ኢትዮጵያ፡ የግብረ ገብ ትምህርት ለምን ያስፈልገናል?

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እና ዶ/ር መስከረም ለቺሳ Image copyright Office of the Prime Minister/ Meskerem

በቅርቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያስነሱና ሲያከራክሩ የነበሩ ምክረ ሃሳቦችን ይዞ በወጣው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ በዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ቆይታ ግብረ ገብ፣ ክሪቲካል ቲንኪንግ፣ ኢንተርፕርነርሽፕ፣ .... እና ሌሎችም የትምህርት ዓይነቶች እንዲሰጡ በምክረ ሃሳብ ደረጃ ቀርቧል።

እነዚህ የትምህርት ዓይነቶች ሊሰጡ መታሰባቸውን በበጎነት ያነሱት እንዳሉ ሁሉ የትምህርት ዓይነት ከማብዛት ውጭ ፋይዳ የላቸውም ሲሉ የኮነኑትም አሉ። ማን ነው የሚሰጣቸው? በምን ያህል ጥልቀት ነው የሚሰጠው? ለምን ያህል ጊዜ ነው መሰጠት ያለባቸው? ከየት ነው መጀመር ያለበት? የሚሉትም በጉዳዩ ላይ ከተነሱ መሠረታዊ ጥያቄዎች ውስጥ ይገኙበታል።

በትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታው ሊሰጡ ከታሰቡ የትምህርት ዓይነቶች አንዱ ደግሞ ባለፉት ዘመናት ሲሰጥ የነበረው የግብረ ገብ ትምህርት ነው።

ሥነ-ምግባር የተላበሱ ሮቦቶች

ወላጆች ለልጆቻቸው የሚመኟቸው ኢትዮጵያዊ መምህር

'The role of civic and Ethical education in democratization process of Ethiopia: challenge and prospects'በሚል በዘንድሮው ዓመት የታተመ ጆርናል እንደሚያስረዳው የሥነ ምግባር ትምህርት 'የሞራል ትምህርት' በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ተካቶ መሰጠት የጀመረው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነው።

ፅሁፉ ላይ እንደተጠቀሰው በወቅቱ የነበረው የሞራል ትምህርት ዓላማ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያን ኃይማኖት ሥርዓትን መሠረት በማድረግ በሥነ ምግባር የታነፁ ትውልዶችን መፍጠር ነበር። ንጉሱን የሚያከብሩ፣ የሚያገለግሉ 'ፈሪሃ እግዚሃብሔር' ያደረባቸው ተማሪዎችን ለማውጣትም የሚያንፅ እንጅ የዲሞክራሲ ሥርዓት ላይ ትኩረት ያደረገ እንዳልነበር በጥናቱ ላይ ተወስቷል።

ከዚያም የደርግ መንግሥት በ1966 ዓ.ም ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የማርክሲስት - ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም ሥር የተለያዩ ፖሊሲዎች ተቀርፀው በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ተካተው ይሰጡ ነበር።

በዘመኑ 'የፖለቲካ ትምህርት' በሚል ይሰጥ የነበረው የትምህርት ዓይነት የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለምን የማስረፅ ዓላማ ነበረው ይላል- ጥናቱ።

ጥናቱ ይሰጡ በነበሩት የትምህርት ዓይነቶች ውስጥም ሰብዓዊ መብት፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ነፃነት የመሳሰሉ ሃሳቦች የተካተቱበት እንዳልነበር በመግለፅ በሁለቱም መንግሥታት የነበረው የሥነ ምግባር ትምህርት የርዕዮተ ዓለም ትምህርት እንጂ ዲሞክራሲያዊ የሆኑ የሥነ ምግባር ትምህርት አልነበሩም ሲል ያትታል።

ከዚያ በኋላ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላም 'የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት' በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ተካቶ እየተሰጠ ይገኛል።

ይሁን እንጂ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ተማሪዎችን በሥነ ምግባር በማነፅ ረገድ ውጤታማ እንዳልሆነ ጥናቱ ከነ ምክንያቶቹ ነቅሶ ያሳያል።

የዲሞክራሲ በተግባር አለመኖር፣ የባለሙያዎች እጥረት፣ ለትምህርቱ ያለው አመለካከት፣ የትምህርቱ ይዘት እና ሌሎች ተግዳሮቶች ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው።

በመሆኑም ይህም እንደ ቀደመው ዘመን ርዕዮተ ዓለምን የማስረፅ እንጅ ተማሪዎችን በሥነ ምግባርና በሞራል አንፆ ማውጣት የሚያስችል አይደለም የሚል ትችት የሚስተናገድበት ሆኗል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋም የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት[ሲቪክ ኤዱኬሽን] ትምህርት መልካም ቢሆንም ግብረ ገብነትን ሊተካው አይችልም ሲሉ ከሚሟገቱት አንዱ ናቸው።

"የግብረ ገብ ትምህርት ድሮ ልጅ እያለን ከሁለተኛ ክፍል ወይም ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ እንማር ነበር ፤ በመሆኑም ተመልሶ መሰጠት አለበት " ሲሉ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ላይ ቀረበውን ምክረ ሃሳብ ይደግፉታል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ክሪቲካል ቲንኪንግ እና ሌሎችም የትምህርት ዓይነቶች መካተታቸው ጥሩ ነው የሚል አቋም አላቸው። "የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታው በጎ በጎ ነገሮች ተካተውበታል" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ሥነ ባህሪ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር መስከረም ለቺሳም በሃሳቡ ላይ ተቃውሞ የላቸውም።

ነገር ግን ግብረ ገብ በትምህርት ቤት ውስጥም ሆነ በከፍተኛ ተቋም ውስጥ በየትምህርት ዓይነቶቹ ውስጥ ገብቶ፣ አኗኗራችንም ውስጥ የሚገለፅ እየሆነ መሰጠት አለበት የሚል አቋም አላቸው። ግቡን እንዲመታም ከተለያየ አቅጣጫ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት ይመክራሉ።

የግብረ ገብነት ትምህርት ለምን አስፈለገ?

"አሁን ያለነው ባቢሎን ውስጥ እኮ ነው፤ በጎና እኩይ የሆነን ነገር መለየት አቅቶናል" የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው የግብረ ገብ ትምህርት እንደገና መተዋወቅ እንደነበረበት በማንሳት በምክረ ሃሳቡ መቅረቡን በጥሩ መልኩ ይመለከቱታል።

"የተበላሸው ተበላሽቷል፤ ነገር ግን ከሥር ጀምሮ እንደ አዲስ መማር አለባቸው፤ ሥነ ምግባር ወሳኝ ነው፤ ለአንድ ማህበረሰብ ሕልውናም መሰረት ነው" ሲሉ ምክንያታቸውን ያስረዳሉ።

ዶ/ር መስከረምም ይህንን የትምህርት ዓይነት መልሶ ለመስጠት የታሰበው በሥነ ምግባር ያለውን ክፍተት የሚሞላ ስላጣን ነው ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ክፍተቶቹ በባህል መላላት፣ በሥርዓተ ትምህርቱ አጥጋቢ አለመሆን፣ በማህበራዊ ትስስር መበጣጠስ፣ ሉላዊነት እና ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖዎች አማካኝነት የሚፈጠሩ ናቸው።

ይህም ብቻ ሳይሆን ራስን ማወቅ፣ አዎንታዊ አስተሳሰብ አለመልመድ፤ በዚያኛው በኩል ግፊት ሲመጣ የሚቋቋሙበት ብቃት እና እውቀት አለመኖሩን እንደ ተጨማሪ ምክንያት ያስቀምጡታል።

የባህል፣ የኃይማኖት፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የፆታ እኩልነትን ማክበር አለባችሁ እየተባለ በሚደረገው ውትወታ ብቻ ግብረ ገብነት ሊጎለብት ይችላል የሚል እምነት የላቸውም።

ይህንን ንግግር በመርህ ደረጃ ሁሉም ሰው ያውቀዋል የሚል ሃሳብ ያላቸው ዶ/ር መስከረም በተግባር ይህንን ለማድረግ የሚያስችል አኗኗር ውስጥ ነን ወይ? የሚለው ላይ ግን ጥያቄ አላቸው።

ዶ/ር መስከረም በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ይሰጥ የነበረውን የግብረ ገብ ትምህርት መለስ ብለው ያስታውሳሉ። በወቅቱ ይሰጥ የነበረው ትምህርት ይሞላ የነበረው ክፍተት ትንሽ ነው ይላሉ።

ምክንያቱም ግብረ ገብነት በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ የሙያ ሥነ ምግባር ሆኖ በመቀመጡ የእያንዳንዱን ሙያ ሥነ ምግባር በደንብ ይማሩት ስለነበር ነው።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የፖለቲካ ጥያቄ እንዴት ይመለስ?

"አባቴ በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ነው የተማረው፤ ለአለባበሳቸው እንኳን ትኩረት ይሰጣል። ማሽን ክፍል ውስጥ ሲገቡ ምን መልበስ እና እንዴት መልበስ እንዳለባቸው፣ ራሳቸውንና ሰውነታቸውን እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው፣ የሚፅፉበት ደብተር፤ የእጅ ፅሁፋቸው በጣም ጥንቃቄ ያደርጉ እንደነበር ነግሮኛል" ይላሉ።

ቅልጥፍናቸው፣ ታዛዥነታቸው፣ አመጋገባቸውን፣ ሁሉንም ሥነ ምግባር ይማሩ ነበር። የዚያን ትምህርት ነፀብራቅም በአባታቸው ላይ መታዘብ እንደቻሉ ያስረዳሉ።

"የማንኛውም ትምህርት ዓላማ ወደ ሥነ ምግባራዊ አስተሳሰብ ማምጣት ነው" በማለት የአንዳንድ ፈላስፋዎችን ንግግር የሚያጣቅሱት ዶ/ር መስከረም አሁን ላይ ያለው የትምህርት ሥርዓት ወደዚህ አቅጣጫ እየመራን ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ውስጥ ነው ሲሉ ያክላሉ።

በሌላው ዘርፍ የጎደለውን በአንድ ትምህርት ለማካካስ መሞከር የበለጠ ክፍተቱን ሊያሰፋው ይችላል የሚል ስጋትም አላቸው።

ዶ/ር ዳኛቸው በበኩላቸው በየትምህርት ዓይነቱ የሚሰጡት የሥነ ምግባር ትምህርቶች ከግብረ ገብነት ተመዘው የወጡ ናቸው፤ በመሆኑም ዋናው ግንድ መኖር አለበት ሲሉ ይሟገታሉ።

በመሆኑም መሠረታዊ የሆነው ግብረ ገባዊ አስተምሮት ያስፈልጋል የሚል ፅኑ አቋም አላቸው።

"ልጆቻችንን በሞራል ማነፅ አለብን" የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው "በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ፤ ሰው ነው ወሳኙ፤ የበጎና የመጥፎ ነገር ዓለም አቀፋዊ የሆነ መለኪያ የለም የሚለው መሻር አለበት" ይላሉ -ዶ/ር ዳኛቸው።

በቀደመው ሥርዓት የግብረ ገብ ትምህርት መኖሩ በጣም በጎ አስተዋፅኦ እንዳሳረፈም ሳይጠቅሱ አላለፉም። አንድ ሃገርና ማህበረሰብ ያለ ግብረ ገብና ሞራል እሴት ሊኖር እንደማይችል ያስረዳሉ።

በመሆኑም ይህ እሴት ከልጅነት ጀምሮ መሰጠት እንዳለበት፣ የግብረ ገባዊ ጥያቄዎችን እያነሱ መለማማድ እንዳለባቸው፣ ፍትሃዊነትን ከሥር ከሥር መማር እንዳለባቸው ይመክራሉ።

ግብረ ገብነትን በመደበኛ ትምህርት መላበስ ይቻላል?

ምንም እንኳን ግብረ ገብነትን የሚያላብሱ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በመደበኛ ትምህርት ውስጥ ተካቶ መሰጠት እንዳለበት ዶ/ር ዳኛቸው የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።

ዶ/ር መስከረምም ቤተሰብ ያላስተካከለውን ትምህርት ቤት የማነፅ ኃላፊነት እንዳለበት ያሰምሩበታል።

አንዳንዴ ከቤተሰብ አቅም በላይ የሆኑ ነገሮች ይኖራሉ የሚሉት ዶ/ር መስከረም የተጣመመውን ለማስተካከል ትምህርት ቤቶች ሁለተኛ እድል ይሰጣሉ ይላሉ። የመምህራን ተነሳሽነት፣ በቂ ሥልጠና፣ በቂ ዝግጅት፣ ብልሃቱና ባህሉም ስለሌለ እንጂ በትምህርት ቤት ጥሩ ዘር መዝራት ይቻላል ባይ ናቸው።

"ተሞክሮ አልወሰድንም፤ ግድ የለሾች ሆነናል፤ ትኩረታችን ገንዘብ፣ ፖለቲካ፣ ብሔር ላይ ነው ይህን ማን ይስራ? ይህ ነው ክፍተቱ" ሲሉም ተግዳሮቱን ይነቅሳሉ።

የአሁኑ ትውልድ ምን ጎድሎታል?

ዶ/ር መስከረም ጎዶሎ ስለመኖሩ ጥርጣሬ የላቸውም። ነገር ግን የአሁኑ ትውልድ ብቻ ነው ወይስ የቀደመው? ሲሉ በመጠየቅ በዚህ ትውልድ ብቻ ጣታቸውን መቀሰር አይፈልጉም።

"የተሳሳተ መስመር ላይ የቆመ ትውልድ፤ ተከታዩም የተሳሳተ መስመር ላይ ቆሞ ይገኛል፤ እናም የዚህ ትውልድ ሞግዚት ማን ነበር? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል" ይላሉ።

በእርግጥ በዚህ ትውልድ ላይ በአለባበስ፣ በአነጋጋር ፣ ለሰው ስሜት አለመጠንቀቅ መታየቱን ባይክዱም ተስፋ ግን ያደርጋሉ - ተንከባሎ የመጣ ብዙ ሸክም ያለበት ትውልድ በመሆኑ የሚያይዋቸው የግብረ ገብነት ችግር ከዚህም ብሶ አለማየታቸውን በማድነቅ።

እዚህም ላይ የአባታቸውን ተሞክሮ ይመዛሉ።

"የግብረ ገብ አስተሳሰቡ ከብዙ ነገር የተቃኘ ነው፤ ከባህሉ ውስጥ ያሉትን ጥሩ ነገሮች ከራሱ ጋር አዋህዶታል። ትምህርት ቤት ሲገባ መምህር ሲያስተምር፤ ጃንሆይ መጥተው ሲጎበኙ፤ ትምህርት ቤቱን እንደ ቀላል አያየውም፤ ትልቅ ኢንቨስትመንት እየተደረገብኝ ነው ብሎ ያስባል" በማለት አሁንም ድረስ የዘለቀ ትዝብታቸውን ያጋራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት አባታቸው የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወድቆ የደርግ ዘመንም ሲመጣም ጥሩ ነገር እንዳለ ለማየት ይችሉ ነበር። የፆታ እኩልነት፣ የሥነ ምግባሩ፣ የሥራ ባህሉ ፣ አንድ ሰው ብዙ መስራት እንዳለበት እንዲሁም ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡ ማሰብ እንዳለበት ያምናሉ።

በመሆኑም ቤተሰብም፣ ሁለቱም መንግሥታት በአንፃራዊ መልኩ ስለ ሃገር የሚያስቡበትና የሚቆረቆሩበት ትውልዶች በነበሩት ወቅት በመሆኑ፤ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚወራውና ውጭ ላይ ያለው የተስማማላቸው እንደነበር ይናገራሉ።

"አሁንም ድረስ በሚሰራው ሥራ ከፍተኛ ገንዘብ በማስከፈል አያምንም፤ ምክንያቱም ኅብረተሰቡ ድሃ ነው፤ የሚመጥነውን ዋጋ ነው የማስከፍለው የሚል አቋም አለኝ ይላል። ይህም መሰረት እንዳለው አንዱ ማሳያ ነው።" ይላሉ- ዶ/ር መስከረም።

በመሆኑም ግብረ ገብነት ከሁሉም አቅጣጫ ነው መሰጠት ያለበት፤ የትምህርት ቤት ብቻ ሸክም መሆን የለበትም ሲሉ ያስረግጣሉ።

1550 ተማሪዎች ለኩረጃ ሲሉ ስማቸውን ለውጠዋል

" ይህ ትውልድ መሪ የለውም፤ የሚጨነቅለት የለውም፤ የኃይማኖት ተቋም ሄዶ 'የኃይማኖት አባቶች ስለ እኔ ግድ የላቸውም' ብሎ ያምናል። የመጥፋት ስሜት፤ እናት አባት የሌለው ትውልድ የመሆን ስሜት ይታይበታል" ሲሉም ትዝብታቸውን ያካፍላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት "ባለሥልጣናትን በቴሌቪዥን እያየ አባቶቼ ናቸው ብሎ እንዲያምን የሚያስችለው ሁኔታ ላይ አይደለም። ፖለቲካውም ምኑም እንደዚያ እንዲያስብ አያስችሉትም። መሪ የሌለው ትውልድ ደግሞ ለሥነ ምግባር ችግር የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ነው"ይላሉ።

አክለውም "በየትም ሆነ በየት ተገፋፍተህ፤ በሌላው ላይ ተረማምደህም ቢሆን ራስህን አድን ዓይነት አስተሳሰብ ውስጥ ነው የምንገባው፤ በመሆኑም ይህ ትውልድ መሪ አጥቷል" ሲሉ ይተቻሉ።

ጨለምተኛ አስተሳሰብ ውስጥ መግባት እና ብርሃን እንዳለ አለማሰብም ይታያል የሚሉት ዶ/ር መስከረም "አዕምሮን ጨለማ ከወረሰው ምክንያታዊነት አይታሰብም ግን ጨለማን ያወረሰው ማን ነው? በግለሰባዊ ደረጃ ማን ነው ጉዳቱ ያለበት? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። በቴሌቪዥን ወጥቶ ማውራት አይለውጥም።" ሲሉ መፍትሔ አመንጭ ጥያቄያቸውን ይሰነዝራሉ።

" ተቆሳስለን መራራቅ፤ ከዚያ እንታረቅ መባባል ነው አሁን ያለው፤ ብዙ ያልተሰራ ነገር አለ፤ በሳል ሰው ያላየ ራሱ በሳል ሊሆን አይችልም" ሲሉም ጠንከር ያለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ትምህርቱ መሰጠቱ ምን ይለውጣል?

ግብረ ገባዊነት የኅብረተሰብና የአገር መሠረት ከመሆኑ አንፃር ከታች ጀምሮ የግብረ ገብ ትምህርት መሰጠት አለበት የሚል አቋም አላቸው- ዶ/ር ዳኛቸው።

ዶ/ር መስከረም በበኩላቸው "የሚያመጣውን ለውጥ አሁን ማየት አስቸጋሪ ቢሆንም ተማሪዎች እንዲነጋገሩ፤ መምህራንም ክፍተት ያለበትን ቦታ እንዲረዱ እና ራሳቸውን እንዲፈትሹ እድል ይከፍትላቸዋል" ይላሉ።

ነገር ግን በቅርፅ ላይ ሳይሆን ግለሰብ ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራ ሥራ ነው ለውጥ የሚያመጣው የሚል እምነትም አላቸው።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ