የጀማል ኻሾግጂ አገዳደል በዝርዝር ይፋ ሆነ

ጀማል ካሾግጂ Image copyright Reuters

ቱርክ ውስጥ የሚገኝ አንድ ጋዜጣ ሳኡዲ አረቢያዊው ጃማል ኻሾግጂ ከመገደሉ በፊት የነበሩትን የመጨረሻ ሰዓታትና አገዳደሉን በዝርዝር የሚገልጽ መረጃ ይዞ ወጥቷል።

ጋዜጠኛ ጃማል ኻሾግጂ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ነበር ኢስታንቡል በሚገኘው የሳኡዲ አረቢያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ውስጥ የተገደለው።

ከቱርክ መንግስት ጋር ግንኙነት ያለው ይህ ጋዜጣ እንዳስታወቀው በእጄ ገባ ያለው መረጃ ጃማል ከመገደሉ በፊትና አገዳደሉን የሚገልጽ የድምጽ ማስረጃ ሲሆን የቱርክ ደህንነት አባላት ነበሩ መጀመሪያ ላይ ያገኙት።

«ካሾግጂ ወዲያው ነበር የታነቀው» ቱርክ

ስለ ጀማል ኻሾግጂ አሟሟት እስካሁን የምናውቃቸው እውነታዎች

ጋዜጣው ላይ የወጣው መረጃ ጋዜጠኛው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ምን እንደተናገረ ጭምር ይገልጻል።

ኻሾግጂ ድንገት ከመሰወሩ በፊት አሜሪካ ውስጥ ሆኖ ዋሽንግተን ፖስት ለተባለው ጋዜጣ ይጽፍ ነበር። በጽሁፎቹም ሳኡዲ አረቢያ መንግስት ይፈጽማቸዋል ስለሚላቸው በደሎች በተደጋጋሚ ይጽፍ ነበር።

ባሳለፍነው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ነበር ኻሾግጂ ቱርክ፥ ኢስታንቡል ውስጥ ወደሚገኘው የሳኡዲ አረቢያ ቆንስላ ጎራ ያለው እጮኛውን ለማግባት የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ለማግኘት ነበር።

ነገር ግን ያላሰበው ነገር አጋጥሞት ከቅጥር ግቢው ሳይወጣ ቀርቷል።

በቆንስላው ውስጥ የተገደለው ኻሾግጂ፣ ወደ ቅጥር ግቢው እንደገባ ነበር የታነቀው ስትል በወቅቱ ቱርክ መግለጫ ሰጥታ ነበር። ከዚያም የጋዜጠኛው በድን አካል ተቆራርጦ እንዲጠፋ ተደርጓል። ይሁ ሁሉ የተከናወነው ቀድሞ በተፃፈ ስክሪፕት መሠረት ነው።

ሳባህ የተባለው ጋዜጣ ከኻሾግጂ ሞት ጋር በተያያዘ ሁለት ዘገባዎችን ይዞ የወጣ ሲሆን የዓለም መገናኛ ብዙሃንን ቀልብ መግዛት ችሏል።

ጋዜጣው እንደሚያትተው ቀድመው የተዘጋጁ ነፍሰ ገዳዮች በቅጥር ግቢው እየተጠባበቁ ነበር። ኻሾግጂ ልክ ወደ ቆንፅላው ቅጥር ግቢ ሲገባ በእነዚህ ግለሰቦች ነው ታንቆ የተገደለው።

እንደ ማስረጃም ጋዜጣው የተለያዩ የፖሊስ ምርመራ ውጤቶችን፣ ከሳኡዲ አረቢያ የመጣ የመርማሪዎች ቡድን አገኘሁት ያለውን መረጃ፣ እንዲሁም ሌሎች አባሪ ሰነዶችን ተጠቅሜያለው ብሏል።

የሳዑዲው ጋዜጠኛ ለመገደሉ ቱርክ አሳማኝ ማስረጃ እንድታቀርብ አሜሪካ ጠየቀች

ኻሾግጂ ወደ ቆንስላው እንደገባ ሁኔታው ስላላማረው ለመመለስ ቢሞክርም በዓለማቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል ስለሚፈለግ ወደ ሳኡዲ አረቢያ መመለስ እንዳለበት ተነግሮት ነበር።

በሃሳቡ ያልተስማማው ኻሾግጂ ስለሁኔታው ለወንድ ልጁ የጽሁፍ መልእክት ልኮ ነበር። ከዚህ በኋላ ነበር እየተጎተተ ወደ አንድ ክፍል ውስጥ የተወሰደው።

ለገዳዮቹም እባካችሁ አፌን አትሸፍኑኝ፤ የአተነፋፈስ ችግር አለብኝ ቢላቸውም ሊሰሙት ፈቃደኛ አልነበሩም። ልክ አፉን እንደሸፈኑት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ራሱን ስቷል።

ተገኘ በተባለው የድምጽ ቅጂ መሰረት ከጭንቅላቱ እስከ አንገቱ ድረስ አየር በማያስገባ ጭንብል እንዲሸፈን ተደርጓል። ህይወቱ ካለፈ በኋላም የጋዜጠኛው በድን አካል ተቆራርጦ እንዲጠፋ ተደርጓል።

ምንም እንኳን ኻሾግጂ ኢስታንቡል የሳኡዲ አረቢያ ቆንስላ ውስጥ መገደሉ ቢረጋገጥም እስካሁን ድረስ ሬሳው እምጥ ይገባ ስምጥ አይታወቅም።

ተያያዥ ርዕሶች