በ2050 የወባ በሽታ ከዓለማችን ሊጠፋ ይችላል ተባለ

የወባ ትንኝ Image copyright Getty Images

ዓለማችን በ2050 ከወባ በሽታ ነጻ ልትሆን ትችላለች። በሰው ልጆች ታሪክ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረውና ሚሊየኖቸን የገደለው የወባ በሽታ በዚህ ትውልድ እድሜ ሊጠፋ እንደሚችል አንድ ጥናት ጠቆመ።

በየዓመቱ 200 ሚሊየን ሰዎች በወባ በሽታ የሚያዙ ሲሆን ብዙ ህጻናት ደግሞ በዚህ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።

የወባ በሽታ ያለ ደም ምርመራ ሊታወቅ ነው

አደገኛ የተባለ የወባ በሽታ በበርካታ ሀገራት ስጋት ፈጥሯል። በኢትዮጵያስ?

ሪፖርቱ እንደሚለው የወባ በሽታን ማጥፋት እንደ ድሮው የማይታሰብና የሩቅ ህልም አይደለም፤ ነገር ግን በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠርና ክትባት ለማግኘት በየዓመቱ የ2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያስፈልጋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የወባ በሽታን ከማጥፋት ጋር ሲነጻጸር የተጠቀሰው ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

የወባ በሽታ ከአራት የተለያዩ ፕላስሞድየም በሚባሉ የፓራሳይት ዓይነቶች የሚተላለፍ ከባድና ሞት አስከታይ በሽታ ነው። አራቱ ፓራሳይቶች፡ ፕላስሞድየም ፋልሲፓረም፣ ፕላስሞድየም ማላሪዬ፣ ፕላስሞድየም ኦቫሌ እና ፕላስሞድየም ቪቫክስ ናቸው።

በቅርብ ጊዜ የወጣ ሪፖርት በ68 የተለያዩ ሃገራት ያሉ የወባ ትንኞች በተለምዶ አገልግሎት ላይ ይውሉ የነበሩ አምስት መድሃኒቶች ተላምደው እንደማይሞቱ ይነግራል።

ከዚያም በተጨማሪ ፀረ-ወባ የሆኑ መድሃኒቶችም በልምምድ ምክንያት ሃይላቸው እየቀነሰ ነው።

ሪፖርቱ ምን አካቷል

የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ከሶስት ዓመት በፊት የጀመረው ይህ ጥናት በዓለማችን ከወባ በሽታ ጋር በተያያዘ አሉ የተባሉ 41 ተመራማሪዎችን ያካተተ ነበር። እነሱም ወባን የማጥፋት ስራ ምን ያክል ስኬታማ መሆን ይችላል እንዲሁም ምን ያክል ገንዘብ ፈሰስ መደረግ አለበት የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሲሰሩ ነበር።

በዚህም መሰረት እ.አ.አ. በ2050 ዓለማችን ከወባ በሽታ ነጻ መሆን እንደምትችል ተገልጿል። ሪፖርቱም በአይነቱ እጅግ የተለየ ነው እየተባለለት ነው።

በምርምር ስራው ተሳታፊ የነበሩት 'ሰር ሪቻርድ ፊቸም' እንደሚሉት ከዚህ በኋላ በሽታውን ማጥፋት እንደ ድሮው ከባድ አይደለም። '' በአንድ ትውልድ እድሜ በሽታውን ማጥፋት እንደምንችል አረጋግጠናል፤ ወሳኙ ነገር ቁርጠኛ ውሳኔ ነው'' ብለዋል።

Image copyright Getty Images

በአንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ስራው እልህ አስጨራሽ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። በተለይ ደግሞ በሰሜን ምዕራብ ከሴኔጋል እስከ ደቡብ ምስራቅ ሞዛምቢክ ድረስ ያለው ቀጠና እጅግ አስቸጋሪ ነው።

የወባ ትንኝ አደገኛ የሆነችው በሂደት ነው

ስለ እንቅልፍ የተሳሳቱ አመለካከቶች

በ2050 ወባን የማጥፋት ስራው አሁን በስራ ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ በመጠቀምና በመጪዎቹ ዓመታት አዳዲስ የመከላከያ ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ ማሳካት እንደሚቻል ባለሙያዎቹ ተናግዋል።

በሳይንሳዊ መንገድ ወባ አስተላላፊ የሆኑት ትንኞችን በማኮላሸት እንዳይራቡ በማድረግ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ጥናቱ ጠቁሟል።

በጥናቱ እንደተገመተው ወባን በ2050 ለማጥፋት ግን በአጠቃላይ የዓለም ሃገራት በየዓመቱ 2 ቢሊየን ዶላር መሰብሰብ መቻል አለባቸው። ይህን ያክል ገንዘብ በየዓመቱ ማግኘት እግጅ አስቸጋሪ እንደሆነ ብናውቅም ቁርጠኝነት ከተጨመረበት ማሳካት እንችላለን ብለዋል ተመራማሪዎቹ።