“በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርን ዛሬም፣ ነገም፣ ወደፊትም የምከራከርበት ነው” ገነት ዘውዴ [ዶ/ር]

ዶ/ር ገነት ዘውዴ Image copyright Embassy of Ethiopia, New Delhi

አዲሱን ዓመት አስመልክተን ከመገናኛ ብዙኃን ጠፍተው የቆዩ ሰዎችን ማፈላለጋችንን ቀጥለናል። አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ሲነሳ ስማቸው አብሮ የሚነሳውን ገነት ዘውዴ [ዶ/ር]ን ፈልገን አግኝተናቸዋል።

ገነት ዘውዴ [ዶ/ር] በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 'ቴክኒካል ቲቸርስ ኤዱኬሽን' በረዳት መምህርነት አገልግለዋል። በዚያው ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር፣ መምህር፣ የቢዝነስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል። በቦስተን በንከር ሂል ኮሚዩኒቲ ኮሌጅ በትምህርት ክፍል የሥራ ልምምድ እንዳደረጉም መረጃዎች ያመለክታሉ።

"የሞራል ባቢሎን ውስጥ ነን፤ በጎና እኩይ መለየት አቅቶናል" ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

ታሪክ እየቀየሩ ያሉት ሴቶች

ከ1993 ዓ.ም በፊት ባሉት ጊዜያት በኬንያ፤ ኬንያታ ዩኒቨርሲቲ 'External examiner' [ከሌላ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ ፈታኝ] ሆነው አገልግለዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚንስትር፣ ከዚያም ከ1992 በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደርም ነበሩ።

የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ድግሪያቸውን በቢዝነስ ትምህርት ከአሜሪካ አገር አግኝተዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኒው ሃምፕሸር (University of New Hampshire)፤ ሁለተኛ ድግሪያቸው ሰፎክ ዩኒቨርሲቲ- ቦስተን (Suffolk University-Boston) ነው ያጠናቀቁት። ሦስተኛ ድግሪያቸውን ከሕንድ አገር ጃዋህራል ኔህሩ Jawaharla Nehru university [JNU] ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት አግኝተዋል። በትምህርት ሚኒስቴር የመጀመሪያዋ ሴት ሚንስትርም እንደነበሩ ገልፀውልናል።

ገነት ዘውዴ [ዶ/ር] ሁለት መጻሕፍትን ጽፈዋል። አንዱ በሴቶች ላይ፣ ሌላው ደግሞ በትምህርት ፖሊሲው ላይ የሚያተኩር ነው። የመጀመሪያው Resistance, freedom and Empowerment: The Ethiopian women struggle [የኢትዮጵያ ሴቶች ትግል] የሚል ሲሆን በአማርኛ ተተርጉሟል። ሁለተኛው መጽሐፍ ወደ አማርኛ ባይመለስም ከሁለት ዓመታት በፊት ነው የወጣው። No One Left Behind የሚልና ስለ ትምህርት ፖሊሲው የሚያትት ነው። ከርሳቸው ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ እነሆ።

አሁን ምን ላይ ነው ያሉት? ምን እየሩ ነው?

አሁን ጡረታ ወጥቻለሁ። ጡረታ ከወጣሁ ሦስት ዓመት ሆኖኛል፤ ነገር ግን ጡረታ ከወጣሁ ጊዜ ጀምሮ 'የሴቶች ልማታዊ ስትራቴጅክ ሴንተር' አቋቁሜ እዚያ ላይ በ'ሪሰርች'[ ጥናት] እና በ'አድቮኬሲ'[የቅስቀሳ ሥራ] እየሠራሁ ነው።

ተቋሙ ምንድን ነው የሚያከናውነው? በዝርዝር ይንገሩኝ እስኪ. . .

በሴቶች ሕይወት ዙሪያ ጥናቶች እያደረኩ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሥልጠናም እንሰጣለን- የ'ሊደርሽፕ' እና የ'ኢንተርፕርነርሽፕ' [የአመራርነትና የሥራ ፈጠራ] ሥልጠናዎች አሉት። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሚዲያም የ'አድቮኬሲ'[የቅስቀሳ] ሥራ እንሠራለን - ስለ ሴቶች ሕይወት።

በሚዲያ ላይ የሚተላለፍ ፕሮግራም ነበረዎት ልበል?

አዎ፤ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ነበረኝ። እናንተም ቢኖራችሁ እንዴት ደስ ይለኝ ነበር። 'የሕይወት ወግ' የሚል በዋልታ ቴሌቪዥን የሚቀርብ ነበር። ነገር ግን በ'ስፖንሰር' [የገንዘብ ድጋፍ] መቋረጥ ምክንያት አሁን ተቋርጧል-ለትንሽ ጊዜ።

በጣም ጥሩ ፕሮግራም ነበር። ከአንድ ዓመት በላይም ተላልፏል። በፕሮግራሙ በሴቶች ሕይወት ዙሪያ 'ዲስከሽኖች' [ውይይቶች] ነበሩ። የተለያዩ የሴቶችን ጉዳዮች እያነሳን ነበር የምንወያየው። በድህነት ምክንያት ቀረ።

ትምህርት ዕድሜን እንደሚያስረዝም በጥናት ተረጋገጠ

በትምህርቱ ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋልና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚሠሩት አለ?

ይሄ አይበቃኝም እንዴ በዚህ ዕድሜ? [ዘለግ ያለ ሳቅ] ይሄ በጣም ብዙ ሥራ ነው። በጣም ብዙ 'ሪሰርች' [ጥናት] አለው፤ 'ትሬኒንግ' [ሥልጠና] 'አድቮከሲ' [ቅስቀሳ] አለ. . . ለአሮጊት ይሄ አነሰው ብለሽ ነው?. . . [ሳቅ]

ዕድሜዎ ስንት ነው ዶክተር? ድሜ አይጠየቅም ይባላል። ግን. . .

ግድ የለም። አሁን እኔ ባል ስለማልፈልግ ግድ የለም። [ሳቅ] 71 ዓመቴ ነው።

አማካሪ ሆነው የሠሩበት አጋጣሚ አለ?

አይ የለም። ምክር ለጠየቀኝ ሰው ግን እሰጣለሁ። ስለ ልጅነት፣ ስለ ሴትነት፣ ስለ አሮጊትነት ምናምን. . .

እግረ መንገዴን ልመከር እንዴ?

በስልክማ ይቆጥርብሻል። ምክር ደግሞ በ'ፐብሊክ'[በአደባባይ] አይደለም። ቁጭ ብለን፤ ሻይ ቡና እያልን ነው።

የትምህርት ፖሊሲው ከእርስዎ ጊዜ ጀምሮ እንደተዳከመ ይወራል፤ እርስዎም ላይ ትችት ሲቀርብ ይሰማል። እንዲያውም እርስዎ ሚንስትር በነበሩበት ጊዜ በተቀረፀው ፖሊሲ እየተማሩ ያሉት ትውልዶች 'የገነት ዘውዴ ልጆች' የሚል ተቀፅላ ወጥቶላቸዋል። እርስዎ ይሰማሉ ስለዚህ?

እሰማለሁ፤ ግን I am not involved [የለሁበትም]። ከትምህርት ሥርዓቱ ከወጣሁኝ. . . ዐሥር ዓመታትን በሕንድ ዲፕሎማት ነበርኩ። አሁን ጡረታ ከወጣሁ ሦስት ዓመቴ ነው። ስለዚህ ከትምህርት ሥርዓቱ 13 ዓመታት ተለይቻለሁ። እናም. . . እሰማለሁ ግን በዚህኛው ሥራ ሴቶች ላይ ስለማተኩር ብዙም እንትን አላልኩም. . . መስማቱን ግን እሰማለሁ።

ሲሰሙ የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው?

ዌል እንግዲህ. . . ጊዜ ኖሮኝ ቁጭ ብዬ የሚባለው ነገር እውነት ነው፤ አይደለም? ምንድ ነው ችግሩ? ብዬ ባጠናው ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን አላጠናሁትም።

ወደ ፊት ለማጥናት አላሰቡም ?

እሱ እንግዲህ. . . እንዴ! እኔ አኮ አርጅቻለሁ [ ሳቅ] ምን ማለትሽ ነው? የተሰማኝን. . . ትምህርት ፖሊሲው ምን እንደነበር፣ እንዴት እንደነበር ጽፌያለሁ። ከዚያ በኋላ የፈለገ ሰው ያንን እየጻፈ ደግሞ ይቀጥል። ሁል ጊዜ አንድ ሰው ላይ ብቻ አይደለም መቀባበል። አለ አይደል. . .

የድምፅዎ ጉልበት ግን እርጅና ላይ ያሉ አይመስሉም?

[ሳቅ] . . . ስለዚህ እኔ የሚሰማኝን መጽሐፍ ላይ አስቀምጫለሁ። ከዛ በኋላ ደግሞ እየተቀባበሉ፤ ያንን 'ኮሬክት'[እርማት] እያደረጉ፤ እየተቀባበሉ መሄድ ደግሞ የአዲሱ ትውልድ ነው። አንድ ሰው ብቻ መሆን የለበትም። አይመስልሽም?

ከዚሁ ከትምህርት ፖሊሲ ሳንወጣ፤ ሚንስትር በነበሩበት ጊዜ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ሳቡን ያመጡት እርስዎ ነዎት ይባላል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ይሄ እኮ እኔ ዝም ብዬ በጭንቅላቴ ያመጣሁት አይደለም። የዩኔስኮ፣ የዓለም አቀፍም ትኩረት ነው። ትምህርት እየተስፋፋ፣ ዘመናዊ እየሆነ በመጣ ቁጥር በጣም ብዙ ምርምሮች ይወጣሉ። እናም ልጆች መጀመሪያ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው መማር ያለባቸው። ትምህርት ደግሞ ማሰብን ፣ ማሰላሰልን ይጠይቃል። የሰው ልጅ የሚያስበው . . . የሚያሰላስለው በአፍ መፍቻ ቋንቋው ነው። በመሆኑም ይህ የዩኔስኮም፣ የዓለም አቀፉም እንትን ነው... ገነት ስብሰባ ላይ ዱብ ያደረገችው አይደለም።

በወቅቱ ብዙ እንደተሟገቱ ስለሰማሁ ነው. . .

በጣም በጣም!. . . አሁንም ቢሆን ነገም ከነገ ወዲያም እሟገታለሁ። ልንገርሽ አይደል? እኔ አንደኛ ደረጃም አይደለም፤ ሁለተኛ ደረጃም እንደዚያ እንዲሆን ከአሁኑ ጀምረን እያሰብን. . . የቋንቋ አካዳሚዎችን እያቋቋምን ምን እያልን ዩኒቨርሲቲዎችም በቋንቋቸው እንዲሆን ብዬ አምናለሁ [የሕንድን ተሞክሮ ያነሳሉ]

እንዲህ መሆኑ ችግሮች የሉትም ብለው ያስባሉ?

አዎ! ችግሮች ይመጣሉ። ችግር የሌለው ነገር አለ አንዴ? ችግር እየፈታን እንሄዳለን እንጅ ችግር ይመጣል ብለን ከችግር አንሸሽም። ቋንቋ የማንነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን. . . ወደ ትምህርት ፣ ወደ ሳይንስ ስንሄድ በጣም ትልቅ መሣሪያ ነው። እኔ ዛሬም ፣ ነገም፣ ተነገ ወዲያም የምከራከርበት ነው።

በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ እንዲህ መሆኑ አይለያየንም?

ለጋራማ፤ የጋራ ቋንቋ አለን እኮ! የፌደራል ቋንቋው አማርኛ እና እንግሊዝኛ ነው። ትምህርት ላይ ሲሆን ግን በእንግሊዝኛ ቋንቋም አይደለም. . . ። እስከ አምስት ስድስት ዓመቱ በቋንቋው ሲቦርቅ የነበረን ልጅ አምጥተሽ፤ አንደኛ ክፍል አስገብተሽ በሌላ ቋንቋ ተማር ስትይው Is it fair? የ'ፌይርነስ' ጉዳይ ብቻ ሳይሆን...ይገባዋል? እና . . . ቀላል ነገር አይደለም። በጣም ከቋንቋው ጋር የተያያዘ ነው። እኔ . . . እንደ ቀላል ለምን እንደሚያዩት አይገባኝም። ስለዚህ ነገም ከነገ ወዲያም የምከራከርበት ጉዳይ ነው።

እስኪ አሁን ደግሞ፤ የግል ሕይወትዎን ያጫውቱኝ?

የሁለት ሴቶች ልጆች እናት ነኝ። አሁን ደግሞ ሁለቱ ሴት ልጆቼ የሦስት ልጆች አያት አድርገውኛል። I am happy with my personal life . . . ያው ትዳር ፈት እንደሆንኩ ታውቂያለሽ ብዬ ነው። [ሳቅ] ግን I'm very happy! ከልጆቼ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ።

በተለይ ከልጅ ልጆቼ ጋር. . . በቃ ፍቅር ይዞኝ . . . ፍቅር ወደታች አይደል? ከእነሱ ጋር ነው ትርፍ ጊዜዬን የማሳልፈው። በሕይወት ያሉ ጓደኞቼም አሉ ከእነርሱም ጋር . . .እ . . . I love to read, I read.. ይሄ ነው የግል ሕይወቴ።

ምን ዓይነት መጽሐፍ ነው የሚያነቡት?

ማንኛውንም። በኢትዮጵያ የተጻፉም በዓለም ላይ ያሉ. . . የኢኮኖሚ፣ የትምህርት ምናምን. . . ድሮ ወጣት ሆኜ ልብ ወለድ ነበር የምወደው አሁን ግን ጠንከር ያሉ [Serious] የሆኑ መጻሕፍትን. . . ልብ ወለድ ድሮ ልጅ እያለሁ እወድ ነበር አሁን ግን አረጀሁ [ሳቅ]

ግን ምርጫዎ የማን ነበር?

በእኛ ግዜ አጋታ ክርስቲ፣ ዳኔላ ስቲል፤ ከኢትዮጵያ ደግሞ ፍቅር እስከመቃብርን ። ፍቅር እስከ መቃብርን ሦስት ጊዜ አንብቤዋለሁ። ሦስት ጊዜም ሳነበው አዳዲስ ነገር አግኝቸበታለሁ። ኦሮማይ ፣ ወንጀለኛው ዳኛ. . . ድሮ አያቴ መጽሐፍ ታነብ ነበር፣ እናም መጽሐፍ ማንበብ ያስተማረችኝ እርሷ ናት።

ሙዚቃስ?

ሙዚቃና እስክስታማ በጣም እወዳለሁ። እስክስታው አለ። አሁን ግን እያረጀሁ ጉልበቴም እየቀነሰ ብዙም አይደለሁ። ግን አሁንም ቢሆን ሙዚቃ ከሰማሁ ነሸጥ ያደርገኛል። እነ አስቴርን፣ ብዙዬን፣ ጥላሁን ገሠሠን እና በተለይ ደግሞ የበዛወርቅን ግጥሞቿን በጣም እወደዋለሁ። በተለይ አንድ ግጥም አላት መጽሐፌም ላይ 'ኮት' አድርጌዋለሁ[ ጠቅሸዋለሁ]።

. . . የማነሽ ይሉኛል የማን ልበላቸው፣

ብቻየን ብቀርስ ምን አስጨነቃቸው. . . የሚለውን።

የተለየ ምክንያት አለው እንዴ?

ለምን መሰለሽ. . . እኔ ከሴት ልጅ ጋር ነው የማያይዘው። ሁልጊዜ ሴት . . .የማነሽ? 'የሰው ነሽ' ነው እኮ። ዕቃ ነሽ ነው፤ የወንድ ዕቃ ነሽ ነው እኮ። ድምጿንም እወደዋለሁ። ከአዳዲሶቹ ቴዲ አፍሮ ደስ ይለኛል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ