''ከአባቴ ጋር በተቃራኒ ጎራ ተዋግቻለሁ'' ታጋይ ዓለምጸሃይ

አለምጸሃይ Image copyright አለምጸሃይ
አጭር የምስል መግለጫ ዓለምጸሃይ

ጊዜው ኢትዮጵያ ከዘውዳዊው ሥርዓት ወደ ወታደራዊው የደርግ መንግስት የተሸጋገርችበት ወቅት ነው።

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እያቋረጡ ትክክል ነው ባሉት የፖለቲካ መስመር የከተማ እና የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱበት ጊዜ።

የአንድ ቤተሰብ አባላት በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ተሰልፈው እርስ በእርሳቸው የሚገዳደሉበት የታሪክ ምዕራፍም ነበር።

ሊገዳደሉ ከአንድ ጦር አውድማ የተገኙ ወንድማማቾች

ለ20 ዓመታት ዴንማርካዊት እህቱን የፈለገው ኢትዮጵያዊ ሀኪም

አለምጸሃይ ካሳ ሃይሉ ትባላለች። በትግራይ ክልል አድዋ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ዕዳጋ ዓርቢ ተወልዳ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምራለች።

ወደ ትግል ስትገባ የ14 ዓመት ልጅ እንደነበረች የምትናገረው አለምጸሃይ፤ በደርግ ስርዓት ይፈጸሙ የነበሩ ኢ-ፍትሀዊ ተግባራትና የህወሓት ታጋዮች ሰብዓዊ ባህሪ ገና በጨቅላ ዕድሜዬ ወደ ትግል እንድቀላቀል ምክንያት ሆኖኛል ትላለች።

ወደ ትግል ከመግባትዋ በፊትም የህወሓት ህቡዕ የከተማ አደረጃጀት አባል ሆና ትሰራ እንደነበር የምታስታውሰው አለምጸሃይ "ደርግ በአድዋ አካባቢ ሰዎች መግደል በመጀመሩ ፈጥኜ ወደ ትግሉ እንድቀላቀል አድርጎኛል" ትላለች።

ማይ ደጉዓለ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ወታደራዊ ስልጠና ወስዳ ወደ ሰራዊቱ ስትቀላቀል የ14 ዓመት ልጅ ብትሆንም "አካሌ ግዙፍ ስለነበር ጠመንጃ ታጥቄ ለመታገል ቀላል ነበር" በማለት ትውስታዋን አካፍላናለች።

ለሁለት የተከፈለው ቤተሰብ

የአለምጸሀይ ወላጅ አባትዋ አቶ ካሳ ሀይሉ ከአጼ ኃይለስላሴ ስርዓት ጀምሮ የወረዳ ጸሃፊ በመሆን ያገልግሉ ነበር። በትምህርቷም ጎበዝ እንድትሆን የላቀ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ታስታውሳለች።

የአጼው ስርአት ወድቆ ወታደራዊው መንግስት ስልጣን ከተቆናተጠጠ በኋላ አቶ ካሳ የደርግ አባል ሆነው ከህወሓት ጋር በሚደረገው ፍልሚያ ይሳተፉ ነበር።

በተቃራኒው የእሳቸው ባሌቤት "በህወሓት አይምጡብኝ'' ብለው የመጀመሪያ ልጃቸው አለምጸሃይ ከተሰለፈችበት ዓላማ ጎን በመቆም ደርግን ለመፋለም መርጠው ነበር።

ከአለምጸሃይ በተጨማሪ የአቶ ካሳ አራት ልጆች የታላቅ እህታቸውን ፈለግ በመከተል የህወሓት ትግልን ተቀላቅለው አባታቸው የሚደግፉትን የደርግ ስርዓት ለመዋጋት ወስነው ነበር።

በዚህ ምክንያት ቤተሰቡ ለሁለት ተከፍሎ እርስ በእራሱ እንዲዋጋ ግድ ሆነ።

እናት፤ ልጆቿ በአንድ በኩል፣ ባለቤቷ ደግሞ በሌላ በኩል ሆነው በጦር አውድማዎች ላይ የመገናኘታቸው ነገር ህሊናቸውን እርፍት ይነሳው ነበር።

ምናልባት ባለቤታቸው ሃሳባቸውን የሚቀይሩ ከሆነ ብለው ወይዘሮ ግደይ ተላ ወደ አቶ ካሳ የተማጽኖ ደብዳቤ ጻፉ።

እንዲህ ይላል፤ "ምናልባት 'የመንግሥት ስራ ጥዬ ከወጣሁኝ የገቢ ምንጭ ላይኖረኝ ይችላል' ብለህ ተጨንቀህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የምትታገልለት ዓላማ ጨቋኝ ከመሆኑ ባሻገር ከመጀመሪያ ልጃችን ጋር በጦር ሜዳ እንድትገናኙ ስለማልፈልግ እባክህን ሰራዊቱን ጥለህ አገርህ ግባ። ሌላው ቢቀር እኔ ሰርቼ አኖርሃለሁ።"

የወ/ሮ ግዳይ ተማጽእኖ ሳይሳካ ቀረ።

ወላጅ አባቷ ለደርግ ስርዓት ታማኝ ስለነበሩ በሃሳባቸው ሳይስማሙ መቅረታቸውን ዓለምጸሃይ ታስታውሳለች። ተስፋ ያልቆረጡት እናት በድጋሚ በልጃቸው አማካኝነት ሌላ ደብዳቤ እንዲጻፍለት ሃሳብ አቀረቡ።

Image copyright Alemtsehay
አጭር የምስል መግለጫ አለምጸሃይ [ከግራ ወደ ቀኝ ሁለተኛ] ከእያሱ በርሄ [ከግራ ወደ ቀኝ ሶስተኛ] ጋር በትጥቅ ትግል ወቅት።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ - ከሰኔ እስከ ሰኔ

"በአባልነት የምታገለግለው ስርዓት የልጆችህን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኝ እና የጸረ-ዲሞክራሲ አራማጆች ስብስብ ነው። የእኔ ወላጅ አባት ሆነህ የዚህ ጨቋኝ ስርዓት ታሪክ ተጋሪ መሆን የለብህም። ልጄ ተሳስታለች ብለህ ብታስብ እንኳ አባት በልጁ አይጨክንምና ከእኔ በተቃራኒ ሆነህ መዋጋት የለብህም" የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ እንደላከችለት ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ አለምጸሃይ አጭውታናለች።

ይሁን እና አቶ ካሳ ሀይሉ ደብዳቤው ቢደርሳቸውም የልጃቸውን ተማጽኖ እንደማይቀበሉ በጻፉት ደብዳቤ በመግለጽ ባለቤታቸውን ደግሞ 'ለምንድነው ልጅትዋን ወደ 'ወንበዴዎቹ' የላክሻት? አሁንም ሳይረፍድ መልሻት' የሚል መልዕክት እንዳስተላለፉ አለምጸሃይ ታስታውሳለች።

አቶ ካሳ ሀይሉ ከልጆቻቸው ጋር በተለያዩ ጎራዎች እየተፋለሙ 1974 ዓ/ም ደረሰ። ልጆቻቸው አለምጸሀይ ካሳ፣ ተስፋይ ካሳ፣ ኃይለኪሮስ ካሳ፣ ጸጋይ ካሳ እና ጽገወይኒ ካሳ በወቅቱ የለየላቸው የህወሓት ታጋዮች ሆነው ነበር።

360 ብር ለአንድ ሕጻን

ምንም እንኳ አባት ከመጀመሪያ ልጃቸው አለምጸሃይ ጋር ብቻ በአንድ የጦር አውድማ ላይ ቢፋጠጡም፤ ከሁሉም ልጆቻቸው ጋር ግን በዓላማ ልዩነት ታግለዋል።

አለምጸሃይ በተሳተፈችበት እና ዓዲ እምሩ በተባለው አከባቢ በተካሄደው ውጊያ አቶ ካሳ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ የቆሰሉ የደርግ የሰራዊት አባላትን ይዘው ወደ ሽረ እንዳስላሰ እንዳፈገፈጉ አለምጻሃይ ትናገራለች።

በ1974 ዓ.ም. ግን የደርግ ሰራዊት እና የህወሓት ታጋዮች በፈረስ ማይ አውድማ ሲዋጉ ውለው በስተመጨረሻ የአለምጸሀይ አባት፣ አቶ ካሳ ሀይሉ በጓዶችዋ አማካኝነት ተማረኩ።

የህወሓት ታጋዮች በውግያው የታጋይ ልጆች አባት መሆናቸውን ተገንዝበው በስነ ስርአት እጅ እንዲሰጡ ቢማጸኗቸውም በሃሳቡ ስላልተስማሙ ከጉልበታቸው በታች መትተው እንደማረኳቸው አለምጸሃይ ታወሳለች። በመጨረሻ ግን በምርኮኝነት ከቆዩ በኋላ ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ህይወታቸው አልፏል።

Image copyright አለምጸሃይ
አጭር የምስል መግለጫ አቶ ካሳ ሀይሉ

ወላጅ አባትሽ ተማርኮ ህይወቱ ማለፉን ስትሰሚ ምን ተሰማሽ? ለአለምጸሃይ ያቀረብንላት ጥያቄ ነበር።

"በታሪክ ተጠያቂ ከሆነ ስርአት ጋር ወግኖ፤ እስከ መጨረሻ በተደረጉ ውግያዎች ተዋግቶ ህይወቱ ማለፉን ስሰማ ከልቤ ነው ያዘንኩት" የምትለው አለምጸሀይ "እኛ ቤተሰቦቹ እና ድርጅቴ ህወሓት ለማድረግ ያሰብነው ነገር ሳይሳካልን ቀርቶ መጨረሻው እንዲህ መሆኑ አሳዝኖኛል" በማለት በሁኔታው እጅግ ሀዘን እንደተሰማት ገልጻለች።

ወላጅ አባትዋ በትምህርትዋ ጎበዝ እንድትሆን የነበራቸው አስተዋጽኦ በማስታወስ [እምባ እየተናነቃት] "በምንም መተከያ የሌለው ውድ አባቴን እኮ በጣም እወደዋለሁ፤ እሱ በህይወት ቢኖር ትግላችን ፍሬ አፍርቶ አዲስ ስርዓት አብረን እንድንገነባ ነበር ምኞቴ።"

"በኤችአይቪ የምሞት መስሎኝ ልጄን ለጉዲፈቻ ሰጠሁ"

የጄኔራል ደምሴ ቡልቶ ልጅ 'መራር' ትዝታ

ሁለቱ የአቶ ካሳ ልጆች ተስፋይ ካሳ እና ጽገወይኒ ካሳ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በተለያዩ ጊዜዎች በተደረጉ ውግያዎች ህይታቸው አልፏል።

የትግል ጓዶቿ እና የቅርብ አመራሮች ብዙ ግዜ "የነጭ ለባሽ ልጅ፣ ነጭ ለባሹ አባትሽን በእጅሽ ነው መማረክ ያለብሽ" ብለው ይቀልዱባት እንደነበር የምታስታውሰው አለምጸሀይ አባት በልጃቸው ተማርከው በትግሉ ግዜ ታሪክ ይሰራል ብለው ያስቡም እንደነበር ነግራናለች።

"ይሁን እንጂ በእጄ ልማርከው ባይሳካልኝም ሁለታችንም ላመንበት ዓላማ ታግለን እኔ የታገልኩበት አላማ በማሸነፉ ሁሌም የምደሰትበት የህይወቴ ምዕራፍ ነው።"

ታጋይ አለምጸሀይ ካሳ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ረዳት ኮምሽነር በመሆን እያገለገለች ሲሆን የሁለት ሴት ልጆች እናት ነች።

ተያያዥ ርዕሶች