በፈረንጅ "ናይት ክለብ" ጉራግኛ ሲደለቅ

ዲጄ አሌክስ በ'ኤይልሃውስ'
አጭር የምስል መግለጫ ዲጄ አሌክስ በ'ኤይልሃውስ'

አንድ የሆነ የአውሮጳ ጉራንጉር ውስጥ፣ «አንድ-ሁለት» ለማለት፣ ወደ አንድ የሆነ መሸታ ቤት ጎራ ስትሉ፣ ለአመል እንኳ አንድ ሐበሻ በሌለበት አንድ የፈረንጅ ቡና ቤት፣ አንድ ቀጭን ዘለግ ያለ 'ፈረንጅ'፣ ከኢትዮጵያ ሙዚቃዎች አንዱን ከፍቶ፣ ትከሻውን ሲሰብቅና ሲያ'ሰብቅ ብታዩት ምን ይሰማችኋል? ለዚያውም የብዙዬን...

"ፎቅና መርቼዲስ ስሜት አይሰጡኝም፤

እኔ ፍቅር እንጂ ሐብት አያሞኘኝም፤

አያገባው ገብቶ ሰው ይዘባርቃል፤

እኔ ስሜን እንጂ ስሜቴን ማን ያውቃል..." የሚለውን...ወዝዋዥና ወስዋሽ ዜማ...።

ይህ ሰው አሌክሳንደር ባውማን ይባላል። 43 ዓመቱ ነው። ዲጄ ስለሆነ አሌክስ እያልን እናቆላምጠዋለን። በስዊዘርላንድ ዙሪክ ጎታርድ እና ከርን በሚባሉ የምሽት ክለቦች ውስጥ...የሙዚቃ ሸክላ 'ያቁላላል'፤ አቁላልቶ ለጆሮ ያጎርሳል፣ አጉርሶ አቅል ያስታል፤ የ60ዎቹን የኢትዮጵያን ሙዚቃ፤ የያ የወርቃማውን ዘመን።

አሌክስ እንኳን ኢትዮጵያ፣ አፍሪካንም ረግጦ ስለማወቁ እንጃ...። ቱኒዚያና ደቡብ አፍሪካ አንድ ሁለቴ ገባ ብዬ ወጥቻለሁ ያለኝ መሰለኝ። ከዚያ ውጭ 'ወላ ሃንቲ'።

አማርኛም ሆነ ኦሮምኛ፣ ትግርኛም ሆነ ጉራግኛ...ጆሮውን ቢቆርጡት አይሰማም። 'ወላ ሃባ...'

ኾኖም የትኞቹ የኢትዮጵያ ሸክላዎች በምን ቋንቋ ፤ በምን ዘመን፤ ከምን ባንድ ጋር እንደተቀነቀኑ ሲያስረዳ አገር ፍቅር ጓሮ ወይ እሪ በከንቱ ጀርባ ያደገ ነው የሚመስለው። የዘፋኞቻችንን ታሪክና የሙዚቃ አጀማመራቸውን ሳይቀር ለጉድ ይተነትናል...ለዚያውም ብ...ጥ...ር...ጥ..ር አድርጎ...።

የቢቢሲ ዘጋቢ አሌክስን ለመጀመርያ ጊዜ ያገኘው በስዊዘርላንድ፣ ዩኒቨርሲሻትስትራሰ 23 ጎዳና፤ ከታላቁ ዙሪክ ዩኒቨርስቲ ማዶ በሚገኘው «ልሀውስ» ውስጥ ነበር።

ባህልን በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ የቀመመው ሮፍናን

አውታር - አዲስ የሙዚቃ መሸጫ አማራጭ

«ልሃውስ» በዓለም ዙርያ የተጠመቁ እልፍ የቢራና የድራፍት መጠጦች የሚሸጡበት ዕውቅ መጠጥ ቤት ነው። ያን ምሽት እዚያ ግቢ ጓሮ ከድራፍቱ ፉት እያሉ እራታቸውን የሚመገቡ በርካታ ስዊሳዊያን ይታዩ ነበሩ።

ዲጄ አሌክስ ታዲያ ለታዳሚው የኢትዮጵያን የወርቃማውን ዘመን ሙዚቃዎች በሸክላ እያጫወተ ሲያምነሸንሻቸው አድሯል።

በዚያች ድንገተኛ ምሽት ያለቀጠሮ የተገናኙት አሌክስና የቢቢሲ ዘጋቢ "አንድ ሁለት" እያሉ ለአንድ ሰዓት ያህል ቆይተዋል። ወጋቸው በጥዑም ሙዚቃዎች ሲታጀብ የሚከተለውን መልክ ይይዛል።

"ፈረንጆች የኢትጵያን ሙዚቃ ሲሰሙ ጆሯቸው ግር ይለዋል"

ዲጄ አሌክስ ሳቂታና ተግባቢ ነው። ዲጄ ኾኖ ድሮስ ሊኮሳተር ያምረዋል እንዴ?!

ከፊትለፊቱ ሸክላ ማጫወቻ ጥንድ ምጣዶች አሉት። ጆሮው 'የከባድ መኪና ጎማ' በሚያካክሉ የአፍኖ- ማድመጫ (Head Phone) ተለብዷል።

ባተሌ ነው። አንድ የጋለ ምጣድ ላይ አንድ የሸክላ ድስት ጥዶ፣ሌላኛው ምጣድ ላይ በስሎ የሚንተከተክ ሸክላን ያወርዳል ። ፋታ ጠብቄ የእግዜር ሰላምታ ሰጠሁት።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ መሆኔን፣ ከባላገር መምጣቴን በትህትና ገልጬ ፍቃዱ ከሆነ በየሙዚቃ መሀል እንድናወጋ ብጠይቀው «ኽረ ምን ገዶኝ» አለኝ፤ በትከሻው፣ እንዲሁም በእንግሊዝ አፍ...።

ምን ዋጋ አለው ታዲያ! አይረጋም። ወጋችን ወግ ለመሆን ገና ወግ ሳይደርሰው ተስፈንጥሮ ይነሳል፤ ሌላ ሸክላ ይጥዳል። የሙዚቃ ባተሌ ነው ብያችሁ የለ!

'ኤይልሀውስ'መጠጥ ቤት በረንዳ ላይ ነው ያለነው። በዚያ ላይ 22፡00 ሰዓት ተኩል አልፏል'ኮ። ደግነቱ በአውሮፓ የበጋ ፀሐይ በጣም አምሽታ ነው የምትጠልቀው። ፀሐይዋ ራሱ ፀሐይ ሞቃ አትጠግብም መሰለኝ ለመጥለቅ ትለግማለች።

አሌክስ የሚያጫውተው ሙዚቃ ደግሞ ልብ ያሞቅ ነበር። ታዳሚ ፈረንጆቹም በግማሽ ግርታና በግማሽ ፍንደቃ ይሰሙታል። ጥላሁን- "ያም ሲያማ ያም ሲያማ ወገኔ ለኔ ብለህ ስማ" ይላል። ሰይፉ ዮሐንስ "የከርሞ ሰው" የሚለውን ልብ-ገዥ ሙዚቃው ያንቆረቁራል።

"አሌክስ! [መቼስ ዓለማየሁ ብልህ ነው የሚቀለው] በምን አጋጣሚ ይሆን ከኢትጵያ ሙዚቃ ጋር የተዋወቅከው?" አልኩት።

"First let me tell you a little bit about the music I am playing now…"ብሎ ጀመረና በእንግሊዝ አፍ የሚከተለውን አጭር ወግ ጠረቅን፤ ሙዚቃ አጅቦን።

"አሁን የምትሰማው የኦሮምኛ ሙዚቃ ነው፤ አሊ ሙሐመድ ቢራ ነው ዘፋኙ...እሱ የኦሮምኛ ሙዚቃ ንጉሥ ልትለው ትችላለህ...አስገራሚ ድምጽ ያለው ሰው ነው...።

"...እኔን በተመለከተ ምን ማወቅ ትፈልጋለህ ታዲያ? አሌክስ እባላለሁ፤ 43 ዓመቴ ነው፤ ጀርመናዊ ነኝ፤ የምኖረው ግን እዚህ ዙሪክ ነው። ከዓመት በፊት የጃማይካ ሙዚቃ አጫውት ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ታዲያ ምን ይሆንልሃል...የሒሩት በቀለን ሙዚቃ እሰማልኻለሁ..በድንገት..."

ሌላ ሸክላ ሊጥድ ተነሳ።

''አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው"

"በ 'ፍቅር እስከ መቃብር' ላይ ህይወት የዘራው አባቴ ነው"

የተቀመጥነው እሱ ሸክላዎቹን ከሚጥድበት የሙዚቃ ምድጃ በዐሥር እርምጃ ርቀት ነው። ያን ያደረገው እሱ ነው፤ ቃለምልልሳችን በመቅረጸ ድምጽ ሲቀረጽ እሱ የሚያጫውተው ሙዚቃ የኛን ድምጽ ውጦ እንዳያስቀረነው ስለሰጋ ነው። የድምጽ ሊቅ'ም አይደል?

አዲስ ሸክላ ጥዶ ሲመለስ ወጋችንን ካቆምንበት ቀጠልን...

"Now Playing is "ሰዮም ጋብራየስ" [ excuse my Amharic pronunciation] ።

[እረ ወላጅ እናቱም ከዚህ በተሻለ አትጠራውም] ልለው ፈልጌ እንግሊዝኛ አልሰበሰብልህ አለኝ...

"ስዩም ገብረየስ እንደ ጥላሁን ገሠሠና ዓለማየሁ እሸቴ ላቅ ያለ ዕውቅና ያለው ሞዛቂ እንዳልሆነ፤ የሠራቸው ሙዚቃዎችም በቁጥር ጥቂት እንደሆኑ አጫወተኝ።

"...እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ለኔ "ሰዮም ጋብራየስ" ታላቅ ሙዚቀኛ ነው።" ብሎ ንግግሩን አሳረገ።

"ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋር እንዴት እንደተዋወቅህ ጠይቄህ አልመለስክልኝም'ኮ...አሌክስ"

"Just a moment….ብሎ ሌላ ሸክላ ሊጥድ ተነሳ። ሸክላዎቹን መልክ አሲዞ ተመለሰ።

This song is by ቢሊኪኒህ ኡጋ!

What? Who?

ቢልኪኒህ ኡጋ…titled "AlKedaShim?" I do not think he is well known.

"What is his name again?" ስሙን እንዲደግምልኝ ተማጸንኩ።

ቢሊኪኒህ ኡጋ...

"Do you mean Workineh Yirga?"

No, no his name is ቢልኪንህ ኡጋ…He is very obscure singer አለኝ። የጠራው ስም የአገሬ አይመስልም፤ ብቻ 'ወርቅነህ ይርጋ፣ ወይ ብርቅነህ ይርጋ ወይ ቢልልኝ አጋ...' የሚባል ዘፋኝ መሆን አለበት እያልኩ፣ "ለማንኛውም ቀጥል..." አልኩት በጥቅሻና በእንግሊዝኛ።

በዚህ ጊዜ "አልከዳሽም" የሚለው ቢሊኪኒህ ኡጋ...የተባለውን ሰው ዘፈን ወጋችንን አጅቦት ነበር።

"መኖሬ ባንቺው ነው እስከመጨረሻ

ፈጽሞም አይክፋሽ የሕይወቴ ጋሻ

መኖሬ ባንቺው ነው እስከመጨረሻ

ፈጽሞም አይክፋሽ የኔ ሆደ ባሻ..." እያለ ያዜማል።

"ኢትዮጵያዊነቴን ያገኘሁት ሙዚቃ ውስጥ ነው" አቨቫ ደሴ

ድምፅ ፈታዮቹ መረዋዎች

እየተገባደደ ባለው ረዥም ሕይወቴ ሰምቼው የማውቀው ዘፈን አይደለም። ይሄ "ቢሊኪነህ ኡጋ" እያለ የሚጠራው ዘፋኝ ጥቂት ሙዚቃዎች ብቻ እንዳሉትና በዘመኑ ብዙም ገንኖ ያልወጣ እንደነበር፣ ነገር ግን ድንቅ ሙዚቀኛ እንደሆነ አብራራልኝ...።

ስሙ ግራ የሆነብኝ ይህ ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ማን ይሆን? ቢሊኪኒህ ኡጋ...ብሎ ስም!?

[ወደ ናይሮቢ የቢቢሲ ቢሮ ተመልሼ ይህንን ጽሑፍ ለሕትመት በማጠናቅርበት ወቅት የዚህን ዘፋኝ ከፊል የግጥሙን ክፍል ለጉግል አቀብዬ «አልከዳሽም» የሚል ሸክላ ያለው ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ማነው አልኩት። ጉግል ፈጥኖ መልስ ሰጠኝ፤ ለዚያውም በምሥል የተደገፈ...።]

...ብርቅነህ ውርጋ ይባላል፤ "ሄጃለሁ ገጠር" የሚል ርእስ ያለው አልበም ያለው፣ ከምድር ጦር ኦርኬስትራ ጋር የሞዘቀ ኢትዮጵያዊ ነው።አትሸኝዋትም ወይ' የሚልና "ገና ልጅ ናት ጋሜ" የሚሉ ሌሎች ሙዚቃዎቸም አሉት። ስለ አገሬ ሞዛቂ አንድ ፈረንጅ የሚያውቀውን ያህል ባለማወቄ ሀፍረት ቢጤ አልሸበበኝም አልልም መቼስ።]

Image copyright Alexander Baumann
አጭር የምስል መግለጫ አሌክሳንደር ከጣሊያናዊ ሸሪኩ ጋር በመሆን 'ኦዲዮአበባ" የተሰኘ የዲጄ ግብረኃየል መሥርቷል

በፈረንጅ የምሽት ክበብ ውስጥ ጉራጊኛ

ዲጄ አሌክስ ስለ ብርቅነህ ውርጋ አውርቶ አይጠግብም።

"ይገርመሀል እዚህ ዙሪክ ውስጥ የምሽት ክለቦች የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን አጫውታለሁ። «አልከዳሽምን" ከከፈትኩ ግን የዳንስ ወለሉ በሰው ይጥለቀለቃል። He always rocks the dance floor. He is my dance floor filler…አለኝ።

አሌክስዬ...የምትለውን ዘፋኝ ብዙ ኢትጵያዊያን የሚያውቁት አይመስለኝም፤ እኔንም ጨምሮ..

"እኔ ስለ ኢትዮጵያዊያን ምርጫ ብዙም አላውቅ ይሆናል፤ ልነገርህ የምችለው ግን እኔ በማጫውትበት ክለብ ውስጥ ስላሉ የውጭ አገር አድማጮች ነው...።

ዲጄ አሌክስ ይህን ብሎኝ እብስ ብሎ ተነሳ...ሸክላ አውርዶ ሸክላ ሊጥድ...

"ማነው ደግሞ አሁን የሚጫወተው?"

አስናቀ ገብረየስን አታውቀውም? [በአርግጠኝነት እየታዘበኝ ነው፤ "ድንቄም ጋዜጠኛ!" የሚል ይመስላል...]

"...ሙዚቃው የተቀረጸው ካልተሳሳትኩ 1988 ሲሆን በካሴት ነበር መጀመርያ የወጣው። እኔ ሸከላውን ያገኘሁት ከአንድ ዓመት በፊት ነው። ይመስለኛል ፈረንሳይ ያለ አንድ ሰው ነው በሸክላ ያሳተመው፤ በቅርቡ።

"እኔምልህ አሌክስ...!ከየት ነው እነዚህን ሸክላዎች ግን የምትለቃቅማቸው። ቅድም ስጠይቅህ ኢትዮጵያ ሄጄ አላውቅም አላልከኝም እንዴ?"

"ሸክላ መሰብሰብ የጀመርኩት ከ15 ዓመቴ ጀምሮ ነው። እንደው ለየት ብሎ ለመታየት አይደለም የምሰበስባቸው። ሙዚቃ ለማጫወት ሌላ ምንም የተሻለ መንገድ ስለማይታየኝ ነው። ለእንደኔ ዓይነቱ የሙዚቃ አጫዋች ሸከላ በብዙ መንገድ የላቀ ነው። ሸክላን ስትዳስሰው ሁሉ ልዩ ስሜት'ኮ ነው የሚሰጠው...።

"ታውቃለህ አይደል ግን አሌክስ...'ከኢትጵያ ሙዚቃ ጋር እንዴት ተዋወቅክ' ብዬህ እስካሁን አልመለስክልኝም..."

የሰይፉ ዮሐንስ «ኤቦላላ ላላ... ኤቦ ላላ» እያጀበን ያነሳሁለት ጥያቄ ነበር።

"ምን መሰለህ፤ ላለፉት ሁለት ዐሥርታት ማለት ይቻላል የጃማይካን ሙዚቃ አጫውት ነበር። በአጋጣሚ በሙዚቃዎች መሀል የኢትዮጵያን ሙዚቃ ሰማሁ። ከዚያ ለረዥም ጊዜ አልተመለስኩበትም። ባለፈው ዓመት የሒሩት በቀለን ዘፈን ስሰማ ተቀሰቀሰብኝ።..."

"ምኑ?"

"ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ያለኝ ስሜት ነዋ!"

"ለመጀመርያ ጊዜ የኢትጵያ ሙዚቃ ስትሰማ ግን ቶሎ ተዋኸደህ?"

"እውነት ለመናገር የመጀመርያው ስሜቴ እንደዚያ አልነበረም። እንደሰማሁት ውድድ አደረገኩት ልልህ አልችልም። ይልቅ ግር ነው ያለኝ። 'ይሄ ደግሞ እንዴት ያለ እንግዳ ዜማ ነው' እንድል ነበር ያደረገኝ።..."

"እውነትህን ነው?"

"አዎ! ነገር ግን እንደ ሙዚቃ አጫዋች አንድ ሙዚቃ ሰምተህ 'በቃ ይሄ ለኔ የሚሆን አይደለም' አትልም። ደግመህ ደጋግመህ ትሰመዋለህ። ይህንኑ አደረኩ። በዚህ ጊዜ ልዩ ፍቅር ውስጥ ወደቅኩ። የሆነ ሰሞን እንዲያውም በሙዚቃችሁ ታመምኩ።( I was struck with Ethio-fever) [በፍላጻው ተወጋሁ፤ የሙዚቃችሁ መብረቅ መታኝ እንደማለት] ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሸክላ ማሳደድ ጀምርኩ።

ሌላ ሸክላ ጥዶ ተመለሰ...

ተፈራ ነጋሽ፡ "በነገራችን ላይ ሙዚቃ አልተውኩም"

የኤርትራ ዘፈኖች በኢትዮጵያዊ አቀናባሪ

"የምትሰማው አሕመድ አብደላን ነው። ኦሮምኛ ነው የሚያዜመው። ይሄንንም ዘፋኝ ብዙ ሰው ያውቀዋል የሚል ግምት የለኝም። አሊ ሸቦን ታውቀዋለህ? እንዴት ግሩም የኦሮምኛ አቀንቃኝ መሰለህ..."

"እኔ ምልህ! ሙዚቃችን ግን ለምን እንደ ማሊ ሙዚቃ ዓለምን ማስደመም ሳይችል ቀረ? እንደው በአጠቃላይ ተስፋ ያለው ይመስልኻል?"

"...ይህን እኔ ለመናገር ይከብደኛል። ሆኖም አቅም የለውም አልልህም። በኢቶፒክስ እና በሙላቱ አስታጥቄ ወደ ዓለም መድረክ የቀረበ ይመስለኛል። ሙላቱ'ኮ እዚህ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ገናና ሰው ነው። የወርቃማ ዘመኑ...ሙዚቃችሁም ትልቅ አቅም አለው።

"የአሁን ሙዚቃችንን ትሰማለህ?"

"ብዙም አይደለም።"

"ለምሳሌ ሮፍናንን ታውቀዋለህ?"

"ማነው ደሞ እሱ?"

"የአዲሱ ትውልድ ድምጽ ነው። ዝነኛ'ኮ ነው።"

"...ይቅርታ እንደነገርኩህ የአሁን ዘመን ከሆነ አላውቅም። ከአሁኖቹ ስሙን የማውቀው ቴዲ አፍሮን ብቻ ነው። ስለዚህ ዘመን ሙዚቃ ለማውራት እኔ ትክክለኛው ነኝ ብዬ አላስብም።"

"ለምንድነው የአሁኖቹን እንዲህ ገሸሽ ያደረካቸው ግን?"

"በጥቅሉ ጆሮ ገብ አይደሉማ። ሁለተኛ 'ሲንተቲክ' ነው። ተፈጥሯዊ ወዝ የላቸውም፤ ይሄ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን አዘውትሬ ለማጫውተው ለጀማይካም ሙዚቃም፣ ለተቀረውም ዓለም ሙዚቃም ያለኝ ስሜት ነው።"

"እንዴት ነው ግን በወርቃማው ዘመን በኢትጵያ ዝነኛ የነበሩትንና ያልነበሩትን የምታውቀው?እና ደግሞ እስኪ የድሮ ሸክላዎችን እንዴት እንደምትሰበስባቸው በዚያው ንገረኝ..."

"ሸክላ በሁለት መንገድ አገኛለሁ። አንዱ በኦንላይን ኢቤይ ላይ እገዛለሁ። በዋናነት ግን ሁለት ሁነኛ ሰዎች አሉኝ፤ ሁለቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። የምፈልገውን ሙዚቃ ያውቃሉ። ሸክላ ከየትም አፈላልገው ገዝተው ይልኩልኛል።አሁን ከመቶ በላይ የኢትዮጵያ ሸክለዎች አሉኝ..."

"ስንት ያስወጣል አንዱ ሸክላ?"

"በአማካይ 20 ዶላር ይሆናል። ነገር ግን ብርቅዬ የድሮ ሸክላዎች ደግሞ አሉ፤እነሱ ውድ ናቸው። ለምሳሌ የሙላቱን አታገኘውም። በጥሩ ይዞታ ላይ ያሉ የኢትዮጵያ ሸክላዎች እስከ ሁለት መቶ ዶላር ያስወጡኛል።"

"...እንደነገርኩህ...አሁን የምትሰማው የኦሮምኛ ዜማ ነው፤ አሕመድ አብደላ ይባላል..."

"...ትናንትና ማታ እዚህ ዙሪክ ምሽት ክበብ ውስጥ ይሄን አሁን የምትሰማውን ሙዚቃ ጨምሮ ሌሎችንም የወርቃማ ዘመን ሙዚቃዎች ሳጫውተው ነበር። አንዳንድ 'ፈረንጆች' ወደኔ የዲጄ አትሮንስ እየቀረቡ "ለመሆኑ ይሄ የምታጫውተው ሙዚቃ ከየት አገር ነው? ቋንቋውስ ምንድነው?" ይሉኝ ነበር። ለጆሯቸው እንግዳ ስለሆነ መሰለኝ። "I told them it's Oromo, it's Tigre, it's Amharic…it's Gurage' it's Ethiopia"

"ሙዚቃችን ግራ አጋቢ ነው ማለት ነው?"

"...ግራ የሚገባቸው ለምን መሰለህ...አንደኛ የአሁን ዘመን ሙዚቃ (contemporary) አይደለም። የ60ዎቹና የ70ዎቹ ነው። ሁለተኛ ከለመዱት የሙዚቃ ቃና እጅግ ያፈነገጠ ነው...የሚጎረብጣቸው እንዳሉ ሁሉ እጅግ አድርገው የሚወዱትም ብዙ ናቸው። የዚያ ዘመን ሙዚቃችሁ ውብ ነው፤ ዘርፈ ብዙ ቅኝቶች አሉት፤ ጃዝ አለው፣ ፋንክና ሶል አሉት፤ ከዚያ ባሕላዊ ሙዚቃዎቻችሁ ሌላ መልክ አላቸው። ያፈነገጡ ሆነው ደስ የሚሉ ናቸው፤ የኦሮምኛ ሙዚቃ ከትግርኛ ፍጹም የተለየ ነው። ትግርኛ ከጉራጊኛውም እንዲሁ..."

"ክለብ ውስጥ ሙዚቃዎቻችንን ስታጫውት እንደው ድንገት እግር የጣለው ኢትዮጵያዊ ሰምቶህ ጉድ ያበት ጊዜ የለም?"

"እምብዛምም አላጋጠመኝም...! ግን አንዴ የማልረሳው ሌሎች እንግዶች እየተዝናኑ አንድ ኢትዮጵያዊ እንባው እየወረደ አየሁ። ወደኔ ተጠግቶ በማጫውተው አንድ ሙዚቃ እጅግ ልቡ መነካቱን ነገረኝ።"

"ሙዚቃውን ታስታውሰዋለህ?"

"ማሕሙድ አሕመድ ነው... 'it's called 'Anwodim Tikatin' [አንወድም ጥቃትን!]

"በነገርህ ላይ ማሙድ ለፌስቲቫሉ እዚህ ዙሪክ ነው ያለው፤ሰምተኻል? ለመሆኑ የድሮዎቹን ሙዚቀኞን አግኝተኻቸው ታውቃለህ?"

"አዎ ማሕሙድ እዚህ መሆኑን ሰምቻለሁ። ሙላቱ አስታጥቄን አግኝቼው አውቃለሁ። ...

"በዚህ ዓመት እዚህ ዙሪክ ኮንሰርት ነበረው። ለአጭር ደቂቃ እንደምንም ብዬ አገኘሁት። ተዋወቅኩት። ተግባቢና ቀና ሰው ነው። ከመድረክ ጀርባ ሄጄ ነበር ያገኘሁት። እሱን በማግኘቴ ምን ያህል እድለኛ ሰው እንደሆንኩ ነገርኩት። የሱን ድ...ሮ የሠራቸውን 45 ሙዚቃዎች ያሉበትን ሸክላ ከነሽፋኑ አሳይቼው ፈርምልኝ አልኩትና እሱ ላይ ፈረመልኝ። በቃ ምን ልበልህ ደ...ስ አለኝ። "

አጭር የምስል መግለጫ የዲጄ አሌክስ የምንጊዜም ምርጥ 5 የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች በምሥሉ የሚታዩት ናቸው

"ወደፊት ታዲያ ምን አሰብክ? ደግሞ አሌክስ...አዲስ አበባማ መሄድ አለብህ...ይሄን ሁሉ ሙዚቃ እያጫወትክ 'ኢትጵያ ሄጄ አላውቅም' ስትል ትንሽ ይከብዳል..."

"እውነትህን ነው። አሁን የዲጄ ግብረኃይል አለኝ። «አውዲዮአበባ» የሚባል። በቡድኑ ውስጥ እኔና አንድ ጣሊያናዊ ጓደኛዬ ነን ያለነው። ቶሚ ይባላል። እሱም ሙዚቃችሁን እንጂ ኢትዮጵያን ፈጽሞ አያውቅም። ሁለታችንም ምን እያሰብን መሰለህ? በይበልጥ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለአውሮጳዊያን ለማስተዋወቅ ዕቅድ አለን።..."

"...ኢትዮጵያ አትሄድም ወይ ላልከው...፤ እንደነገርኩህ ኢትዮጵያን የማውቃት በሙዚቃ ነው፤ ኢትዮጵያ አለመሄዴም ያሳፍረኛል። በዚህ ዓመት መጨረሻ ከቶሚ ጋር አዲስ አበባ ለመሄድ እያሰብኩ ነው። ምን ትላለህ?"

"ይቅናህ! ሌላ ምን እላለሁ...! ይቅናህ አሌክስ..ይቅናህ!"

ተያያዥ ርዕሶች