የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ማን ነበሩ?

ሮበርት ሙጋቤ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ሮበርት ሙጋቤ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1924 የተወለዱት ሮበርት ሙጋቤ የእንጨት ሠሪ ልጅ ናቸው። የተማሩት በሮማን ካቶሊክ ሚሽነሪ ትምህርት ቤት ነበር።

ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ፎርት ሀሬ ዩኒቨርስቲ ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው ከተማሩ በኋላ፤ ጋና ውስጥ መምህር ነበሩ።

ጋና ሳሉ በፓን አፍሪካዊው ክዋሜ ንክሩማ አስተሳሰብ እጅግ ይማረኩ ነበር። የመጀመሪያ ባለቤታቸውም ጋናዊት ነበሩ።

በ1960 ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ መጀመሪያ ላይ ከጆሽዋ ንኮሞ ጋር በጋራ ሠርተዋል። ኋላ ላይ ግን 'ዚምባብዌ አፍሪካን ናሽናል ዩኒየን' ወይም ዛኑን መሰረቱ። የጆሽዋ ንኮሞ ፓርቲ ከሆነው 'ዚምባብዌ አፍሪካን ፒፕልስ ዩኒየን' ወይም ዛፑ ፓርቲ ጋር በቅርበት ይሠሩ ነበር።

ዛኑን በመሰረቱ በአራተኛው ዓመት ጠቅላይ ሚንስትር ኢን ስሚዝና አስተዳደራቸውን በመሳደባቸው ታሠሩ። እሥር ላይ ሳሉ ልጃቸው ቢሞትም ቀብሩ ላይ ለመገኘት ፍቃድ አልተሰጣቸውም ነበር።

በጎርጎሳውያኑ 1973 ላይ እዛው እሥር ቤት ሳሉ የዛኑ ፕሬዘዳንት ሆነው ተመረጡ። ከእሥር ከተለቀቁ በኋላ ወደ ሞዛምቢክ አቅንተው ያኔ 'ሮዴዢያ' ትባል ወደነበረችው የአሁኗ ዚምባብዌ የጎሪላ ተዋጊዎች ልከው ነበር።

የሮበርት ሙጋቤ ጥቅሶች

ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣን ለቀቁ

ሮዴዢያ ነፃነቷን እንድታገኝ ያደርጉት በነበረው ጥረት ወለም ዘለም የማያውቁ፣ ቆፍጣና ሰው መሆናቸውን አስመስክረዋል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ሙጋቤ (በስተግራ) ጆሽዋ ንኮሞ (በስተቀኝ) 1960ዎቹ አካባቢ

የሙጋቤ የመደራደር ብቃት ተቺዎቻቸውን ሳይቀር በአድናቆት ያስጨበጨበ ነበር። 'ዘ ቲንኪንግ ማንስ ጉሬላ' እየተባሉም ተሞካሽተዋል።

ሙጋቤ በአመራር

በህመም ሳቢያ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሙጋቤ ዚምባብዌ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የመጀመሪያው መሪ ናቸው። ሙጋቤ አገራቸው ዴሞክራሲ የሰፈነባት እንደምትሆን ቃል ገብተው ነበር።

ያሉት ግን አልሆነም። ዚምባብዌ በግጭት የምትናጥ፣ በሙስና የተጨመላለቀች፣ ኢኮኖሚዋ የተናጋ አገር ሆነች።

ሙጋቤ ምዕራባውያንን አጥብቆ በመተቸት ይታወቃሉ። በተለይ የቀድሞው የዚምባብዌ ቅኝ ገዢ ዩናይትድ ኪንግደምን "ጠላት አገር" ይሏት ነበር። ምንም እንኳን ሙጋቤ ለተቀናቃኞቻቸው ርህራሄ አልባ ቢሆኑም የአፍሪካ አገራት መሪዎችን ድጋፍ ለማግኘት አልተቸገሩም።

ማርክሲስት ነኝ የሚሉት ሙጋቤ ሥልጣን እንደያዙ፤ ደጋፊዎቻቸው ሲፈነድቁ ነጮች በተቃራኒው ከዚምባብዌ ለመውጣት ሻንጣቸውን ሸክፈው ነበር።

ሆኖም ሙጋቤ ይቅር መባባልን ያማከሉ ንግግሮች በማድረግ ተቀናቃኞቻቸውን ለማጽጽናት ሞክረዋል።

Image copyright Getty Images

ሙጋቤ አብረዋቸው ይሠሩት ከነበሩት ጆሽዋ ንኮሞ ጋር በምርጫ ፉክክር ወቅት ቅራኔ ውስጥ ገብተው ነበር። ዛኑ አብላጫ ድምፅ ሲያገኝ ምርጫው ተጭበርብሯል ተብሎም ነበር።

ለዘመናት በስልጣን ላይ ያሉት ስድስቱ መሪዎች

ሙጋቤ ከሥልጣን አልወርድም እያሉ ነው

የዛፑ ንብረት በሆኑ አካባቢዎች መሣሪያ ከተገኘ በኋላ ጆሽዋ ንኮሞ በካቢኔ ሽግሽግ ከሥልጣናቸው ዝቅ ተደርገዋል። ሙጋቤ ደጋግመው ስለዴሞክራሲ ቢናገሩም፤ በ1980ዎቹ የንኮሞ ደጋፊዎች ናቸው የተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተጨፍጭፈዋል።

በሰሜን ኮሪያ በሰለጠኑት አምስተኛ ብርጌድ የዚምባብዌ ጦር ጭፍጨፋ ሙጋቤ እጃቸው እንዳለበት ቢነገርም፤ ሕግ ፊት ቀርበው ግን አያውቁም።

የዛፑ ፓርቲ መሪ ጆሽዋ ንኮሞ በደረሰባቸው ከፍተኛ የሆነ ጫና ምክንያት፤ ከዛኑ ጋር ለመቀላቀልና በጣም ጠንካራ የሆነውን 'ዛኑ ፒ-ኤፍ' የተባለ ፓርቲ ለመመስረት ተስማምተው ነበር።

ይሁን እንጂ በ1987 ሙጋቤ የአገሪቷ ፕሬዝደንት ሆነው ተሾሙ። ከዚያም በ1996 ለሦስተኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመን ለፕሬዚደንትንት ተመረጡ።

ባለቤታቸው በካንሰር በሽታ በሞት ከተለየቻቸው በኋላ በዚያው ዓመት መጀመሪያ ከግሬስ ማሩፉ ጋር ትዳር መሰረቱ። ሙጋቤ አርባ ዓመት ከሚበልጧት ባለቤታቸው ግሬስ ሁለት ልጆችን አፍርተዋል። ሦስተኛውን ልጃቸውንም የወለዱት የ70 ዓመት የዕድሜ ባለ ፀጋ ሳሉ ነበር።

ሙጋቤ ከዘረኝነት አስተሳሰብ ነፃ የወጣ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በርካታ ተግባራት አከናውነዋል። በጎርጎሳውያኑ 1992 ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የመሬት ባለቤት መሆን የሚያስችል የመሬት ይዞታ ደንብ አስተዋወቁ። የደንቡ ዓላማ የነበረው ከ4500 በላይ በሚሆኑ ነጭ ገበሬዎች ተይዞ የነበረውን መሬት የዚምባብዌ ባለቤት ለሚሏት ጥቁሮች እንደገና ለማከፋፈል ያለመ ነበር።

Image copyright AFP

በዚህ ምክንያት በ2000 መጀመሪያ አዲስ የተመሰረተው ለዲሞክራሲዊ ለውጥ ንቅናቄ [ሙቭመንት ፎር ዲሞክራሲ ቼንጅ] መሪ በነበሩት ሞርጋን ፅፋንጊራይ በሚመራው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ነበር።

ሙጋቤ ከአርሶ አደሮቹ ጎን ባለመቆማቸው የእንቅስቃሴው ደጋፊ ተደርገውም ይቆጠሩ ነበር። የቀድሞ ወታደሮች በነጮች ተይዞ የነበረውን መሬት የግላቸው ያደረጉ ሲሆን፤ በወቅቱም በርካታ ገበሬዎችና ጥቁር ሠራተኞች ተገድለዋል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ 2008 አካባቢ የኤምዲሲ የመብት ተሟጋቾች ጥቃት ደርሶባቸው ነበር

የዚምባብዌ የፖለቲካ ሽኩቻ

በ2000 ምርጫ የዚምባብዌ ምክር ቤት 57 መቀመጫዎች በኤምዲሲ ፓርቲ ቢወሰዱም፤ የዛኑ ፒ-ኤፍ ፓርቲ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ለማድረግ ሲባል 20 መቀመጫዎችን በቀጥታ ሙጋቤ ሰይመዋል።

ከሁለት አመት በኋላ በተደረገ ምርጫ ደግሞ ሙጋቤ 56.2 በመቶ ሲያሸንፉ ተፎካካሪያቸው ሻንጋራይ 41.9 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል። ነገር ግን በርካታ የገጠር አካባቢ ሰዎች እንዳይመርጡ ክልከላ ተደርጎባቸው የነበረ ሲሆን፤ ከምርጫ በኋላም በመላ አገሪቱ ተቃውሞ ተቀጣጥሎ ነበር።

ኤኤምሲ ፓርቲን በመደገፍም አሜሪካ፣ እንግሊዝና የአውሮፓ ህብረት ምርጫው ተጭበርብሯል በማለትና ቀጥሎ የመጣውን ሕዝባዊ ተቃዉሞ በመደገፍ ዚምባብዌንና ሙጋቤን ያለደጋፊ ብቻቸውን አስቀርተዋቸዋል።

ደቡብ አፍሪካ በናይጄሪያ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለምን ዘጋች?

ለጉብኝት ክፍት የተደረገው የቀድሞው ማዕከላዊ እሥር ቤት በፎቶ

የጋራ ብልጽግና መድረክ ዚምባብዌ የዴሞክራሲ መሻሻል እስከምታሳይ በማለት ከማንኛውም ጉባዔ አግዷት ነበር።

ጥቁር ገበያን ለመቆጣጠር በሚል በ2005 የተደረገው ንቅናቄ በአገሪቱ ሕገ ወጥነትን የበለጠ አባብሶታል። 30 ሺህ የሚደርሱ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ሲታሠሩ፤ በርካታ ትንንሽ ከተሞች ወድመዋል። 700 ሺህ የሚጠጉ ዚምባብዌያውያን ቤት አልባም ሆነዋል።

2008 ላይ ሙጋቤ ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ የመጀመሪያው ዙር ላይ ቢረቱም፤ በመጨረሻ ተስቫንጊራይ ከውድድሩ ራሳቸውን ስላገለሉ ሥልጣን ይዘዋል።

በተስቫንጊራይ ደጋፊዎች ላይ ጥቃት ከመሰንዘሩ አስቀድሞ ተስቫንጊራይ በዚምባብዌ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ ማድረግ አይታሰብም ብለው ነበር። ከዛ በኋላ ዚምባብዌ በኑሮ ውድነት ትናጥ፣ ምጣኔ ሀብቷም ያሽቆለቁል ጀመር።

መንግሥት የውሀ ማከሚያ ከውጪ ለማስገባት አቅም ስላልነበረው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኮሌራ ምክንያት ለሞት መዳረጋቸውን ተከትሎ፤ ሙጋቤ ከተቀናቃኛቸው ጋር ሥልጣን ለመጋራት ፍቃደኛነት አሳይተዋል።

ለወራት ከዘለቀ ድርድር በኋላ 2009 ላይ ሙጋቤ ተስቫንጊራይን ጠቅላይ ሚንስትር አድርገው ሾሟቸው።

ሆኖም የመብት ተሟጋቾች ሙጋቤ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ያሰቃያሉ ሲሉ ይከሷቸዋል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ሮበርት ሙጋቤ

ገደብ የለሽ ሥልጣን የታየበት ምርጫ

ወቅቱ በዚምባብዌ ገደብ የለሽ ሥልጣን የታየበትና የ89 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው ሙጋቤ በተወዳዳሪነት የቀረቡበት ነበር። ሆኖም ሙጋቤ እድሜያቸው እየገፋ ሲመጣ ለተለያዩ የጤና ችግሮች መጋለጣቸው አልቀረም።

በወቅቱ ማን ሊተካቸው ይችላል? የሚል ስጋትም ነበር። ሁኔታው የሙጋቤ አስተዳደር ሕዝቡ ላይ ጫና እንዳሳደረ አሳይቷል። የዚምባብዌ አስተዳደር ምን ያህል የተከፋፈለ እንደሆነ የሚያሳዩ ነገሮች ቀስ በቀስ መገለጥም ጀምረዋል።

በወቅቱ ሙጋቤ ምንም ተቀናቃኝ እንዳይገጥማቸው፤ ተከታዮቻቸው እርስ በርሳቸው እንዲጠላለፉ ሆነ ብለው ፖለቲካዊ ጨዋታ ይጫወቱ ነበር ተብሏል። ሙጋቤ ቢሞቱ እንኳን ባለቤታቸው ግሬስ እሳቸውን በመተካት ሥልጣን እንደሚይዙ ወሬዎችም ይናፈሱ ነበር።

"የሞራል ባቢሎን ውስጥ ነው ያለነው፤ በጎና እኩይ መለየት አቅቶናል" ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

የስድስት ቀን ጨቅላ በቦርሳዋ ይዛ የተገኘችው ሴት ተከሰሰች

እሳቸውም የዋዛ አልነበሩም 2015 ላይ በ2018 በሚደረገው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ። 2016 ላይም ፈጣሪ ወደ ማይቀርበት ሞት እስከሚጠራቸው ድረስ ሥልጣን ላይ እንደሚቆዩ ተናገሩ።

ታዲያ ያኔ ሙጋቤ ቢመረጡ ኖሮ የ94 ዓመት አዛውንት ፕሬዚደንት ይሆኑ ነበር።

የሆነው ሆኖ ከፈጣሪ የተላከ ሞት ሳይሆን የዚምባብዌ ብሔራዊ ጦር ወደ ሮበርት ሙጋቤ ገሰገሰ። ሕዳር 15፣ 2017 ላይ በቁጥጥር ሥር ውለው ለአራት ቀናት በቁም እስር ከቆዩ በኋላ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የዛኑ ፒ-ኤፍ መሪ ሆነው ሙጋቤን ተኩ።

ሙጋቤ 'ሥልጣኔን ምን ሲሆን እለቃለሁ?' ብለው ቢያንገራግሩም፤ ከስድስት ቀናት በኋላ የዚምባብዌ ፓርላማ ሮበርት ሙጋቤ ከሥልጣናቸው መነሳታቸውን አበሰሩ።

ሙጋቤ ሥልጣናቸውን የለቀቁት እሳቸውም ሆነ ቤተሰባቸው ወደፊት ከሚደርስባቸው ማንኛውም ችግር እንዲጠበቁና በሚፈልጉት የንግድ ዘርፍ ለመሰማራት እንዲችሉ ከተደራደሩ በኋላ ነበር። ቤት፣ ሠራተኞች፣ ተሽከርካሪዎች እና ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ሥልጣንም ተሰጥቷቸዋል።

ሙጋቤ በግል ሕይወታቸው

ሙጋቤ በአለባበሳቸው 'ወግ አጥባቂ' የሚባሉ ነበሩ።

የአልኮል መጠጦችን የማይቀምሱ፤ ወዳጆቻቸውንና ጠላቶቻቸውን ለይተው የሚያውቁ ነበሩ ይባላል።

አፍሪካን ከቅኝ አገዛዝ ለማውጣት ሲታገሉ 'የአፍሪካ ጀግና' ተደርገው የሚወሱት ሮበርት ሙጋቤ፤ ወደ ጨቋኝ መሪነት በመለወጣቸው ይተቻሉ። አገሪቷንም ወደ ባሰ ድህነት እንዳሸጋገሯትም ይነገራል። ራዕያቸው ግን በዚምባብዌ ታሪክ ሲዘከር ይኖራል።

ሙጋቤ ሕይወት ወሳኝ የሚባሉ ዓመታት- እንደ ጎርጎሳውያን አቆጣጠር

1924፡ የተወለዱበት ዓመት

1964፡ በሮዲዥያ መንግሥት የታሠሩበት

1980፡ ከነጻነት በኋላ ያለውን ምርጫ አሸነፉ

1996፡ ግሬስ ማሩፉን አገቡ

2000፡ በሕዝበ ውሳኔ ተሸነፉ። በዚህ ምክንያት ደጋፊ ሚሊሻዎቻቸው በነጭ የተያዘውን እርሻ ቀምተው፤ በተቃዋሚ ደጋፊዎች ላይ ጥቃት አደረሱ።

2008፡ በመጀመሪያ ዙር ምርጫ ከሻንጋራይ ቀጥሎ ሁለተኛ ሆኑ። ቢሆንም በደጋፊዎቻቸው ላይ በመላ አገሪቱ በደረሰ ጥቃት ሻንጋራይ ምርጫውን አቋረጡ።

2009፡ የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት መዳከሙን ተከትሎ ሻንጋራይን ጠቅላይ ሚንስትር አድርገው ሾሙ።

2017፡ ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ እንዲተኳቸው መንገድ ለመጥረግ ሲባል ምክትላቸው ኤመርሰን ምናንጋግዋን ከሥልጣን አገዱ።

ሕዳር 2017፡ ወታደሩ ጣልቃ በመግባት ከሥልጣን አወረዳቸው

ተያያዥ ርዕሶች