"ፍቅር እስከ መቃብርን አልረሳውም" ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም

በግራ ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) እና ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም
አጭር የምስል መግለጫ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም

በ2010 ዓ. ም. የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፤ በትግራይ ክልል ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ባሉ የተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ ከ1995 ዓ. ም. ጀምሮ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል።

በህወሐት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ካሉት ጥቂት ሴቶች አንዷ ሲሆኑ፤የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ከመሾማቸው በፊት የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የደቡብ ምሥራቅ ዞን አስተዳዳሪ፣ የትግራይ ክልል የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም በፓርቲያቸው ውስጥም የገጠር ዘርፍ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።

አስመራ የተወለዱት ወ/ሮ ኬሪያ፤ በትምህርት ዝግጅታቸውም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኢንቫይሮሜንታል አንትሮፖሎጂ ሰርተዋል።

ቢቢሲ አማርኛ በዓሉን ምክንያት በማድረግ አፈ ጉባኤዋ እንዴት ነው የሚያሳልፉት? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች አንስተንላቸዋል።

ከነፍስ የተጠለሉ የዘሪቱ ከበደ ዜማዎች

በዓላትን እንዴት ያሳልፋሉ?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ በዓል ለሴትና ለወንድ አንድ አይደለም። በተለይ በከፍተኛ ደረጃ አመራር ላይ ስትደርሺ ያው መቼም ሥራ አቋርጠሽ የቤት፣ የበዓል ላዘጋጅ አትይም። ነገር ግን ሁለቱንም አደራርበን ነው የምንሠራው። ስለዚህ የቤቱም እንዲሟላ የእረፍት ሰአትሽን፣ የመኝታ ጊዜሽን ዋጋ የምትከፍይበት ጊዜ አለ። የቤቱንም ሆነ የሥራም ደግሞ እንዳይደናቀፍ በተሟላ መልኩ የመምራት ኃላፊነት አለ። ሁለቱንም በሚያቀናጅና በሚያስማማ መንገድ መሆን አለበት።

በተለይ አዲስ ዓመትን ለየት ባለ መንፈስ፣ አስተሳሰብ እና ዝግጅት ለሥራ ብቻ ሳይሆን ለሕይወትም፣ ለቤትም፤ እንዴት እንደምትመሪው የምታቅጅው፤ ሁለቱንም የቤትና አደባባይ አቀናጅተሽ በአዲስ መንፈስ የምትቀበይው በዓል ነው።

የሼፎች የበዓል ምግብ ምርጫ፡ ሼፍ ዮሐንስ፣ ጆርዳና እና ዮናስ

"ሰዓረ ሙዚቃ በጣም ያዝናናው ነበር" ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ

ስለዚህ በተለይ የዘንድሮው አዲስ ዓመት ደግሞ በአገራችን ላይ የሚታዩ ብዙ ነገሮችም ስላሉ እነዚህን አዳጋች ነገሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል፤ የተሻለ ነገር እንዴት መሥራት እንዳለብን ከወዲሁ በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ አሰራር፤ አገራችን፣ ሕዝባችን ሰላም እንዲሆን፤ የተረጋጋ ኑሮና ሕይወት እንዲመራም ጭምር የምታስቢበት ነው፤ በዛ በደስታ ውስጥ ሆነሽ ማለት ነው።

በዓል ላይ ምን ያደርጋሉ፤ ቤት ውስጥ እንዴት ነው የሚያሳልፉት?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ አንዳንድ ሰዎችን ምን ትታዘቢያለሽ? ወደ ከፍተኛ አመራር ስትደርሺ ቤትሽ ገብተሽ ምንም እቃ እንደማታነሺ አድርገው የሚወስዱ አሉ። ነገር ግን እውነታው ሌላ ነው። ለሴት ልጅ በተለይ በኛ አስተዳደግ፣ በባህሉም፣ በእሳቤውም ብዙ ያልተቀረፉ ችግሮች አሉ።

ስለዚህ ሴት ልጅ ከፍተኛ አመራርም ትድረስ የትኛውም ቦታ ላይ ብትሆን ቤት ስትገባ የሚጠበቅባት የቤት ውስጥ አገልግሎቶች አሉ። የግድ ወደቤቷ፣ ወደጓሮ መግባቷ አይቀርም። ምንም እንኳን የቤት ሠራተኛ ቢኖርም፤ ያው ምን እንደተዘጋጀ፣ እንደጎደለ፣ ምን እንደተሟላ አያለሁ። ማገዝ የሚያስፈልጉና መስተካከል የሚያስፈልጉ ነገሮችን ታስተካክያለሽ።

''አባቴ የቼልሲ ደጋፊ ነበር'' የሜጄር ጄኔራል ገዛዒ አበራ ልጅ

ልጆችም፣ ባለቤትም አለ። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በቤትም ጭምር ተጨማሪ ሰዓት የምትሠሪው አለ፣ ተጨማሪ የምትከፍይው ጊዜና የምትከፍይው ጉልበት አለ፤ ለየት ያለ ለሴት።

ወንድ ግን ዞሮ ዞሮ ቤት የተሠራለትን ቁጭ ብሎ የሚጠብቅ ነው። ምናልባት የአሁኑ ትውልድ የሚያግዙ ወንዶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለኛ ግን በቤትም ጭምር ትልቅ ኃላፊነት ነው የተጣለብን። በተለይ በበዓል ለሴት ልጅ ተጨማሪ ሥራው ከፍተኛ ነው።

የተለያዩ ክብረ በዓላት አሉ። ለርስዎ ለየት ያለው የትኛው ነው?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ ከእምነት ጋር ከተያያዘ ያው አረፋና ኢድ አልፈጥር ነው። ግን ከባህላችንና ከአገራችን ከሆነ አዲስ ዓመት ደስ ይለኛል። አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ አስተሳሰብ ከሁሉም ሕዝብ ጋር በጋራና በደስታ የምንቀበለው ስለሆነና የዘመን መለወጫም ስለሆነ እሱም ትልቅ በዓል ነው።

በዓል ሲነሳ ብዙ ጊዜ የሚነሳው ምግብ ነው እና እርስዎ የሚወዱት ምግብ አለ? በአጠቃላይ የሚወዱት ምግብ ምንድን ነው?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ እኔ አብዛኛውን ጊዜ ምግብ አልመርጥም፤ ከሁሉም በላይ የምወደው ምግብ ግን ሩዝ በስጋ ነው። ባህላዊ፣ የተለመደ ምግባችን ሽሮም እወዳለሁ። በተለይ ከመጀመሪያው ተመጥኖ፣ ቅመም ገብቶበት፣ በደንብ በስሎ፣ የተከሸነ ሽሮ በጣም ነው የምወደው። ሁሉንም ምግብ እሠራለሁ፤ እችላለሁ ያው ሴት ልጅ የምትችለውን (ሳቅ)

ከበዓል ምግብስ የሚወዱት?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ ከበዓል ምግብ ዶሮ ነው የምወደው። በዓል ሲመጣ ከሁሉም በፊት ቀድማ የምትሠራው ዶሮ ናት። ለሴት ልጅ ያው ጣጣዋ ብዙ ነው። ዶሮ ለመሥራት ትንሽ ጉልበትና ጊዜ ትፈልጋለች። ያው በበዓል ላይ ዶሮ፣ ብርዝ፣ አብሽ የሚባልም አለ (በተለይ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ)፤ እነዚህ ጊዜ የሚፈልጉና አስቀድመሽ የምትሠሪያቸው ናቸው።

መከላከያ የሶሪያ እና የየመን ዜጋ የሆኑ የአይኤስ አባላትን በቁጥጥር ሥር አዋልኩ አለ

ድፎ ዳቦና ሁሉም ነገር እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። በበአሉ ጊዜ ደግሞ ቄጠማውም፣ ፈንዲሻውም፣ ከረሜላውም፣ ብስኩቱም ይዘጋጃል። ይሄ ሁሉ ሲሟላ ነው በአል፣ በአል የሚሸተው።

በትርፍ ጊዜዎ ምን ያደርጋሉ? ፊልም ያያሉ? ሙዚቃ ያዳምጣሉ?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ ሙዚቃ ያንን ያህል አላዳምጥም። ድሮ ብዙ ሙዚቃዎችን አደምጥ ነበር። በአሁኑ ሰአት የማዳምጥበት ጊዜ የለም (ሳቅ)፤ ድሮ ግን የአስቴር አወቀን ሙዚቃ አዳምጥ ነበር። በአሁኑ ሰአት የተወሰኑ ፊልሞች አያለሁ። በርግጥ እያቆራረጥኩ ነው የማየው።

ጽሐፍ ያነባሉ? አሁን እያነበቡት ያለ መጽሐፍ አለ?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ መጽሐፍ አነባለሁ። አብዛኛውን ጊዜ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው የማነበው፤ በአገር ውስጥ የሚታተሙትን እንዲሁም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያዘጋጃቸው የነበሩ ፅሁፎችን አነባለሁ። ሌላው ደግሞ ከአገራችን ተመሳሳይ ሥርአት ያላቸው አገራት የሚከተሉትን ርዕዮተ ዓለም አነባለሁ። በተለይም ከፌደራሊዝም ሥርአት ጋር ተያይዞ የማነባቸው አንዳንድ ፅሁፎች አሉ።

2011፡ በፖለቲካና ምጣኔ ኃብት

በዓመቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች ጥቂቱ

ለመዝናናት ልብወለድ አያነቡም?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ 'ፊክሽን' ድሮ አነብ ነበር (ሳቅ)፤ በተለይ ድሮ ትምህርት ጨርሰን ክረምት ላይ ሲሆን ብዙ ልብወለዶች አነብ ነበር።

ካነበቡት ልብወለድ መፅሀፎች የማይረሱት አለ?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ ያው 'ፍቅር እስከ መቃብር' ን አልረሳውም (ሳቅ) በአንድ ጊዜ ጀምሬ ሳላቋርጥ የጨረስኩት ነው። እሱን ነው በብዛት የማልረሳው

ያዘኑበትና የተደሰቱበት የሚያስታውሱት ቀን አለ?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ አለ ግን...ይኼ እንኳን ቢቀር ይሻለኛል።

መጀመሪያ ከእንቅልፍዎ ሲነሱ ወይም ሲተኙ የሚያደርጉት ተመሳሳይ ነገር አለ?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ ከአልጋየ ተነስቸ መጀመሪያ ሁልጊዜም እሰግዳለሁ። ማምሸት እወዳለሁ፤ እና ስተኛም የማነበውን ነገር አንብቤ ነው የምተኛው፤

የሚወዱት ጥቅስ አለ? ሁልጊዜም ከህሊናዎ የማይጠፋ? ወይም እንደ ይወት መርህ የሚጠቀሙበት?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ አለ! በትግርኛ ስለሆነ፤ በአማርኛ ሲተረጎም ትርጉሙን ሊያጣ ይችላል።

ለበዓሉ ምን መልዕክት አለዎት? ለኢትዮጵያ ዝብስ ምን ይመኛሉ?

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡ ያው በዓሉን በተለያየ መንገድ ነው የምናከብረው፤ በተለይ የአሁኑን በአል ከወትሮው ለየት የሚያደርገው በሕዝቦች መካከል የነበረው አብሮነት፣ መቻቻልና መከባበር፣ መፈቃቀርና መደጋገፍ ትንሽ የላላበት ጊዜ ባለበት ነው የምናከብረው።

ትልቁ ነገር አገራችን የልማት፣ የሰላም ተምሳሌት፣ የዕድገትና የብልፅግና ተምሳሌት የምትሆነው በሕዝቦቿ ላይ ያለው አንድነት፣ መቻቻልና መከባበር ሲጠነክር ነው።

ያለፈውን ብዙ ችግሮቻችን እንዳሉ ትተን ለሚቀጥለው ለ2012 ዓ. ም. የሰላም፣ የብልፅግናና የእድገት እንዲሆንልን እመኛለሁ።

አገራችን ብዙ ችግሮች እንዲሁም እድሎች አሉ። እድሎቻችንን በደንብ አስፍተን መጠቀም፤ በተለይ ከሚለያዩን አንድ የሚያደርጉንን ትኩረት አድርገን፤ የሕዝቦች አንድነት የሚጠናከርበት፤ ሁላችንም የየራሳችንን ድርሻ መወጣት አለብን። ሰላም የሚፈጠረው በእያንዳንዱ ዜጋ ሰላም በሥነ ልቦናው፣ በአእምሮው ሲፈጠር ነው።

ሁላችንም በሥነ ልቦናና በአዕምሯችን ሰላም ፈጥረን ከሌሎች ጋርም ሰላም ሆነን አገራችን የሰላምና የእድገት ተምሳሌት እንድትሆን ሁላችንም መጣር እንዳለብን ቃል የምንገባበት መሆን አለበት።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ