በዓመቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች ጥቂቱ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ችግኝ ሲተክሉ
አጭር የምስል መግለጫ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ችግኝ ሲተክሉ

ኢትዮጵያ 2011 ዓ. ም. ን አገባዳ 2012ን ልትቀበል የቀሯት ጥቂት ቀናቶች ናቸው። በ2011 ዓ. ም. በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ አነጋጋሪ፣ አወዛጋቢ፣ አሳዛኝ እንዲሁም የሰውን ስሜት ሰቅዘው ይዘው ከነበሩት ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹ እነሆ. . .

የውጤት ግሽበት

በቅርቡ የዘንድሮ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት በተሰጡት አራት የትምህርት አይነቶች ብቻ እንደሚወሰን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። ከ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ትምህርቶች ሒሳብ፣ እንግሊዝኛ፣ አፕትቲዩድ፣ ጂኦግራፊና (ለማኅበራዊ ሳይንስ) ፊዚክስ (ለተፈጥሮ ሳይንስ) ተመርጧል።

አጭር የምስል መግለጫ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት በተሰጡት አራት የትምህርት አይነቶች ብቻ መወሰኑ አነጋጋሪ ነበር

እንደ ምክንያት የተቀመጠው ደግሞ ሌሎቹ የትምህርት አይነቶች ከፍተኛ የውጤት ግሽበት ስለታየባቸው መሆኑም ተገልጿል። ጉዳዩ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን፤ በፈተና አሰጣጡ ላይ ችግሮች ከነበሩ መስተካከል የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው ወይ? በተመረጡት ትምህርቶች ውጤት ብቻ መዳኘት ተማሪዎችን ማዕከል ያላደረገ እንዲሁም እድል የሚነፍጋቸው ነው ብለው የተቹትም አልታጡም።

ብሔራዊ ፈተናዎች ምን ያህል ከስርቆትና ከስህተት የተጠበቁ ናቸው?

350 ሚሊዮን ችግኞች

ሐምሌ 22፣ 2011 ዓ. ም. ኢትዮጵያ በ12 ሰዓታት ውስጥ 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ቆርጣ ተነሳች። በቀኑ መገባደጃ ላይ የፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ፤ አገሪቱ 350 ሚሊዮን ችግኞችን መትከሏን አሳወቁ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፤ የደን መመናመንን ለመከላከል አርባ ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ችግኝ የመትከል ዕቅድ ይዘው የተነሱት በቅርቡ ነው።

መንግሥት እንደሚለው፤ የሚተከሉት ዛፎች ለበጎ ፈቃደኞች መታደል የጀመሩት ከሦስት ቀናት በፊት ጀምሮ ነበር። በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዕለተ ሰኞ ሐምሌ 22፣ 2011 ዓ. ም. መደበኛ ሥራቸውን በመተው ዛፍ በመትከል እንዲውሉ ተደረገ።

ችግኝን በዘመቻ መትከል መቼ ተጀመረ?

በአንድ ቀን 350 ሚሊዮን ዛፎች መትከል ይቻላል ወይ? የሚለው ብዙዎችን ሰቅዞ የያዘ ጉዳይ ነበር። እንደተለመደው ጉዳዩ የማኅበራዊ ድር አምባ መነጋገሪያ ከመሆን አልተቆጠበም። ይቻላል ብለው የተነሱና ችግኝ የተከሉ፤ ከዛፉ ጋር ፎቶ የተነሱ ባይጠፉም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያጋጠማቸውን የፖለቲካ ፈተና በችግኝ ተከላ ሽፋን እያደባበሱት ነው ብለው የወቀሱም አልጠፉም።

አጭር የምስል መግለጫ ሰኞ ሐምሌ 22፣ 2011 ዓ. ም. የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሁም የግል ተቀጣሪዎችም መደበኛ ሥራቸውን በመተው ዛፍ ተክለዋል

የመረጃ ትክክለኛነትን የሚያረጋግጠው ክፍላችን ቢቢሲ ሪያሊቲ ቼክ፤ በቀን 350 ሚሊዮን ዛፎች መትከል ባያዳግትም፤ እጅግ ከባድ ዝግጅት ይጠይቃል ይላል። ባለሙያዎችም ይህንን ነው የሚሉት። አልፎም ክብረ ወሰን የሚመዝግበው 'ጊነስ ወርልድ ሬከርድስ' ከኢትዮጵያ የደረሰን መረጃ የለም ማለቱ መነጋገሪያ ርዕስ ነበር።

ስለጉዳዩ በቢቢሲ አማርኛ የተሠራ ዘገባ፦ ጊነስ ዎርልድ ሪከርድስ፡ «ስለተተከሉት ዛፎች ከኢትዮጵያ የደረሰን ማስረጃ የለም»

ቶቶ ቱርስ

ቶቶ ቱርስ የተሰኘው ዓለም አቀፍ አስጎብኝ ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርግ የነበረው ጉዞ በዓመቱ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር። ድርጅቱ ወደ ላሊበላ ይዟቸው ሊመጣ ያሰባቸው ጎብኝዎች የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን መሆናቸው ነው ጉዳዩ እንዲጦዝ ያደረገው።

ቶቶ ቱርስ በኢትዮጵያ ለ14 ቀናት የሚዘልቅ የጉብኝት መርኃ ግብር አውጥቶ ጎብኚዎችን እየመዘገበ ሳለ ነበር ተቃውሞ እየተበረታበት የመጣው። በአንድ ሰው 7 ሺህ 900 የአሜሪካን ዶላር የሚጠየቅበት ይህ የጉብኝት ፕሮግራም በሁለት ሳምንት ቆይታው አርባ ምንጭ፣ ደቡብ ኦሞ፣ የጣና ገዳማት፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ አክሱምን እና ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለማስጎብኘት መርሃ ግብር ቀርፆ ነበር።

Image copyright NURU Photo
አጭር የምስል መግለጫ ጫናው የበረታበት ቶቶ ቱርስ ለጎብኝዎቹ ደህንነት በመስጋት ጉዞውን ሰርዟል

መጀመሪያ ላይ ድርጅቱ ምንም እንኳ ተቃውሞ ቢረታበትም ጎብኝዎች ይዞ ወደ ላሊበላ ከመጓዝ እንደማይቆጠብ አስታውቆ ነበር። የቶቶ አስጎብኚ ድርጅት መስራች እና ባለቤት ዳን ዌር በበኩላቸው ''በተፈጠረው ነገር በጣም አዝኛለሁ። ወደ ኢትዮጵያ የምናደርገውን ጉዞ ግን አንሰርዝም'' ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠው ነበር።

ይህ ጉዳይ ማኅበራዊ ድር አምባ እንዲሁም መገናኛ ብዙሃን ላይ በርካቶች በተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ላይ ያላቸውን እይታ ጎራ ለይተው የተወያዩበት ሆኗል። ብዙዎችም ጥቃት እንደሚያደርሱ የዛቱ ሲሆን፤ የኋላ ኋላ ግን ጫናው የበረታበት ቶቶ ቱርስ ለጎብኝዎቹ ደህንነት በመስጋት ጉዞውን ሰርዟል።

ስለጉዳዩ በቢቢሲ አማርኛ የተሠራ ዘገባ፦''ወደ ኢትዮጵያ የምናደርገውን ጉዞ አንሰርዝም''

የምክትል ከንቲባው ጫማ እና ቪላ

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከመገናኛ ብዙሃን እና ከማኅበራዊ ድር አምባ አፍ ጠፍተው አያውቁም።

አጭር የምስል መግለጫ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ

አንድ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተካሄደ ያለን አንድ የግንባታ ሥፍራን ሲጎበኙ የተጫሙት ጫማ የሰውን ቀልብ ስቦ ነበር። 'ባሌንሲያጋ' የተሰኘው ይህ አሜሪካ ውስጥ የሚመረት ጫማ ዋጋው ውድ መሆኑ ነው ሰዎች ፎቶዉን እንዲጋሩትና እንዲነጋገሩበት ያደረጋቸው።

"አዲስ አበባ የምንወዛገብባት ሳትሆን በጋራ የምንኖርባት ከተማ ናት" ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ

በበይነ መረብ መሻሻጫ መስኮቶች ላይ ይህ ጫማ በወቅቱ ገበያ በትንሹ 780 ዶላር [22 ሺህ ብር ገደማ] ያወጣል። ይህ ለአንድ ጫማ የተሰጠ ዋጋ መናር ብዙዎችን አደናግሮ ነበር። ከንቲባው የፈለጉትን መጫማት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ነው ሲሉ የሞገቱም አልጠፉም።

ከዚህ በተጨማሪ የምክትል ከንቲባው ነው የተባለ ቤት በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን፤ በተለይም ለኪራይ የሚከፍሉት 140ሺ ነው መባሉ ደግሞ የበለጠ ጉዳዩን ወደ ሌላ መስመር ወስዶት ነበር። ቀጥሎም ከንቲባው ለኪራይ የሚከፍሉት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ሳይሆን 680 ብር ብቻ ነው መባሉ የአንድ ሰሞን የማኅበራዊ ሚዲያ ወሬ ማድመቂያ ሆኗል።

የ "መፈንቅለመንግሥት" ሙከራ

ኢትዮጵያ ስድስት ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮችን ያጣችው በጥቂት ቀናት ልዩነት ውስጥ ነበር።

ቅዳሜ አመሻሽ፤ ሰኔ 15፣ 2011 ዓ. ም. ። ባህር ዳር በተኩስ ተናወጠች፤ አዲስ አበባም የቀለሃ ድምፅ ተሰማ። መንግሥት የመንበር ፍንቀላ ሙከራ ነው ባለው በዚህ ጥቃት፤ ባህር ዳር ከተማ ላይ የክልሉ አስተዳዳሪ የነበሩት አምባቸው መኮንን [ዶ/ር] እና አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ ወዲያውኑ ሕይወታቸው ማለፉ ታወቀ።

አልፎም አዲስ አበባ ላይ ደረሰ በተባለው ጥቃት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጄኔራል ሰዓረ መኮንን እና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮነን ጄኔራል ገዛኢ አበራ መገደላቸው ታወቀ። ክስተቱ ከተሰማበት አልፎ ባለው ሰኞ ደግሞ በቅዳሜው አደጋ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩት የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ ማለፋቸው ተነገረ።

አጭር የምስል መግለጫ ከግራ ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፣ ጄነራል አሳምነው ፅጌ እና አምባቸው መኮንን [ዶ/ር]

የባህር ዳሩ እና የአዲስ አበባው ጥቃት ግንኙነት አላቸው ሲል መንግሥት አስታወቀ። ዋነኛ ተጠርጣሪ ደግሞ የአማራ ክልል የፀጥታ ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ መሆናቸው ተነግሮ ግለሰቡን ፍለጋ መጠናከሩ ተነገረ።

ሰኞ ሰኔ 17፣ 2011 ዓ. ም. ዘንዘልማ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ብሔራዊው የቴሌሊቪዥን ጣቢያ አስታወቀ።

ከቅዳሜ እስከ ሰኞ ድረስ የተሰሙት ዜናዎች ለበርካታ ኢትዮጵያውያን አስደንጋጭ የነበሩ ናቸው። ከ "መፈንቅለ መንግሥቱ" ጋር ተያይዞ የጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሰአረ መኮንን እና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ገዳይ ተብሎ የተጠረጠረው ጠባቂያቸው ጉዳይ ውዥንብር መፍጠራቸውንም ብዙዎች በማኅበራዊ ሚዲያቸው አጋርተዋል።

ጄነራል ሰዓረ ላይ ጥቃት አድርሷል የተባለው ግለሰብ ቢጎዳም በቁጥጥር ሥር መዋሉ መጀመሪያ ተገለፀ። ትንሽ ቆይቶ ግለሰቡ ቢቆስልም በቁጥጥር ሥር ውሏል የተባለው ግለሠብ ራሱን አጥፍቷል መባሉ ግርታን ፈጠረ። እንዴት በቁጥጥር ሥር ያለ ሰው ራሱን ያጠፋል? የብዙዎች ጥያቄ ነበር።

ነገር ግን ዘግይቶ ደግሞ ብሐራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ግለሰቡ አልሞተም፤ በሕይወት አለ ሲል አተተ። በብዙ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ውዝግብና መነጋገሪያ ሆኖም አልፏል።

ስለጉዳዩ በቢቢሲ አማርኛ የተሠራ ዘገባ፦ ስለ'መፈንቅለ መንግሥት' ሙከራው እስካሁን የማናውቃቸው ነገሮች

ዶላር

የዶላር የውጭ ምንዛሬ የጥቁር ገበያ ዋጋ በ2011 ዓ. ም. በጣም በርካታ ጊዜ ማሻቀብ እና ማሽቆልቆል አሳይቷል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በቅርቡ አንድ ዶላር በጥቁር ገበያ ያለው ዋጋ ከ40 ብር በላይ መድረሱ ተዘግቦ ነበር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፤ የዶላር የጥቁር ገበያ ሰዎች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ባሉት መሠረት፤ አንድ ሰሞን የጥቁር ገበያ ሱቆች ተዘግተዋል፤ ሲያሻሽጡ ነበሩ ያተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም የሚዘነጋ አይደለም። ቢሆንም በቂ ዶላር ባንኮች የላቸውም የሚል ቅሬታ በተለይም ከነጋዴዎች መሰማቱ አልቀረም።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችም በቂ ዶላር ባንኮች ውስጥ ሳይከማች ጥቁር ገበያውን ማሸግ አዋጭ አይደለም ሲሉ የመንግሥትን ውሳኔ የመጨረሻው መፍትሄ አይደለም ብለው ኮንነውት ነበር።

በቅርቡ አንድ ዶላር በጥቁር ገበያ ያለው ዋጋ ከ40 ብር በላይ መድረሱ ተዘግቦ ነበር። የጥቁር ገበያ ሱቆቹ ግን ከድንገተኛ የፖሊስ ፍተሻ አልዳኑም። እንደሌሎቹ አንገብጋቢ ርዕሶች ሁሉ የዶላር ዋጋ ማሻቀብ ጉዳይ ኢትዮጵያን እንዲወያዩበት ሆኗል።

ስለጉዳዩ በቢቢሲ አማርኛ የተሠራ ዘገባ፦ጥቁር ገበያውን ማሸግ መፍትሄ ይሆን?

ኢቲ 302 አደጋ

መጋቢት 1፣ 2011 ዓ. ም. ቀኑ ደግሞ እሁድ። በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የተሳፈሩ 157 ተጓዦች እንደወጡ ቀሩ።

ረፋድ ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማሪፊያን የለቀቀው መዘዘኛ አውሮፕላን በተነሳ በስድስተኛው ደቂቃ እንደተከሰከሰ ተሰማ። አውሮፕላኑ ውስጥ የ33 አገራት ዜጎች መኖራቸው ታወቀ። ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አፍሪቃ ደነገጠች፤ ዜጎቻቸው በአደጋው እንዳለፉ የሰሙት አውሮፓ እና አሜሪካም ዜናው ዱብ ዕዳ ሆነባቸው።

የኢቲ 302 የመጨረሻዎቹ ስድስት ደቂቃዎች

ከወራት በፊት በኢንዶኔዥያው ላይን ኤር የሚመራ ተመሳሳይ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን መከሰከሱ ሰዎች አደጋውን ከቦይንግ ጋር እንዲያይዙት አደረጋቸው።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የተሳፈሩ 157 ተጓዦች ሕይወታቸውን አጥተዋል

የኢቲ 302 አደጋ የመጀመሪያ ውጤት እንደጠቆመውም የአውሮፕላን አብራሪያው የተቻለውን ሁሉ ቢያደርግም አደጋውን መከላከል አለመቻሉን ነው። በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በቦይንግ መካከል ለወራት ጣት መቀሳሰር እና መወነጃጀል ሆነ።

በስተመጨረሻም ቦይንግ የአደጋውን ሙሉ ኃላፊነት መውሰዱን አመነ። ለሟች ቤተሰቦች የሚሆን ካሳ በማለትም 100 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን አስታወቀ። ይህ ካሳ ግን የሟች ቤተሰቦችን እጅግ ያስቆጣ ነበር።

በቦይንግ እና በሟች ቤተሰቦች መካከል ያለው እሰጥ አገባ አሁንም አልተቋጨም። የሟች ቤተሰቦች በጋራ በመሆን ቦይንግን ለመክሰስ እና ለመርታት አልመዋል። በዚሁ ሁሉ መካከል ግን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች አስፈላጊው ጥገና እስኪደርግላቸው ድረስ ከአገልግሎት ውጭ ይሁኑ ተብለው ታግደዋል።

የሴቶች ሹመት

ሚያዚያ 9፣ 2011 ዓ. ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቧቸው የካቢኔ አባላት እጩዎች በሙሉ ድምጽ ነበር የፀደቀላቸው። አዳዲስ ሚንስትሮችን ወደፊት ያመጡ ሲሆን፤ ስድስት ሚንስትሮችን ደግሞ ከነበሩበት ሥፍራ ወደሌላ ሚንስትር መሥሪያ ቤት እንዲዘዋወሩ አድርገዋል።

ከካቢኔው ተሿሚዎች መካከል 50 በመቶው ሴቶች መሆናቸው በወቅቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ እንደማስረገጫ ''የሴቶችን ተሳትፎ በሁሉም የአመራር እርከን ማረጋገጥ ስለሚያስፈልግ ነው'' ሲሉ ተናግረው ነበር።

ሃምሳ በመቶ የሚኒስትሮች ሹመት ለሴቶች

Image copyright Gegnit Ethiopia/ Twitter
አጭር የምስል መግለጫ ከካቢኔው ተሿሚዎች መካከል 50 በመቶው ሴቶች መሆናቸው በወቅቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር

በተለይ ሴቶችን በተመለከተ፤ በእሳቸው ካቢኔ ውስጥ የፆታ ተዋጽዖ እና ለሴቶች የተሰጠው የሥልጣን እርከን የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ የሚሞግቱ አልጠፉም። ሴቶች እንደሁልጊዜው የተለመዱ ቦታዎች ናቸው የተሰጧቸው፤ ቁጥሩ ብቻ ነው ከፍ ያለው የሚለው መከራከሪያ አቅርበውም ነበር።

ከዚህ ባለፈ ማኅበራዊ ሚዲያው የተለያዩ አስተያየቶችን አስተናግዷል። ሴቶች ሹመት የተሰጣቸው በሴትነታቸው ብቻ እንደሆነ ተደርጎ፤ ሌሎች ወንዶች ሲሾሙ የማይጠየቁ የብቃት ጥያቄዎች መንሸራሸራቸውንም አንዳንድ ነቃሾች እየተቹ ፅፈዋል።

ከካቢኔ ሹመት ባለፈ ሳህለወርቅ ዘውዴ የአገሪቱ ፕሬዝደንት፤ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት 2011 ዓ. ም. ላይ ነው።

እግር ኳስ እና የብሔር ፖለቲካ

እንከን የማያጣው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ እንደ 2011 ዓ. ም. የውድድር ዘመን የተፈተነ አይመስልም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፖለቲካው ወደ እግር ኳስ ሜዳ መግባቱ ለአድማጭ ለተመልካች በግልፅ የሚታይ እውነታ ነው።

ክልላቸውን ወክለው የሚጫወቱ ክለቦች ደጋፊዎች ሜዳ ድረስ ዘልቀው ተጫዋቾችና ዳኞችን እስከመምታት ደርሰዋል። የከነማ ክለቦችም ከዚህ የፀዱ አልነበሩም።

Image copyright Daniel Asmelash
አጭር የምስል መግለጫ ትግራይ ስታዲየም

ውድድሩ ሊጠናቀቅ ጥቂት ጨዋታዎች ሲቀሩት ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የመቀሌ 70 እንደርታ ጨዋታ ፌዴሬሽኑ በወሰነው መሠረት እንዲሰረዝ መደረጉ ነገሮች እንዲጦዙ ምክንያት ሆኖ ነበር። ፌዴሬሽኑ ጨዋታው በገለልተኛ ሜዳ [አዳማ] በዝግ እንዲካሄድ መወሰኑ ያልተወጠላቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ጨዋታውን እንደማያከናውኑ አስታውቀው ነበር። በዚህም ምክንያት ውድድሩ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ቆይቷል።

በስተመጨረሻም ፌዴሬሽኑ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ፤ የፀጥታ ኃይልም እንዲጠናከር አደርጋለሁ ብሎ የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታው እንዲከናወን ሆኗል። ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁም አይዘነጋም።

የኋላ ኋላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የነበረው መቀሌ 70 እንደርታ የመሪው ፋሲል ከነማ ነጥብ መጣልን ተከትሎ የ2011 ዓ. ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ መሆን ችሏል።

ስለጉዳዩ በቢቢሲ አማርኛ የተሠራ ዘገባ፦ ፌዴሬሽኑ፡ «የቡና እና መቀለ ደጋፊዎች ባሉበት ጨዋታ ሊካሄድ አይችልም»