የሆንግ ኮንግ ሰልፈኞች ፕሬዝደንት ትራምፕ እባክዎ ይታደጉን እያሉ ነው

ተቃዋሚዎች Image copyright Reuters

ዲሞክራሲን የሚሹት ሰልፈኞች ፕሬዝደንት ትራምፕ 'ሆንግ ኮንግን ታደጉልን' ሲሉ በከተማዋ በሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ ጄነራል ጽ/ቤተ ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ።

አደባባይ የወጡት ሰልፈኞች የአሜሪካን ባንዲራ እያውለበለቡ "ፕሬዝደንት ትራምፕ እባክዎን ሆንግ ኮንግን ይታደጉ" እና "ሆንግ ኮንግን ወደ ቀድሞ ሃያልነቷ ይመልሱ" የሚሉ ጽሁፎችን አንግበው ነበር።

የሆንግ ኮንግ ፖሊስ፡ «ሰልፈኛ አስመስለን ፖሊስ አሰማርተናል»

የሆንግ ኮንጓ መሪ የተቃዋሚዎችን ድርጊት አወገዙ

በሚሊዮን የሚቆጠሩት እና ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡት ሰልፈኞች ከቻይና ጋር ያላቸው ቁርኝት እንዲያበቃ የሚሹ ናቸው።

የቀድሞዋ የእንግሊዝ ቀኝ ግዛት የሆነችው ሆንግ ኮንግ የቻይና አካል ስትሆን፤ ነዋሪዎቿም የዘረ ሃረጋቸው ከቻይና የሚመዘዝ ይሁን እንጂ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች እራሳቸውን እንደ "ቻናዊ" አይመለከቱም።

የሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ የዳሰሳ ጥናት እንዳመላከተው 71 በመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎች እራሳቸው እንደ ሆንግ ኮንግ ዜጋ እንጂ እንደ ቻይናዊ አይመለከቱም። እንደ ጥናቱ ውጤት ከሆነ በተለይ ወጣቱ "ቻይናዊ" በመባሉ ኩራት አይሰጠውም።

14ኛ ሳምንቱን በያዘው የተቃውሞ ሰልፍ፤ ቻይና ሌሎች ሃገራት በጉዳዩ ላይ እጃቸውን እንዳያስገቡ አስጠንቅቃለች።

ቻይና በተደጋጋሚ የሆንግ ኮንግ ጉዳይ የሃገር ውስጥ ጉዳይ መሆኑን እና ማናቸውም አይነት የውጪ ሃገራት ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት እንደማይኖረው አሳስባለች።

ዛሬ በተደረገው ሰልፍ አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ የተጠየቀ ሲሆን፤ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች የአሜሪካን ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር አሜሪካ ሆንግ ኮንግን ከቻይና 'ነጻ' እንድታወጣ ጠይቀዋል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ለተቃውሞ የወጡት ሰዎች የያዟቸው መልዕክቶች በቀጥታ ለፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የተላለፉ ነበሩ።

ሆንግ ኮንግ ተቃውሞ መነሾ ምንድነው?

በሆንግ ኮንግ ተቃውሞው የተጀመረው በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ከሆንግ ኮንግ ወደ ቻይና ተላልፈው እንዲሰጡ የሚያስችል ሕግ ተግባራዊ ሊደረግ መታሰቡን ተከትሎ ነበር።

ተቃውሞ በቻይና፡ መንግሥት 'የውጭ ኃይሎችን' እየወቀሰ ነው

ባህር አቋራጩ የቻይና ድልድይ ተከፈተ

ምንም እንኳ ሆንግ ኮንግ የቻይና አካል ብትሆንም፤ የቻይና እና የሆንግ ኮንግ የሕግ ስርዓት የተለያየ ነው።

ይህ ብዙ ያጨቃጨቀው ሕግ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ እንዲወድቅ ቢደረግም፤ የተቃዋሚዎች ጥያቄ መልኩን ቀይሮ አሁንም በሆንግ ኮንግ የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ናቸው።

በተቃውሞ ወቅት በቁጥጥር ሥር የዋሉት በምህረት እንዲለቀቁ እና በተቃውሞ ወቅት በፖሊስ ተፈጽመዋል የተባሉት የመብት ጥሰቶች እንዲመረመሩ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት እየጠየቁ ይገኛሉ።