የአረና ፓርቲ አባል ንብረት የሆኑ 13 ፍየሎች መታሰራቸው ተነገረ

የፓርቲ አባል ንብረት የሆኑ 13 ፍየሎች መታሰራቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, SIMON MAINA

የምስሉ መግለጫ,

ፎቶ፡ GettyImages

ከሰሞኑ ባለቤትነታቸው የአረና ትግራይ ፓርቲ አባል ናቸው የተባሉ አስራ ስድስት ፍየሎች የመታሰራቸው ዜና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

የአረና ፓርቲ ሊቀመንብር አቶ አብርሃ ደስታ በላፈው ረቡዕ የፓርቲው አባል ንብረት የሆኑ 16 ፍየሎች በትግራይ ክልል ቆላ ተምቤን ወረዳ ንኡስ ወረዳ ወርቅ አንባ ቀይሕ ተኽሊ ቀበሌ ውስጥ መታሰራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የፍየሎቹ ባለቤት የሆኑት አቶ ዜናዊ አስመላሽ 16 ፍየሎቻቸው ታስረውባቸው እንደነበረ ተናግረው፤ ታስረው ከነበሩት ፍየሎች ሶስቱ አምልጠው ወደ ቤት መመለሳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአረና ፓርቲ ሊቀመንበሩ አቶ አብረሃ፤ አቶ ዜናዊ አስመላሽ የአረና ፓርቲ አባልና የተንቤን አካባቢ አስተባባሪ መሆናቸውን ይናገራሉ። አቶ ዜናዊ አስመላሽ ከዚህ ቀደም ለእስር ተዳርገው እንደነበረ እና በተደጋጋሚ የግድያ ዛቻዎችን ይደርስባቸው እንደነበረ አቶ አብረሃ ያስረዳሉ።

አቶ ዜናዊ ፍየሎቻቸው የታሰሩባቸው የአረና ፓርቲ አባል በመሆናቸው መሆኑን ይናገራሉ። አቶ ዜናዊ እንደሚሉት ከሆነ ፍየሎቻቸው ለእስር ከመዳረጋቸውም በላይ በእርሳቸው ላይ ተደጋጋሚ የሆነ የግድያ ማስፈራሪያዎች እንደሚደርሳቸው አምርረው ይናገራሉ።

ፍየሎቹ ዕሮብ እለት ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአንድ ሰው ተነድተው በአከባቢው በሚገኝ ሚሊሻ ቤት ውስጥ እንደታሰሩ ከሰው መስማታቸውን አቶ ዜናዊ ይናገራሉ።

አቶ አብረሃም ፍየሎቹ የተወሰዱት ወደ የሚሊሻ አዛዡ ቤት ስለመሆኑ መረጃ አለኝ ይላሉ።

አቶ ዜናዊ 'ፍየሎቼ ተወስደውብኛል' በማለት ለፖሊስ አቤቱታ ቢያቀርቡም 'ከአረና አባልነትህ መውጣት አለብህ ካልሆነ ፍየሎቹ አይሰጡህም' የሚል ምላሽ ከፖሊስ እንደተሰጣቸው አቶ አብርሃ ይናገራሉ።

አቶ ዜናዊ በበኩላቸው ፍየሎቹ እንዲመለሱላቸው ለፖሊስ አቤቱታ ሲያቀርቡ 'በፌስቡክ ሄደህ እንዳስወረኀው መፍትሄውን እዛው ፈልግ' እንደተባሉ እና አሁን ላይ ግራ ተጋብተው ያለ መፍትሄ ተቀምጠው እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አብረሃ እንደሚሉት ከሆነ በፓርቲው አባላት ላይ እንደዚህ አይነት በደል ሲፈፀም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከዚህ ቀደምም የአንድ የአረና ፓርቲ አባል ንብረት የሆኑ ሁለት ላሞች በጥይት መገደላቸውን ያስታውሳሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ክብሮም የተባለ የፓርቲው አባል፤ ንብረቱ የሆኑ የቤት እንስሳቶች ተወስደው ታስረውበት እንደነበረ ይናገራሉ። ግለሰቦቹ ወደ ፖሊስ ሲያመለክቱም 'አረናን ተው' የሚል ማስጠንቀቂያዎች ይቀርቡላቸዋል ሲሉ አቶ አብረሃ ያስረዳሉ።

ለድርጊቱ የህወሃት አመራሮችን ተጠያቂ የሚያደርጉት አቶ አብረሃ፤ "ውሳኔው ከህውሃት አንሚመጣ እናውቃለን" ይላሉ። አቶ አብረሃ በአከባቢው አመራሮች ላይ ክስ እንደሚመሰርቱ ጨምረው ተናግረዋል።

ረዳት ኢንስፔክተር ፍሰሃ አብረሃ የቆላ ተንቤን ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ናቸው። ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት ረዳት ኢንስፔክተር ፍሰሃ "በአካል ካልመጣችሁ መነጋገር አንችልም" በማለት መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በጉዳዩን ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ትግራይ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እና ለህውሃት ፓርቲው ቃል አቀባይ ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ስልካቸውን በለማንሳታቸው አልተሳካልንም።