ታዋቂ አፍሪካውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ አንሄድም አሉ

የዙሉ ወንዶች Image copyright Getty Images

ጥቂት የማይባሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ አፍሪያውያን ከዚህ በኋላ እግራቸው ደቡብ አፍሪካን እንደማይረግጥ እየገለጹ ነው። ምከንያታቸው ደግሞ በሰሞኑ ከሌላ አገራት የመጡ አፍሪካውያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግድያና ዝርፊያ በመቃወም ነው።

ናይጄሪያውያን ሙዚቀኞች እና የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ውሳኔያቸውን ይፋ ለማድረግ ግንባር ቀደሞች ሆነዋል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት የተፈጸሙትን ጥቃቶች አወገዙ

ደቡብ አፍሪቃዊቷን የቦክስ ቻምፒዮን የገደለው ተያዘ

ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ከሆኑ አገራት አንዷ ስትሆን፤ በርካታ አፍሪካውያን ሠርተን እንቀየራለን በማለት ወደ አገሪቷ ያቀናሉ።

ይህ ደግሞ ሥራ አጥ ለሆኑ በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን እንደ ትልቅ ስጋት ነው የሚታየው ብለዋል የአገሪቱ የማህበረሰብ ልማት ሚኒስትር።

ናይጄሪያዊው ታዋቂ የአፍሮቢት ስልት አቀንቃኝ 'በርና ቦይ' የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከእንቅልፉ እስከሚነቃ ድረስ ወደ ደቡብ አፍሪካ ድርሽ አልልም ሲል መልእክቱን በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።

''ከዚህ በፊት እ.አ.አ. በ2017 ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የጥላቻ መልዕክቶችና ጥቃቶችም ደርሰውብኝ ነበር'' ብሏል።

ሌላዋ ናይጄሪያዊ ዘፋኝ 'ቲዋ ሳቬጅ' በበኩሏ፤ በያዝነው ወር በደቡብ አፍሪካ ልታዘጋጀው የነበረውን የሙዚቃ ኮንሰርት መሰረዟን በትዊተር ገጿ አስታውቃለች።

''ደቡብ አፍሪካውያን በሕዝቦቼ ላይ እየፈጸሙት ያለው ኢ-ሰብአዊና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊትን እቃወማለሁ'' ብላለች።

የናይጄሪያ መንግሥት ደግሞ በደቡብ አፍሪካዋ ኬፕ ታውን እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ስብሰባ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዬሚ ኦሲባንጆ ስብሰባውን እንደሚታደሙ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም ኬፕ ታውን እንደማይሄዱ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት ሞሃመዱ ቡሃሪ ናይጄሪያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዳይሄዱ በትዊተር ገጻቸው አስጠንቅቀዋል።

በሌላ በኩል የዛምቢያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፊታችን እሁድ ከደቡብ አፍሪካ ጋር በዋና ከተማዋ ሉሳካ ሊያደርገው አስቦት የነበረውን የወዳጅነት ጨዋታ መሰረዙን አስታውቋል።

''ይህንን የወሰንነው ከደህንነት ስጋት አንጻር ነው። ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማንም ሊያውቅ አይችልም። የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድንን ደህንነት ማረጋገጥ እንፈልጋለን'' ብለዋል የፌደሬሽኑ ዋና ጸሃፊ አድሪያን ካሻላ።

ትሬቨር ኖዋ የዓለማችን አራተኛው ቱጃር ቀልደኛ ሆነ

እራስን ለማጥፋት ከማሰብ ወደ ሚሊየነርነት

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ፤ አገራችን የሁሉም አፍሪካውያን ቤት ናት የሚል መልዕክት ቢያስተላልፉም፤ የአገሬው ሰው ሊሰማቸው ፍቃደኛ የሆነ አይመስልም። ብዙዎች አሁንም በንግድ ሥራ የተሰማሩ የሌሎች አገራት ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ ይውጡልን እያሉ ነው።

በናይጄሪያ ደግሞ የደቡብ አፍሪካውያን የሆኑ ድርጅቶች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። 'ሾፕራይት' የተባለው ታዋቂ ደቡብ አፍሪካ መደብር ናይጄሪያ ውስጥ ጥቃት ተፈጽሞበታል። የአገሪቱ ፖሊስም ሁኔታውን ለመቆጣጠር አስለቃሽ ጭስ ለመጠቀም ተገዷል።

'ኤምቲኤን' የተባለው የደቡብ አፍሪካ የቴሌኮም ድርጅትም በናይጄሪያ የሚገኙ ሁሉንም ሱቆቹን እየዘጋ እንደሆነ አስታውቋል።

በደቡብ አፍሪካ ቢያንስ አምስት ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ የገለጸ ሲሆን፤ ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ደቡብ አፍሪካውያን መሆናቸውን አረጋግጫለው ብሏል። የቀሪዎቹ ዜግነት ግን እስካሁን አልታወቀም ተብሏል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እስካሁን 189 ሰዎች በቁጥጥር ውለዋል።