"ስተዳደር የቆየሁት በዋናነት ለመለስ በሚሰጠው የጡረታ ገቢ ብቻ ነው" ወ/ሮ አዜብ መስፍን

የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን Image copyright AFP

ወ/ሮ አዜብ መስፍን የሕወሓት ነባር ታጋይና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ናቸው። ቀዳማዊ እመቤት በነበሩበት ወቅት የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ማኅበር (ትዕምት ወይም ኤፈርት) መሪ ነበሩ። ወ/ሮ አዜብ፤ የባለቤታቸው መታሰቢያ የሆነው የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሰብሳቢም ናቸው።

ቀዳማዊ እመቤት በነበሩበት ወቅት፤ በአዕምሮ ህሙማን ዙሪያ የሠሩትን ሥራ በጣም እንደሚኮሩበት ይናገራሉ። በተለያየ ዘርፍ ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ያከናወኗቸው በርካታ ሥራዎች ስለመኖራቸውም ያስታውሳሉ። በኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን የተቋቋመው "የጉልት ማዕከል" የተባለውን ሃሳብ ከማመንጨት ጀምሮ እስከመጨረሻው መሳተፋቸውን እንደ አብነት ያነሳሉ። ["የጉልት ማዕከል" በጎዳና የንግድ ሥራ የተሠማሩ ሴቶች የሚደገፉበት ፕሮጀክት ነው።]

ታዲያ በዚህ ጊዜ ዋናውና መደበኛ ሥራቸው በፓርቲው የሚሰጣቸውን ሥራ መሥራት ነበር። "ራሴን የምወቅስበት ሥራ ሳልሠራ እና ጥሩ ሥራ ሰርቼ ከፓርቲው መውጣቴን እኮራበታለሁ፤ ሰው የፈለገውን ቢል" ይላሉ።

"ሕገ-መንግሥቱ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትርን በሚመለከት ክፍተት አለበት" ውብሸት ሙላት

'ደብረፅዮን'፣ 'ጌታቸው አሰፋ'...ከዘንድሮው አሸንዳ አልባሳት ስሞች መካከል

ድህነትን በመታገል ረገድ በርካታ ሥራዎችን እንዳከናወኑም ይናገራሉ። "ለሕዝብ ይጠቅማሉ ብዬ የተንቀሳቀስኩባቸው ሥራዎች ጥሩ ናቸው ብዬ አምንባቸዋለሁ" ሲሉ ያክላሉ።

ባለቤታቸው፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ባሳለፍነው ነሐሴ ወር ሰባት ዓመት ሞልቷቸዋል።

ለመሆኑ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ባለፉት ዓመታት ምን ሲሠሩ ቆዩ? አሁንስ በምን ሥራ ላይ ነው ያሉት?

አዲስ ዓመትን አስመልክተን ከብዙሃን መገናኛ የጠፉትን ስንፈልግ፣ ስናስፈልግ ካገኘናቸውና ለቃለ መጠይቅ ፈቃደኛ ከሆኑት ከወ/ሮ አዜብ ጋር ጥቂት ተጨዋውተናል. . .

እንኳን አደረሰዎት ወ/ሮ አዜብ

እንኳን አብሮ አደረሰን።

አሁን የት ነው የሚኖሩት? ተቀማጭነትዎ የት ነው?

ብዙ ሰዎች አዲስ አበባ የለችም ይላሉ። ግን አዲስ አበባ ነው ያለሁት- አንዳንዴ ገባ ወጣ ከማለቴ ውጭ።

ባለቤትዎን የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስን በሞት ካጡ በኋላ ቤተ መንግት የሄዱበት አጋጣሚ አለ?

[ፋታ]. . . ብዙ ጊዜ አልሄድም። የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ሁለት ቀን የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ሄጃለሁ። ያው ስብሰባው እዚያው ግቢ ውስጥ ስለነበር። ከዛ ውጭ ግን አልሄድኩም፤ መሄድም አልፈልግም።

በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ አስተዳደር ጊዜ ማለት ነው?

አዎ! በቅርቡ አንድ ጊዜ የሄድኩ ይመስለኛል። በስብሰባዎች ምክንያት ስሄድ ነበር፤ ነገር ግን ብዙም አልሄድኩበትም።

ቤተ መንግ ከልጆችዎከቤተሰብዎ ጋር ለረም ዓመታት የኖሩበት ነውና አይናፍቅዎትም?

እ. . . [ዝምታ] በዚያ ሳልፍ እንኳን ምንም ስሜት አይሰማኝም። ምክንያቱም አወጣጤ ላይ. . . መለስን ቀብሬ ነው የወጣሁት። እና ደግሞ ቤተ መንግሥትን እንደ ታጋዮች ነው የኖርንበት። የሥራ ድርሻ ተሰጥቶን ነው የኖርንበት።

ከቤተ መንግሥት ስንወጣ መለስን ቀብሬ እወጣለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ሁለታችን አብረን የምንወጣበትና እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነፃ ሆነን ተንቀሳቅሰን የምንኖርበትን ጊዜ እመኝ ነበር። እኔ ብንቀሳቀስም፤ መለስ ግን የመንቀሳቀስ እድል አላገኘም ነበር።

እዚያው እንደታሰረ፣ እዚያው ቀብሬው መውጣቴ ይሰማኛል [ሳግ በተናነቀው ድምፅ]. . . ከቤተ መንግሥት ይልቅ ሥላሴ [ቤተ ክርስቲያን] ስገባ በጣም ይሰማኛል። እና. . . ቤተ መንግሥትን ሳይ፤ መለስን ቀብሬ የተመለስኩበትን ሰዓት ብቻ ነው የማስታውሰው። አስክሬኑን ይዤ የወጣሁበትን ደቂቃዎች ብቻ ነው የማስታውሰው። ሌላው በሙሉ ለምን እንደሆነ አይገባኝም. . . ትዝ አይለኝም።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈትን ተከትሎ፤ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ

ጩኸቱ. . . አስክሬኑ ሲወጣ፤ አስክሬን ይዤ ስገባ. . . ድንጋጤው። መጨረሻ ደግሞ ስንወጣም፤ አወጣጣችን ራሱ ትልቅ ችግር ነበረው። እ. . . እሱም የራሱ ድርሻ አለው መሰለኝ፤ ላለማስታወሴ። የማስታውሰው ግን ይኼኛው ነው። የቀብር ቀኑን፣ ከቀብሩ ስንመለስ፣ አስክሬኑን ይዘን ስንገባ. . .

ባለቤትዎ በሞት ከተለዩ ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል። እስካሁን ምን ሲሩ ነው የቆዩት?

እንደሚታወቀው በፓርቲ ሥራ ላይ አይደለም ያለሁት። ለእኔና ለልጆቼ የሚያስተዳድሩንን ሥራዎች ለማስተካከል ደፋ ቀና ስል ነው የቆሁት። በተጨማሪ ዋናው ሥራዬ የባለቤቴን ሥራዎች ለማስቀጠል፣ ፅሁፎቹን ለማሳተም የሚያስችለኝን አጠቃላይ ዶክመንቶቹን በማዘጋጀት ላይ ነበርኩ። እርሱም ተጠቃሏል።

ታዲያ ለግልዎ መተዳሪያ የሚሆን ምን ሥራ አገኙ?

በንግድ ዘርፍ ለመግባት እያሰብኩ ነው። እንዴት እንደምሠራ፣ መነሻ ገንዘቡን እንዴት እንደማገኝ ወይ ከሰዎች ጋር ሆኖ. . . እስካሁን የተለያየ ድርጅትን ለማማከር. . . ፓርቲው የንግድ ሥራ ላይ አሰማርቶኝ ስለቆየሁ እኔን የሚመለከት ምንም አልነበረም።

ለሕዝብ ነው የሠራሁት። ለሕዝብ አስረክቤ. . . ይረከባሉ ለተባሉ ሰዎች አስረክቤ፤ ባዶ እጄን ነው የወጣሁት። ስተዳደር የቆሁት በዋናነት ለመለስ በሚሰጠው የጡረታ ገቢ ነው። እና ከቤተሰብ፣ ከዛም ከዛም. . . ከአሁን በኋላ ግን የራሴን ሥራዎች መሥራት እፈልጋለሁ።

አልፎ አልፎ ከተለያዩ ትልልቅ ድርጅቶች ጋር ለማማከርም ከእነርሱ ጋር ለመሥራትም የሞካከርኳቸው እዚያም እዚህም አሉ. . . ከተሳኩልኝ አንዳንድ ነገሮች ለመጀመር ፍላጎትና ዝግጁነት አለኝ።

የባለቤትዎ የጡረታ ገንዘብ ምን ያህል ነው?

በወር አስራ አራት ሺህ ብር ገደማ መሰለኝ።

በትዳር ስንት መት ነው የቆዩት

ኦው. . . ሕወሓት ሠርግ ከፈቀደ ጀምሮ እስከ መስዋዕቱ ድረስ አብረን ነበርን። 25/26 ዓመታት። ሦስት ልጆች አሉን። አንዷ በረሃ ነው የተወለደችው። ሁለቱን አዲስ አበባ ነው የወለድኳቸው። አንዱ. . . ብዙ ጊዜ ሰው ይምታታበታል። እኔ አልወለድኩትም። እናት አለችው ግን የሟቹ ጓደኛችን ክንፈ ገብረ መድህን ልጅ፣ ያሳደኩት ልጅ አለን።

ሁሉም ልጆችዎ ከእርስዎ ጋር ነው የሚኖሩት?

አሁን ለአባታቸው ሙት ዓመት ገብተው ነበር። አንዱ ወደ ውጭ አገር ሄዷል። ሦስቱ ግን ከእኔ ጋር ነው ያሉት። እንግዲህ ራሳቸውንም እየቻሉ ነው፤ ተመርቀዋል። የጨረሱም ያልጨረሱም አሉ። እና እነሱም ጥግ ጥጋቸውን ይይዛሉ።

ባለቤትዎመለስ ዜናዊን ዶክመንቶችና ጽሁፎች ሲያሰባስቡ እንደቆዩ ነግረውኛል ምን ያህል ቢበረክቱ ነው ይህን ያህል ዓመታት የፈጀብዎት?

ባለፈው ዓመት አሳውቀን ነበር። ወደ ስምንት መጻሕፍት. . . ራሱ የደረሳቸው፣ የራሱ መሆናቸው በራሱ የእጅ ፅሁፍ የተረጋገጡ፣ ባለፈው ደግሞ በመንግሥትና በፓርቲ ስም ሲወጡ የነበሩ፣ ፅድት ብለው ዝግጅታቸው የተጠናቀቁ ወደ ስምንት መጻሕፍት አሉ።

በአጠቃላይ ግን ወደ 30 ምናምን ይደርሳሉ። እነርሱንም ባለፈው ከነበረው ሁኔታ ጋር ከማተሙ ይልቅ ይዞ መቆየቱ ይሻላል ብለን አንዳንዶቹን ይዘናቸው ነበር። የበጀት እጥረትም አጋጥሞን ነበር።

የነበረንንና ያገኘነውን በሙሉ በቅድሚያ ለሕዝብ መናፈሻው 'ኢንቨስት' ስላደረግነው ነው። ስለ ዲሞክራሲ የፃፈው በቅርቡ ይታተማል። ስለ ግብርና የፃፈውና ሌሎችም ጠቅለል ተደረገው በቅርቡ ይታተማሉ።

''ከ122 ዓመት በፊት የተጣለ መሰረት ዛሬ እየተናደ እንዳይሆን'' ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ

አሁን ላለው ትውልድም ሆነ ለመጭው ትውልድ ይጠቅማሉ ያልናቸውና መውጣት አለባቸው ብለን ያሰብናቸው ጠቅለል ጠቅለል ብለው ይወጣሉ።

በተለይ የመደራደር አቅሙ ምን ይመስል እንደነበር እና ነገሮችን አስቀድሞ የሚያይባቸው፣ የሚመለከትባቸው፣ የሚተነትንባቸው፣ የሚገመግምበት መንገድ ምን ይመስል እንደነበር፤ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ይበጃል፤ ለትውልዱ ይጠቅማል ያልናቸው የተዘጋጁ ነገሮች አሉ። እነሱም በዚህ ዓመት ይወጣሉ ብዬ አምናለሁ። ዝግጅታቸው የተጠናቀቁት ወደ ስምንት ወይም አስራ አንድ ይደርሳሉ።

ስለዚህ ስምንቱ መጻሕፍት ተጠናቀው አልቀዋል ማለት ነው?

ተጠቃሎ አልቋል። የመጨረሻ ዲዛይናቸው ይቀራል። ሁለቱ ግን ዲዛይናቸውም ምናምናቸውም ስላለቀ በቅርቡ ታትመው ይወጣሉ።

የት ነው የሚታተሙት?

በ 'ቮሉዩም' [በክፍል] ስለጀመርነው እና የ 'ሃርድ ከቨሩ' [ሽፋኑ] ነገር አስቸጋሪ ስለሆነ የተወሰነው ውጭ ይታተማል። በብዙው ደግሞ እዚህ ታትሞ ለአንባቢያን በቅርብ እንዲገኝ እናደርገዋልን።

በአጠቃላይ ስንት መጽፍ አላቸው?

በአጠቃላይ ከ30 በላይ ናቸው የጻፋቸው። ያዘጋጀናቸው ሰነዶቹ በጣም ብዙ ናቸው። አሁን በቅርቡ እንዲታተሙ ያልፈለግናቸው የራሱ የጥናት ፅሁፎችም አሉ። በእንግሊዝኛ ተዘጋጅተው የተቀመጡ፤ በጣም ግዙፍ። እነርሱን ሳያካትት ማለት ነው እንጅ፤ ብናካትታቸው በጣም ብዙ ናቸው። ከ30 በላይም ይሄዳሉ። ግን አሁን ዝግጁ ናቸው፣ ሊወጡ ይችላሉ ብለን ያመንባቸው ስምንቱ ናቸው።

እነዚህን ነገሮች ለማስተካከልማነው የሚረዳዎት?

ትልቋ ልጄ ከእኔ ጋር ትሠራለች። ከአባቷ ፋውንዴሽን ጋር ትሠራለች። ሌሎች በፋውንዴሽኑ ስር የተሠሩ አሉ። አብዛኛውን ሰነዶቹን እኔ አውቀው ስለነበር ለዛ ነው ባለፉት ዓመታት ፀጥ ብዬ ሰነዶቹን መለየት ላይ፣ ማደራጀት ላይ [ያተኮርኩት]። አንዳንዶቹ 'ኦሪጅናል' [የራሱ የእጅ ጽሁፍ] እኔ ጋር ስለነበሩ፤ የማሰባሰቡ ጉዳይ፣ የማደራጀቱ ጉዳይ በቅርብ በእኔ ነበር የሚሠራው።

ከዚያ በኋላ ግን ሌሎቹን ሥራዎች ልጄም አለች፤ ሌሎችም አሉ የሚሠሩ። አዘጋጅቶ ለልጆቹ ማስረከብ ነበር. . . እኔ የቤት ሥራዬን ጨርሻለሁ።

መናፈሻው ላይም እየንደሆነ ገልፀውልኛል ከምን ደርሷል?

መናፈሻው በጉለሌ ተራራ ላይ የሰፈረ ነው። በጣም ትልቅ ነው። ስፋቱን አሁን በትክክል አላስታውሰውም። ለማንኛውም. . . ማዕከሉ ቤተ መጻሕፍት፣ የጥናት ማዕከል፣ ለጥናትና ምርምር ለሚመጡ እንግዶችና ተማሪዎች የእንግዳ ማረፊያ ክፍል አለው። መሰብሰቢያ አዳራሽ አለው። 'አውት ሉክ' [እንደ መናፈሻ] አለው።

ከአንዱ ወደ አንዱ ሲኬድም የመሬት አቀማመጡና የመሬት ዲዛይኑ ለታሪኩ እንዲመች ተደርጎ ተዘጋጅቷል። በአብዛኛው የተሸፈነው በአገር በቀል ዛፎች ነው። መሄጃዎቹ፣ መውረጃዎቹ ያለፋቸው የሕይወት ታሪኩን የሚገልፁ ሆነው ተዘጋጅተዋል። በ7ኛ ሙት ዓመቱ ላይ ምስሎቹ አለፍ አለፍ ብለው ቀርበዋል።

በጣም በታወቁ ባለሙያዎች፣ ትውልድ ተሻጋሪ ሆኖ እንዲቀር ታስቦ በጥንቃቄ የተዘጋጀ ዲዛይን ነው። እያንዳንዳቸው የራሳቸው መልዕክት አላቸው። ከመልዕክታቸው በተጨማሪ ውበትም አላቸው። እንደ ቤት. . . እንደ ግንባታ ብቻ ሳይሆን እንደ 'አርት ፒስ' [የጥበብ ሥራ] ሆነው እንዲቀሩ ተደርጎ ነው የተሠራው።

ለአገልግሎት መቼ ነው የሚከፈተው?

በቅርቡ ይሆናል። ጊዜው በውል አይታወቅም፤ ምክንያቱም አስመርቀን መክፈቱን አልፈለግነውም። ሲመረቅ ወዲያውኑ ሥራ ከመጀመሩ ጋር መያያዝ አለበት። የሰው ኃይሉም፣ መጻሕፍቱም. . . ሁሉም ዝግጅቶች ተጠቃለው እንደተመረቀ ወዲያውኑ ሥራ እንድንጀምር አድርገን ለመክፈት ስለፈለግን ነው።

ዚህን ራዎች ለማከናወን የገንዘብ ድጋፉ ከየት ነው ተገኘው?

ባለፈው መለስ እንደተሰዋ፤ የመለስ ፋውንዴሽን ሲመሰረት፤ ጎረቤት አገራትም፣ የአገራችን ክልሎችም፣ የፌደራል መንግሥትም እና ከሌላ. . . ከሕዝብ የተውጣጣ የገንዘብ ድጋፍ ነበረ። ያንን እንዳለ ወደዛ ነው ያስገባነው። ወደ ቤተሰብ የመጣ ምንም ነገር የለም። እርሱ እንደ ቋሚ ቅርስ ሆኖ እንዲቀር ስለፈለግነው። እናም ግንባታው እየተጠቃለለ ያለው በዚያ ነው።

የመፍቱ የሕትመት ወጪም?

አዎ! በዚያው በተደረገው ድጋፍ ነው። የራሱ የፋውንዴሽኑ አካውንት አለው። ወደ ፋውንዴሽኑ አካውንት ነው ገቢ የተደረገው። ከፋውንዴሽኑ አካውንት ደግሞ እያንዳንዱ ክፍያ ይካሄዳል። እርሱ ደግሞ በየዓመቱ ኦዲት ይደረጋል።

ፋውንዴሽኑ ላለዎት ሚና ምንድን ነው?

እንዳልኩሽ. . . ባለፈው ዋና፣ ትልቁ የእኔ ሥራ የተበታተኑ የመለስ ጽሁፎችን ማዘጋጀት ነበር። ሕወሓት እኔን ማስወጣቱ ትልቅ እድል ነው የሰጠኝ። ጊዜ አላገኝም ነበር፤ ማሰባሰብም አልችልም ነበር። የተበታተኑትን በሙሉ የማስታውሳቸውን፣ እጄ ላይ የነበሩትንና ሌላ ጋር የነበሩትን ለማሰባሰብ ቅድሚያ የሰጠሁት እሱን ነበር።

የሕወሓት ግምገማና እርምጃ ወዴት ያመራ ይሆን?

ይህን አዘጋጅቶ 'ዲጂታይዝ' ማድረግ፣ ለሚችሉት ለማስተላለፍ የጨረስኩትም በቅርቡ ነው። ዋናው ትኩረቴ የመለስን ሰነዶች የማዘጋጀት፣ ያው ሳዘጋጅ ደግሞ 'ካታጎራይዝ' ለማድረግ እየተነበበ ስለሆነ፤ ለማንበብም ትልቅ እድል ነው ያገኘሁት። እና ዋናው ሥራዬ እሱ ነው የነበረው። አልፎ አልፎም ሌሎች የምሠራቸው ነገሮች ነበሩ። ይህን ስላጠቃለልኩ ነው አሁን ወደ ሌላ ሥራ መግባት አለብኝ የምለው።

የገፈርሳ የአምሮ ህሙማን ማከል ጉዳይስ?

ያን ጊዜ ግንባታውን አጠቃለን ቁልፉን አስረከብን። ጤና ሚኒስቴር ተረክቦ ከአማኑኤል ሆስፒታል ጋር እንዲያያዝ ነበር ያደረግነው። ማዕከሉ ተከፍቶ እንዲሠራ 'ብራዘርስ' የተባሉ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮች፤ በ 'ሳይካትሪስት' [የሥነ ልቦና አማካሪነት] እንዲያገለገሉ ከውጪ አምጥተናል። አራት፣ አምስት ዓመታት አገልግለዋል። አሁን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር ነው የሚሠራው።

የእኔ ኃላፊነት የነበረው ግንባታውን አስጨርሶ፣ ማዕከሉን አደራጅቶ፣ አብቅቶ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲከታተለው ማድረግ ስለነበር፤ አሁን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

የወደፊት ዕቅድዎ ምንድን ነው?

ዋናው ሥራዬ ብዬ የማምነው በመለስ ስም የተሰየመውን የሕዝብ መናፈሻ ለሕዝብ ክፍት ማድረግ ነው- ወደ ማጠቃለል ደረጃ ስለደረሰ። እሱንና ልጆቼ ላይ አተኩሬ በዋናነት መስራት። የራሴን ሥራዎች፣ የግሌን ሕይወት የማስተዳድርበትን ለመጀመር እፈልጋለሁ። በየትኛው አቅጣጫ? እንዴት ብሎ? የሚለውን አጠቃልዬ ስጨርስ እገልፀዋለሁ።

በትርፍ ጊዜዎ ምንድን ነው ዝናናዎት?

አትክልት እወዳለሁ። ጊዜዬን ከአበባ ጋር፣ ከችግኝ ጋር፣ ከአትክልቶች ጋር ባሳልፍ እመርጣለሁ። ቤቴን እወዳለሁ። ከቤት ውጭ ብዙ መውጣት አልፈልግም። ከሥራ ወደ ቤቴ ነው የምመጣው። ስፖርት. . . የእግር ጉዞ አደርጋለሁ። ረዥም መንገድ እጓዛለሁ። አልፎ አልፎ ተራራዎችን እወጣለሁ. . . ራሴን ለመፈተን ስፈልግ መውጣት እችላለሁ። አልችልም ግን እወጣለሁ።

የት ተራራ ወተው ውቃሉ?

ያው. . . ከሽሮ ሜዳ ወደ እንጦጦ ማሪያም እወጣለሁ።

ባለቤትዎ የድምጻዊት አስቴር አወቀ ሙዚቃ አድናቂ እንደነበሩ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። የእርስዎ ምርጫስ?

የመለስ ተፅዕኖ መሰለኝ አስቴርን በጣም እወዳታለሁ። 'አልበሟ' ከመኪናዬ ተለይቶኝ አያውቅም. . . አዳዲስ የወጡ ሙዚቃዎችንም አዳምጣለሁ። ሌሎች ብዙዎችን አዳምጣለሁ። ብዙ ጊዜ ግን የአስቴርን ሙዚቃ እወዳለሁ። በጣም ብዙ ጊዜ ከራሴ ሕይወት ጋር የሚገጥም ስለምትዘፍን ደጋግሜ የእርሷን እሰማለሁ። ሌሎችንም ትግርኛ ሙዚቃዎችን እሰማለሁ።

ሙዚቃዎች ናቸው ከራስዎ ሕይወት ጋር የሚገጥሙት?አንድ ሁለት ምሳሌ ቢሰጡኝ?

በጣም ብዙ አጋጣሚዎች ሕይወቴ ጋር. . . ወደ ዝርዝር ልታስገቢኝ ነው እንጂ. . . [ሳቅ] ለምሳሌ አንድ ጊዜ የዘፈነችው ዘፈን አለ። ስለ ሰው፣ ስለ ሰው ቀድጄ ልልበሰው የምትለው። በዚያ ሰዓት ሕወሓት ውስጥ መከፋፈል የገጠመበት ወቅት ነበር። እርሱ እኔን ካጋጠሙኝ አጋጣሚዎች ጋር ገጥሞልኝ ነበር።

[የአስቴር 'ወየው ጉድ!' የሚለው ሙዚቃዋ ከስንኙ ትንሽ እንበላችሁ]

[. . . አትሸበር ልቤ ለሆነ ላልሆነው

ስለ ሰውስለ ሰው ቀድጀ ልልበሰው. . . ]

እ. . . እነ አያ ጅቦ. . . ወይ ሥራን አይሠሩ፤ ወይ ሰው አያሠሩ ብላ የዘፈነችውንም እወደዋለሁ። እንደዛ አይነት አጋጣሚ ገጥሞኛል።

[ይህ ዘፈን 'እማሙ' ይሰኛል። ከስንኞቹ ጥቂቶቹን እናካፍላችሁ]

[ሰው ሩ ሰው ጥሩ እባካችሁ

እነ ቆርጦ ቀጥል እንዴት አደራችሁ?

***

ለምን ይነኩኛል ወሰውሱኛል

ቆራርጠው ቀለው ወነጅሉኛል

***

ፀጉር አትሰንጥቁ አየር አትመትሩ

ፈጣሪን አክብሩ ርታችሁ እደሩ ]

ድሮ ልጅ ሆኜ፤ ሜዳ ሆኜ፤ የምወደው ዘፈኖቿም አሉ። 'አገር አገር አለች፤ ይች አገረ ብርቁ' ብላ የምትዘፍነውን ደጋግሜ [እሰማው] እወደው ነበር። እ. . . የማን ነበር? ድንገት ሳለስበው ብላ የምትዘፍነዋ [የድጻዊት ብዙነሽ በቀለን ነው] የሚለውንም እወደው ነበር።

አስቴር አወቀ ከመለስ መሰዋዕት በፊት ያወጣችው ሲዲ ነበር። ከትራሳችን የማይለይ። 'ጨጨሆ' ያለበት። እዚያ አልበም ላይ አምስተኛው ወይም አራተኛው ቁጥር ላይ ያለው አለ። 'ካለ እሱ በስተቀር ሰው እንደሌለ' ምናምን ብላ የምትዘፍነው። እሱን እወደዋለሁ።

[ዘፈኑ 'ፍቅር አያልቅበት' ይሰኛል፤ አንድ ስንኝ እነሆ]

[. . . ትዝታህ በሙሉ ይደቀናል ከዐይኔ

ሰው እዳልተራ ካንተ በቀር ለእኔ]

መለስ ከተሰዋ በኋላ ያወጣችው ሲዲም ገጥሞልኛል። ስለዚህ አስቴር ትስማማኛለች ለእኔ።

አቶ መለስ የአስቴርን ሙዚቃ አብዝተው ሚወዱት ለምን ነበር? የተለየ ምክንያት ነበራቸው?

መለስ ሙዚቃ ማዳመጥ ይወዳል። አዳማጭ ብቻ አይመስለኝም። የሙዚቃ መሣሪያዎቹ እንዴት እንደገቡና የሚሰጡትን ድምፅ ለይቶ ማውጣት ይችል ነበር። ግጥሞቹን፣ ትርጉማቸውን፣ ቅኔያቸውን ያውቃቸዋል። በጣም ትልቅ ዋጋ ይሰጣቸዋል።

ከትግርኛ ዘፈኖች የታጋይ እያሱ በርሄን ሙዚቃዎች በጣም ያደንቅ ነበር። የእርሱ ትግርኛ ብዙዎቻችን ሳይገባን መለስ ይገባዋል- ቅኔው ውስጥ ላይ ያለው። ይዘቱን የመተንተን፣ ሙዚቃዎችን የማወቅ፣ የመረዳት ችሎታ ነበረው መለስ። እንግሊዝኛም ሲሰማ እንደዛው ነው።

አቶ መለስ ያንጎራጉሩ ነበር?

አዎ በጣም! ጠዋት ጠዋት ሲነሳ . . . አሊያም ማታ ሲገባ ያንጎራጉር ነበር። ያው ድምፅ የለውም ግን ግጥሞቹ ይወጣሉ።

አቶ ጌታቸው አሰፋ በሚያውቋቸው አንደበት

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ