አል-ቃይዳ ከቢን ላደን ልጅ መገደል በኋላ

ሃምዛ ቢን ላደን Image copyright CIA
አጭር የምስል መግለጫ ሃምዛ ቢን ላደን

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሃምዛ ቢን ላደን፣ የቀድሞ የአል-ቃይዳ መሪ የኦሳማ ቢን ላድን ልጅ አሜሪካ ባካሄደችው ኦፕሬሽን መገደሉን ይፋ አደረጉ።

ከአንድ ወር በፊት በርካታ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በስም ያልተጠቀሱ የአሜሪካ የደህንነት ቢሮ ባልደረባን ዋቢ እያደረጉ የሃምዛን መገደል ዘግበው ነበር።

ሃምዛ ከሁለት ዓመት በፊት በአሜሪካ መንግሥት ''አሸባሪ'' ተብሎ ተፈርጆ ነበር።

አልቃይዳ ከወዴት አለ?

የኦሳማ ቢን ላደን ልጅ 'በአየር ጥቃት መገደሉ' ተነገረ

የ30 ዓመት ወጣት የነበረው ሃምዛ አባቱን በመተካት የአል-ቃይዳ መሪ እንደነበረ ይታመናል። ሃምዛ በተደጋጋሚ በአሜሪካ እና በሌሎች ሃገራት ላይ ጥቃቶች እንዲሰነዘሩ መልዕክቶችን ያስተላልፍ ነበር። ሃምዛ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት የአባቱን ገዳዮች ለመበቀል በምስልና በድምጽ የተቀረጸ መልዕክት ለተከታዮቹ አስተላልፎ ነበር።

ዋይት ሃውስ ባወጣው መግለጫ ላይ ፕሬዝደንት ትራምፕ "የአል-ቃይዳ ከፍተኛ አመራር የነበረው እና የኦሳማ ቢን ላደን ልጅ ሃምዛ ቢን ላደን የአሜሪካ ጸረ-ሽብር ግብረ ኃይል በአፍጋኒስታንና ፓኪስታን ድንበር ባካሄደው ኦፕሬሽን ተገድሏል" ብለዋል።

መግለጫው ሃምዛ የተገደለበት ኦፕሬሽን መቼ እንደተካሄደ አልጠቀሰም።

ከጥቂት ወራት በፊት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የኦሳማ ቢን ላደን ልጅ ያለበትን ለጠቆመኝ ወደ 1 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ብሎ ነበር።

መስከረም 11፣ 2001 አሜሪካ፣ ኒው ዮርክ ውስጥ የአውሮፕላን ግጭት በመፍጠር ወደ 3000 የሚጠጉ ሰዎች በመግደል ተጠያቂ የሆነው ቢን ላደን፣ ከአደጋው ከአስር ዓመት በኋላ በ2011 ፓኪስታን ውስጥ በአሜሪካ ልዩ ሃይል መገደሉ ይታወሳል።

አል-ቃይዳ ወዴት አለ?

የአልቃይዳ ቡድን መስራች ኦሳማ ቢላደን ፓኪስታን ውስጥ በአሜሪካ ኃይሎች ከተገደለ ዓመታት ተቆጠርዋል። ቡድኑ በዓለማችን ላይ አደገኛ የሚባሉ የጂሃድ ጥቃቶችን ይፈፅም የነበረ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችንም ያዝዝ ነበር።

ቡድኑ ጥቃቶችን ለመፈፀም የማይነጥፍ የገንዘብ ምንጭ እንደነበረውም ይታመናል። ነገር ግን የቡድኑ መሪ ቢን ላደን ከተገደለ በኋላ የአል-ቃይዳ ስም እየደበዘዘና ጉልበቱም እየሟሸሸ መጥቷል።

አል-ቃይዳን ይመራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የሃምዛ ቢን ላደን መገደል የአል-ቃይዳን አቅም እጅጉን ሊያዳክም ይችላል ተብሏል።

በሳዑዲ 'አንድ ወንድ እኩል ይሆናል ሁለት ሴት'

የአሜሪካ ደህንነት ኃይል የቢንላደን መገደልና የአይኤስ ቡድን መጠናከር አል-ቃይዳ አዳዲስ ዘዴዎችን እንዲጠቀም አስገድደውታል ይላል። አል-ቃይዳም ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅና ደቡብ እስያ ቅርንጫፎች አሉት።

እ.ኤ.አ. በ2015 የአል-ቃይዳ መሪ የሆኑት አይማን አል ዛዋሃሪ ለቡድኑ መሪነት "የመንጋው መሪ አንበሳ" ብለው አንድ ወጣት አስተውቀዋል።

ወጣቱ የኦሳማ ቢላደን ልጅ ሃምዛ ቢን ላዲን ሲሆን በብዙዎች የወደፊቱ የአልቃይዳ መሪ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።

ጥቂት ስለ አል-ቃይዳ

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኦሳማ ቢን ላደን እ.አ.አ. 2001 ዓ.ም. ካቡል አፍጋኒስታን
  • እ.አ.አ. 1980ዎች መጨረሻ ላይ በአፍጋኒስታን ተመሰረተ።
  • ኦሳማ ቢን ላደን ከአፍጋኒስታን ሶቪየት ሕብረት ኃይልን ለማስወጣት በአሜሪካ ድጋፍ የሚደረግለት ድርጅት አቋቋመ።
  • የድርጅቱም ስም ''አል-ቃይዳ'' ሲል ሰየመው።
  • እ.አ.አ. 1989 ላይ አፍጋኒስታንን ለቅቆ ወጣ። ከዚያም 1996 ኃይ ወደ አፍጋኒስታን በመመለስ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሙስሊም ወጣቶች የውትድርና ስልጠና መስጠት ጀመረ።
  • በመቀጠልም አል-ቃይደ በአሜሪካ፣ በአይሁዶች እና በአጋሮቻቸው ላይ ጦርነት አወጀ

ተያያዥ ርዕሶች