ዶ/ር ደራራ ጢሞቲዎስ፡ በአሜሪካ ለከተማ ምክር ቤት አባልነት እየተወዳደሩ ያሉት ኢትዮጵያዊ

ዶ/ር ደራራ ጢሞቲዎስ Image copyright Dr Derara Timotiwos
አጭር የምስል መግለጫ ዶ/ር ደራራ ጢሞቲዎስ

ላለፉት 13 ዓመታት በአሜሪካ የኖሩት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ደራራ ጢሞቲዎስ፤ የአሜሪካ ዜግነታቸውን በእጃቸው ካስገቡ ገና አንድ ወራቸው ነው።

ይሁን እንጅ በአሁኑ ሰዓት በጆርጂያ ግዛት አትላንታ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው የክላርክስተን ከተማ የምክር ቤት አባል ለመሆን እየተወዳደሩ እንደሚገኙ ገልፀውልናል።

የኮንግረስ አባል ለመሆን እየተንቀሳቀሰ ያለው ኤርትራዊ

ትራምፕ ስለስደተኞች በተናገሩት ወቀሳ ደረሰባቸው

"ከዚህ ቀደምም ለምክር ቤት ለመወዳደር ፍለጎት ነበረኝ" የሚሉት ዶ/ር ደራራ፤ የአገሪቱን ዜግነት ሳያገኙ በመቆየታቸውና ያለ ዜግነት መወዳደር ባለመቻሉ ከዚህ በፊት በነበሩት ውድድሮች ላይ ሳይሳተፉ ቀርተዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ክላርክስተን 13 ሺህ ሰዎች የሚኖሩበት ትንሽ ከተማ ቢሆንም አብዛኞቹ ነዋሪዎች ስደተኞች ናቸው፤ ከተማውም የሚታወቀውም በዚሁ ነው።

"ይህ ከተማ በጣም ትንሽ ነው፤ ነገር ግን ከ40 አገራት በላይ የመጡ ዜጎች ይኖሩበታል፤ ለምሳሌ ከእኔ መኖሪያ ቤት በቀኝ በኩል ከኔፓል የመጡ ሰዎች ይኖራሉ፤ በግራ በኩል የሚኖሩት ደግሞ ከበርማ የመጡ ናቸው፤ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን እንዲሁም የሌላ አገር ዜጎችም በአካባቢያችን ይኖራሉ" በማለት ከተማው የተለያዩ ዜጎች ተሰባጥረው የሚኖሩበት መሆኑን ያስረዳሉ።

ከልጅነታቸው ጀምሮ በምክር ቤት የመወዳዳር ሃሳብ እንደነበራቸውና ያለፉበት የገዳ ሥርዓት ለውድድሩ ፍላጎት እንዳሳደረባቸው የሚናገሩት ዶ/ር ደራራ፤ ከአንድ ወር በፊት የአሜሪካ ዜግነት በማግኘታቸው ለውድድር መቅረብ እንደቻሉ ይናገራሉ።

በዚህም የአሜሪካ የዲሞክራሲን ሥርዓት "እውነት ለመናገር፤ አንድ ሰው ከሌላ ቦታ መጥቶ የሚኖርበትን ከተማ ለማስተዳደር መወዳዳር ማለት ትልቅ ነገር ነው" ሲሉ ያመሰግናሉ።

"ይህ ሰው ጎሳው ምንድን ነው? ከየት መጣ? ሳይሆን፤ ይህ ሰው ሃሳቡ ምንድን ነው? ምን መሥራት ይችላል? የሚለውን ነው የሚያዩት፤ በመሆኑም አገራችን ከዚህ ብዙ ነገር መማር ትችላለች" በማለት የፖለቲካ ተሳትፏቸው ለኢትዮጵያ ዜጎችም ሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውድድሮች ውስጥ ላሉ አካላት መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ያምናሉ።

ከአገር ውጭ በንደዚህ ዓይነት ውድድር ላይ ሲሳተፉ ስለገጠማቸው ተግዳሮት የጠየቅናቸው ዶ/ር ደራራ፤ "ሰው ዓላማ ላደረገው ነገር መጣር፣ መፍጨርጭር አለበት። አንዳንድ ሰዎች ቋንቋውን አንችልም የሚሉት ነገር አለ፤ እውነት ነው፤ ነገር ግን ሃሳብ ካላቸው ሃሳባቸውን ዳር ለማድረስ ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም" ሲሉ ይመልሳሉ።

ማንኛውም ሰው የተወለደበት ዓለማ አለው የሚሉት ዶ/ር ደራራ፤ ከአላማው ወደኋላ የሚመልሰውን ፍርሃት ጥሶ ማለፍ እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ በሚኖሩበት ከተማ እምብዛም ስለማይታወቁ የምረጡኝ ቅስቀሳ ለማድረግ ቤት ለቤት ለመዞር ተገደዋል።

"ሰው አያውቀኝም ብዬ፤ ወደ ኋላ አልመለስም" በማለት በጎ ሃሳብ በመያዛቸው እንደሚመረጡ ተስፋ ሰንቀዋል።

ከተመረጡ ምን ለመራት አሰበዋል?

"ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለስደተኞች ጥሩ አይደሉም" የሚሉት ዶ/ር ደራራ፤ የሚቀጥለውን ምርጫ ካሸነፉ በስደተኞች ላይ ትኩረት አድርገው ለመሥራት አልመዋል። ምክንያታቸው ደግሞ በአሜሪካ ስደተኞችን በተመለከተ እየወጡ ያሉ ሕጎች እየጎዷቸው ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው።

ዶ/ር ደራራ እንደሚሉት፤ ከመንግሥት የምግብም ሆነ ሌላ እርዳታ የሚያገኙ ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ እንዳያገኙ ሕጉ ይከለክላል። በዚህም ሳቢያ ስደተኞች ፈቃድ ለማግኘት ሲሉ ይህንን እርዳታ በመተው ለችግር ይጋለጣሉ።

ትራምፕ ኢትዮጵያውያን ላይ ተፅእኖ እያሳደሩ ነው?

በዓመቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች ጥቂቱ

"ካሸነፍኩ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች ጋር በመሆን ስደተኞች እንዲረዱ እሠራለሁ። በእርግጥ ይህንን አሁንም እየሠራሁ ነው ያለሁት" ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ለሚሠሩት ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ ለማያገኙ ሰዎች አቅማቸውን ያገናዘበ ቤት መግዛት እንዲችሉ ለማድረግ እንደሚሠሩም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የሌሎች አገራት ዜጎች እንግሊዘኛ ስለማይችሉ መንግሥት የሚሰጠውን አገልግሎት እያገኙ አይደሉም የሚሉት ዶ/ር ደራራ፤ እሳቸው ከተመረጡ ይህንን ችግር ሊያቃልሉ እንደሚችሉ ነግረውናል።

በከተማው ፖሊስ ውስጥና ከተማ አስተዳደር ውስጥ የኢትዮጵያዊያን ሥራ ላይ አይታዩም፤ በመሆኑም በእነዚህ የሥራ መስኮች ላይ ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉም እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።

የ39 ዓመቱ ዶ/ር ደራራ ወደፊትም የጆርጂያ ምክር ቤት አባል ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ