በስህተት ገቢ የተደረገላቸውን 3 ሚሊዮን ገደማ ብር የተጠቀሙት ጥንዶች ክስ ተመሰረተባቸው

Stock image of person retrieving money from ATM Image copyright Getty Images

በባንክ በተፈጠረ ስህተት ምከንያት አካውንታቸው ላይ ገቢ የተደረገውን ገንዘብ ወጪ ያደረጉት ጥንዶች በስርቆት ክስ ተመሰረተባቸው።

ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ፔንስሎቬኒያ ግዛት የሆነው ሮበርት እና ቲፋኒ ዊሊያምስ የተባሉት ጥንዶች 120 ሺህ ዶላር (3.4 ሚሊዮን ብር ገደማ) በባንክ ስህተት አካውንታቸው ውስጥ ገቢ ከተደረገ በኋላ ጥንዶቹ ገንዘቡን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ አውጥተውታል።

ቅንጡ መኪና ጭምር የገዙት ጥንዶቹ አሁን ላይ ከ100ሺህ ዶላር በላይ ዕዳ ተቆልሎባቸዋል።

በስህተት የተሰጣቸውን 1 ሚሊየን ብር የመለሱት መምህር

ጥንዶቹ ለፍርድ ቤት በሰጡት ቃል ገንዘቡ የእነርሱ አለመሆኑን እያወቁ ወጪ አድርገውታል። በዋስ የተለቀቁት የ36 እና የ35 ዓመት ጥንዶች፤ በስርቆት እና የተሰረቀ ንብረት መቀበል የሚሉ ክሶች ተመስርተውባቸዋል።

ቢቢ ኤንድ ቲ የሚባለው ባንክ ግንቦት 23 ላይ ለአንድ የኢንቨስትመንት ኩባንያ መላክ የነበረበትን ገንዘብ በስህተት ወደ ጥንዶቹ አካውንት ገቢ አድርጎላቸዋል ሲሉ የፖሊስ ባልደረባው አሮን ብራወን ተናግረዋል።

''ከአባቴ ጋር በተቃራኒ ጎራ ተዋግቻለሁ'' ታጋይ ዓለምጸሃይ

የባንኩ የሂሳብ ባለሙያዎች ስህተት እንደተፈጸመ ሰኔ 13 ላይ ቢረዱም፤ ጥንዶቹ ስህተቱን ለባንኩ ሳያሳውቁ በ20 ቀናት ልዩነት ውስጥ 107ሺህ ዶላር ወጪ አድረገዋል።

ጥንዶቹ፤ በ20 ቀናት ውስጥ ሼቭሮሌት ቅንጡ መኪና፣ ኩሽና፣ ሽንት ቤት እና የመኝታ ቦታ ያለው የሽርሽር መኪና፣ ሁለት ባለ አራት ጎማ ሞተር፣ የውድድር መኪና እና የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎችን ከመግዛታቸውም በተጨማሪ፤ ለተቸገሩ ጓደኞቻቸው 15ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሰጥተዋል።

የፖሊስ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ ጥንዶቹ ከባንኩ ገንዘብ እንዲመልሱ ጥሪ ሲቀርብላቸው፤ ገንዘቡን ሙሉ ለሙሉ ወጪ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

''ቲፋኒ ዊሊያምስ ለባንኩ ባለቤቷ አብዛኛውን መጠን ወጪ ማድረጉን ካሳወቀች በኋላ፤ ከባለቤቷ ጋር ተመካክራ ገንዘቡን መልሰው የሚከፍሉበት የክፍያ አማራጭ እንደሚያጤኑ ተናግራ ነበር" ብለዋል የፖሊስ ባልደረባው አሮን ብራዎን።

በጋምቤላ የተራድኦ ድርጅት ሰራተኞችን በመግደል የተጠረጠሩ አለመያዛቸው ተገለፀ

ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ባንኩ ጥንዶቹን ማግኘት አልቻለም ነበር። ገንዘቡ ወደ ጥንዶቹ ሂሳብ ቁጥር ገቢ ከመደረጉ በፊት በጥንዶቹ ሂሳብ ቁጥር ውስጥ የነበረው ከ1ሺህ ዶላር ያነሰ ገንዘብ ነበር።