [ቅንጭብ ታሪክ] የሚተረጉምልን' ሲሉኝ፣ ' ኧረ ተርጉመነዋል የሚሉ አጋጥመውኝ ያውቃሉ' ብዬ እነርሱን ፈልጌ አገናኘኋቸው። ከዚያ ሲያዩት ማተም ፈለጉ፤ ለማሳተም ሲጠይቁኝም 'አትሙ' ብዬ ፈቀድኩ። ቅድሚያ ተድባበን ጠየቅሁት እርሱ በመጽሐፉ ላይ አንቺ ማዘዝ ትቺያለሽ ከእኔ ወጥቷል አለኝ። ፈቀድኩላቸው።

ሰዎቹ መጀመሪያ በፍላጎት ነበር መተርጎም የጀመሩት በኋላ ግን አሳታሚው ስራው እንዲጠናቀቅ ከፍሎ አስተረጎማቸው።

ከዚህ ውጪ አንቺ ካሳተምሻቸው ውስጥ ወደሌላ የተተረጎሙ ስራዎች አሉ?

የለም።

ከማሳተም ውጪ የራስሽ የሆኑ ስራዎች የፃፍሽው አለ?

ካተምኳቸው ውስጥ ሁለቱ የኔ ስራዎች ናቸው።

የትኞቹ ማለት ናቸው?

አንዱ 'ከርቸሌ በውስጥ ዓይን' ይላል እውነተኛ ታሪክ ነው። ጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ ነው። ሁለተኛው 'ራምቦ' ነው። 'ራምቦ ድንቅ ሰው' ይሰኛል። ራምቦ ፈረንሳያዊ ገጣሚ ነው።

ሐረር ውስጥ የኖረው ራምቦ ነው አይደል?

አዎ አስር ዓመት ሐረር ኖሯል። እዚያ የኖረበትም አሁን ሙዚየም ሆኗል። ለንጉሥ ምኒሊክ መሳሪያ ሸጧል። የሚገርም ሰው ነው በጣም፣ በጣም። እርሱንም የፈረንሳይ ኤምባሲ ስፖንሰር [ ድጋፍ] አድርጎልኝ ነው ያጠናሁት። ምክንያቱም መጀመሪያ ራምቦ፣ ራምቦ ሲሉ ምንድን ነው እናንተ ታጋንናላችሁ እንጂ ምንድን ነው ራምቦ ስል እስቲ አንቺ ቼክ አድርጊው (አጥኚው) አሉኝ።

እኔ የማውቀው' የሰከረ መርከብ' የሚለውንና ዶ/ር ብርሃኑ አበበ የተረጎሙትን አንድ ግጥሙን ብቻ ነበር። በጣም ነበር ያን ግጥሙን የምወደው። በኋላ ግን የሕይወት ታሪኩን ሳጠና የልጄ ያህል ነው የወደድኩት።

ልጄ ስትይ ወልደሻል እንዴ?

አልወለድኩም (ሳቅ) ዘጠኝ መጽሐፎችን ግን ወልጄያለሁ፤ አዋልጃለሁ።

በጋዜጠኝነት ሕይወትሽ አወዛጋቢና አከራካሪ አስተያየቶችን ስትሰጪ እና ስትጽፊ አስታውሳለሁ። አንቺ ራስሽን አወዛጋቢ እና አከራካሪ ጉዳዮችን እንደሚያነሳ ሰው ትቆሪያለሽ?

እንደሱ ሳይሆን። የተማርኩት የሰለጠንኩት ዘርፍ 'ክሪቲካል ቲንኪንግ'(ጥልቅና ተንታኝ እሳቤ)ና ኢንቨስቲጌቲቭ ጆርናሊዝም [የምርመራ ዘገባ ጋዜጠኝነት] ነው። ስለዚህ በተማርኩት መሰረት ነው ለመስራት የሞከርኩት። ብዙ ሰው ኡኡ ይላል። እኔ ግን ያየሁትን የሰማሁትን እንደገና ደግሞ ሙያው እንደሚጠይቀው፣ ሁሉንም አካላት፣ ጉዳዩ ላይ ይመለከታቸዋል የሚባሉትን አካላት በሙሉ እድል በመስጠት 'ፌር' [ሚዛናዊ] የሆነ ነገር ነው የምሰራው። ግን ይናደዳሉ። እኛ ሀገር ደግሞ አንደኛ በሚዲያው ላይ ባለቤቶቹ ከጀርባው ስላሉ የሚተች ስራ ስሰራ አይፈለግም ነበር። እና አብዛኛው ጽሑፌ በጭቅጭቅ ነበር ቢሮ ውስጥ ራሱ የሚታተምልኝ። እንጂ ለመለየት፣ አከራካሪ ለመሆን በማለት አይደለም።

ሴት በመሆኔ ነው እንጂ ይህንን ሀሳብ ወንድ ቢለው ብለሽ አስበሽ ታውቂያለሽ?

ኖ [በጭራሽ] ሴት ምናምን የሚል ሀሳብ አይመጣብኝም። ግን እኔ ለቆምኩለት ነገር አላፈገፍግም። እስከ ጥግ ድረስ ነው የምሄደው። አንተ እንቢ ብትለኝ ቀጥሎ ያለው ሰውዬ ጋር፣ ቀጥሎ ያለው እንቢ ቢለኝ የበላዩ ጋር እሄዳለሁ። አላቆምም፤ እልህ ስለሚይዘኝ አይ እንቢ ብለዋል ብዬ አላቆመውም። ምክንያቱም እኔ በጣም ዋጋ የምሰጠው ነገር ጊዜ ነው። ጊዜዬን ያጠፋሁበትን ጉዳይ ልትከለክለኝ አትችልም።ማንም እንዲያሳምነኝ መልካም ፈቃድ አለኝ። ስንዱ ይህ ጉዳይ በዚህ መልኩ ችግር ያመጣል። መስተካከል አለበት ካልከኝና ከታየኝ እሺ እላለሁ። ካልመሰለኝ ደግሞ እስከ ጥግ ነው አላቆምም። እና ስለምከራከርና ስለምጨቃጨቅም ነው ልዩ የምመስላቸው።

ለሕዝብ ተወካች ምክር ቤት አባልነት ተወዳድረሽ ነበር አይደል?

አዎ! ምርጫ 97 ነዋ ያውም ከባዱ ጊዜ።

አሸነፍሽ ወይስ ተሸነፍሽ?

እንዴ ቅንጅት አይደል እንዴ ጆከር ጥሎ የቦነሰው (በከፍተኛ ድምፅ ነው ያሸነፈው)

በግልሽ ነበር የተወዳደርሽው?

አዎ በግሌ ነው የተወዳደርኩት።

በቂ የሕዝብ ድምጽ አግኝተሽየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትብትገቢ ኖሮ ምን ለማሳካት ነበር ሀሳብሽ የነበረው?

ዋናው ዓላማዬ ለመወዳደር ከጻፍኩት የመወዳደሪያ ሀሳብ ውጪ በግል አንደኛ ፕሮቴክሽን [ጥበቃ]ፍለጋ ነው። ጋዜጠኛ ነበርኩ፤ እና በብዙ ጉዳዮች ስጋትና እየተጠራህ በፖሊስ መጠየቅ በጻፍክ ቁጥር የሚያስደነግጡህ ነገሮች ነበሩ፤ ከእነሱ ፕሮቴክሽን [ከለላ]ፍለጋ ነው። ሁለት ፋይሎችን እንደልብ ለማየት ነው። ብዙ ሐሜቶች ብዙ ጭቅጭቆች አሉ። ግን ፋይሎቹን ለማየት አቅም የለንም። መንግሥት ይከለክልሀል። ወይ ባለሀብት ይከለክልሀል። ብቻ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ስትሆን አቅም ይሰጥሀል እነዚህን ጉዳዮች፣ ፋይሎች ለማየት፣ ኢሚውኒቲ ራይት [ያለመከሰስ መብት] አለህ። ስለዚህ በርከት ያሉ ስራዎችን ለመስራት ነበር ሀሳቤ የነበረው።

የትኞቹን ፋይሎች ነበር በወቅቱ ለማየት ትፈልጊ የነበረው?

ለምሳሌ በከፍተኛ ደረጃ ብሔራዊ ባንክ ላይ ይካሄድ የነበረውን ዝርፊያ፣ ጉሙሩኩ፣ ባለስልጣናቱ። ብዙ ናቸው በጣም ብዙ።

ዝም ብሎ አንድ የሰላሳ፣ የሰላሳ አራት ዓመት ልጅ ሚሊዮነር ሆነ ይሉሀል። እኛ ከተማው ላይ ተወልደን አድገን ሰባራ ሳንቲም የለንም። ከየት መጡ የምትላቸው አንድ ፍሬ ልጆች ግን ሚሊዮነር መሆናቸውን ትሰማለህ። እነዚህ ጥያቄዎችና ጉዳዮችን ለመመርመርና ለመከታተል አቅም ይፈልጋል። አቅም ስልህ ደግሞ በተለይ ፕሮቴክሽን [ከለላ]።

የምልህ ሐሜቱ፣ ጭቅጭቁና ጥቆማው እኮ አለ። ግን ለማጣራት ስትሄድ ፋይሉን የሚሰጥህና የሚፈቅድልህ አካል የለም። ስለዚህ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ከሆንክ ግን እነዚህን [አካላት] ለመጠየቅ ማንም ሊከለክልህ አይችልም፤ መታወቂያው ራሱ በቂ ነው። ምክንያቱም የ100ሺህ ሕዝብ ድምጽ ነህ። ስንዱ ብቻ አይደለችም። ከስንዱ ጀርባ የ100 ሺህ መራጭ ሕዘብ ድምጽ ይዣለሁ ማለት ነው።

የምትኖሪው በኪራይ ቤቶች ቤት አራት ኪሎ ስለነበር፣ የምትሰሪውም ለፓርቲው ልሳን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስለነበር፣ የኢህአዴግ ደጋፊ እንደነበርሽ በተደጋጋሚ ሲነሳ አስታውሳለሁ። በወቅቱ አንቺ የኢህአዴግ ደጋፊ አልነበርሽም?

እኔ የምቃወመውም ሆነ የምደግፈው የግል የሆነ ነገር የለም። ካለው እንቅስቃሴ ውስጥ ልክ የሆነውን ልክ ነው እላለሁ። ልክ ያልሆነውን ልክ አይደለም እላለሁ። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሲቀጥረኝ መጀመሪያ ዩኒቨርስቲ እየተማርኩ ቲያትር ትምህርት ክፍል ልግባ ብዬ ስከለከል ግቢ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ አደረግኩ። ለብቻዬ!

ማለት ከመንግሥት ፈቃድ አውጥቼ፣ ሕጉን ተከትዬ ማለት ነው። እርሱን ሲያዩ እኛ ጋር ስራ ግቢ ሲሉኝ አላመነታሁም። ሄጄ ገባሁ፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ። ያኔ አብዮት ነው፤ ለውጥ ነው። ብዙዎቻችን ተስፋ አድርገናል ለውጡ ጥሩ ነገር ያመጣል ብለን። ግን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ገብቼ እየሰራሁ ብዙ ልክ ያልሆኑ ነገሮች አየሁ። እናም ሶስት ዓመት ያልሞላ ሳንሰራ ነው አብረን የገባነው በሙሉየ ተባረርነው። ። ሁላችንም በአንድ ላይ ተጠራርገን ነው የወጣነው።

እና ባጋጠመኝ ጉዳይ ብዙ ነገር የማየትና መደናገጥ ይዤ ነው የወጣሁት። ይህን እያየን፣ ይህን እየሰማን እንዴት እንዲህ ይሆናል? የሚል ስሜት ይፈጠርብሀል እና እሱኑ ነው ይዤ የቀጠልኩት።

የሰልፉን ጉዳይ ካነሳሽው. . . ስለ አንቺ የሚያነሱ ሰዎች 'ስንዱ እኮ ብቻዋን ሰልፍ የወጣች ነች' ይላሉ። በወቅቱ ለብቻ ሰልፍ መውጣት፣ ያውም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ ከባድ አልነበረም?

ንዴተኛ ስለሆንኩ እኮ ነው። ከባድ መሆን አለመሆኑን በምን ታውቃለህ? በወቅቱ ወጣት ነኝ፣ ንዴት ተሰምቶኛል። የምፈልገው የትምህርት ክፍል እንዳልገባ ተከልክያለሁ፣ ተበድያለሁ የሚል ስሜት አዳብሬያለሁ። ስለዚህ መጀመሪያ ጠየቅሁ። ከትምህርት ክፍሉ ጀምሬ ከዚያ ቋንቋዎች ጥናትን ጠየቅሁ። ከዚያ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ጠየቅሁ። ማንም መልስ የሚሰጥ የለም።

ለነገሩ አብዮት ነው። ሁሉም ፈርቷል። ተደነጋግጧል። እና ሴኔቱ ፈርሷል። እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን መጨረሻ ላይ ሊፈታቸው የሚችለው ሴኔቱ ነበር። የዩኒቨርስቲው ሴኔት የለም። እና እኔ በንዴቴ እያንዳንዱን እርከን እየተከተልኩ ሰልፍ ጋር ደረስኩ።

መፈክር ይዘሽ ነበር?

ኦፍ ኮርስ! (በትክክል)፣ ዘፈን ሁሉ እዘፍን ነበር፤ ሰው ከተሰማራ እንደየስሜቱ የሚለውን እዘፍን ነበር። (ሳቅ)

ምን ይል ነበር መፈክሩ?

"የዩኒቨርስቲ መምህራን የተማሪዎች ፍላጎት ላይ መቀለድ ያቁሙ" የሚል ነበር። "ባለሰልጣናት ስልጣናችሁን እኛን ለመጨቆኛ አታውሉት" የሚልና ሌላም መፈክርም አሰማ ነበር።

መጀመሪያ የት ትምህርት ክፍል ነበር የተመደብሽው?

የአማርኛ ቋንቋ

በኋላ ወደምትፈልጊው የቲያትር ትምህርት ክፍል መደቡሽ?

ቀረ እንጂ! በወቅቱ ውሳኔ የሚሰጥ ጠፋ። ስለዚህ ዊዝድሮው [ለጊዜው ለማቋረጥ መልቀቂያ ጠይቄ] አድርጌ ወጣሁ። ከዚያ ጋዜጠኝነት ቀጠሩኝ፤ በዛው ጋዜጠኝነት ውስጥ ቀልጬ ቀረሁ። ግን አስተማሩኝ ጋዜጠኝነት።

የት ተማርሽ ጋዜጠኝነት?

በዩኒቨርስቲ ደረጃ ሳይሆን ከየቦታው አስተማሪ ያመጡና በየአንዳንዱ ጉዳይ ላይ የሶስት ወር፣ የስድስት ወር ስልጠና ይሰጡን ነበር። እንደዛ እያደረጉ ነው ያሰለጠኑን።

ከበርካታ ታዋቂ ደራሲያን ጋር እንደማሳለፍሽ፣ የበርካታ ደራሲያንን ስራ እንደማንበብሽ የማን ስራ የበለጠ ይመስጥሻል?

ሙሉጌታ ተስፋዬና ጋሽ ስብኀት። ስራቸው ውስጥ ደግነታቸው ቸርነታቸው ሁሉ ይታያል። እኔ መርዝ ከመድኀኒት እየቀላቀሉ የሚግቱንን ጸሐፊያን አልወድም፤ ችግር አለብኝ። እገሌ ከእገሌ ልልህ አልችልም። ግን ብዙ ጽሑፎች መርዝ ከመድኀኒት የቀላቀሉ ናቸው። የሆነ የፀብ ደቦን የሚሰብኩ ምናምን ናቸው። እነ አቦይና ሙሉጌታን ስታይ ግን እንደሱ አይደሉም። ማህበረሰቡን የሚወዱ ክብር ያላቸው ናቸው። ስለዚህ እነርሱን ነው የምወደው። ባሴ ሐብቴንም በጣም ነው የምወደው።

ከኢትዮጵያ ከወጣሽ ምን ያህል ጊዜ ሆነሽ?

ስድስት ዓመት ሆነኝ።

ከሀገር ቤት ከሕትመቱ ዓለም ከደራሲያኑ ውሎ የምትናፍቂው፣ አጣሁት የምትይው ነገር የለም ሩቅ እንደመኖርሽ?

ሀሬን በጣም ነው የምናፍቀው፣ ከደራሲያኑም ከድርሰቱም ውጪ የሕዝቡ ፈገግታ ፣ ከነድህነቱ፣ ኢትዮጵያዊ ሲለምንህ እንኳ ፈገግ ብሎ ነው። የዓመት በዓል ጊዜ ውል የሚልህ ቄጠማው፣ እጣኑ አለ። እኔ ጭንቅላቴ የሚያስበው በአማርኛ ነው። አሁንም ብትጠይቀኝ ማንኛውንም ነገር ተነስቼ ማሰብ የምችለው ከአዲስ አበባ ነው። እና ሀገሬን እናፍቃለሁ እወዳለሁ።

በእርግጥ የሀገር አንደኛ የለም። ሕይወትን ደግሞ በምርጫ ብቻ አትኖራትም። ግን ተገፍተህ እዚህ ጋር ትደርሳለህ። አላማርርም፤ ግን ሀገሬ ይናፍቀኛል።

አሁን የነገርሽኝ የሀገር ናፍቆትሽን ነው። ከደራሲያኑ ዓለምስ ምን ይናፍቅሻል?

አብሮ ማበድ፣ አብሮ መሳቅ መጫወት። አብሮ መፈላሰፍ። ጸሐፊ ስትሆን ከየትም አታመጣውም ኢኒስፓይሬሽን [መቀስቀስ] ይፈልጋል። መነሻህ ሁሌ አካባቢህ፣ ሕዝቡ፣ ኑሮህ ነው። ስለዚህ ሁሉም ይናፍቁኛል። እና ጓደኞቼም በጣም ይናፍቁኛል። አራት ኪሎ፣ ማለዳ ካፌ የኔ ካፌ ነበር የሚመስለኝ። ጠዋት ጠዋት አረፋፍጄ ሶስት ሰአት ተኩል ላይ ወጥቼ እዚያ ስቀመጥ ሁሉም ይመጣሉ።ጋዜጠኛው፣ ሰዓሊው፣ ደራሲው። አራት ኪሎ ማዕከል ነው። የአዲስ አበባ እርግብግቢቱ ማለት ነው። ስለዚህ በጣም ነው የምናፍቀው አራት ኪሎን። በዛ ላይ ሐያ ዓመት የኖርኩበት ነው። ብዙ ደራሲ፣ ጋዜጠኛ ቤቴ ይመጣል።

ለመጨረሻ ጊዜ የአማርኛ ድርሰት ያነበብሽው የማንን ነው?

እንዴ አሁንም አነባለሁ። አሁን ለምሳሌ የአለማየሁ ዋሴ እሸቴ መጽሐፍ፣ መርገምት አጠገቤ አለ። ከዚህ በፊት አንድ ስራቸውን አንብቤያለሁ። አነባለሁ። በተለይ ወጥ ስራዎች ከሆኑ።

ተያያዥ ርዕሶች