ሳዑዲ ላይ በተፈጸመው ጥቃት የኢራን እጅ እንዳለበት የአሜሪካ መረጃ ጠቆመ

የሳተላይት ምስሎች Image copyright Reuters

አሜሪካ የደህንነት ተቋሟን በመጥቀስ ይፋ ያደረገቻቸው የሳተላይት ምስሎች ቅዳሜ ዕለት በሳዑዲ አረቢያ ላይ በተቃጣው የድሮን ጥቃት ላይ ኢራን እጇ እንዳለበት ጠቆሙ።

ኢራን ግን የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ምንም አይነት ተሳትፎ አላደረኩም ብላ ትከራከራለች።

በኢራን የሚደገፉት እና በየመን የሚንቀሳቀሱት የሁቲ አማጽያን ለጥቃቱ ሃላፊነቱን እኛ እንወስዳለን ቢሉም፤ ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣን ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ጥቃቱ የተሰነዘረበት አቅጣጫ እና ስፋት የሁቲ አማጽያን ፈጽመውታል ብሎ ለማሰብ አያስችልም ብለዋል።

በሁለቱ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ የደረሰው ጥቃት የዓለምን የነዳጅ አቅርቦት በ5 በመቶ ከመቀነሱም በላይ የነዳጅ ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓል።

በሳዑዲ ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ

አሜሪካ ሳዑዲ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አደረገች

የሁቲ አማጺያን ወደ ሳዑዲ ሚሳዔል ተኮሰች

አሜሪካ ምን እያለች ነው?

አሜሪካ ሳዑዲ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደባትም።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ ቅዳሜ ዕለት የሳዑዲ ነዳጅ ማውጫ ተቋማት ላይ ለተሰነዘረው የድሮን ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አድርገዋል።

ከምዕራባውያን መንግሥታት ድጋፍ የሚያገኘው ሳዑዲ መራሹ ኃይል በየመን እየተደረገ ባለው ጦርነት ለየመን መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ ኢራን ደግሞ ለሁቲ አማጽያን ድጋፍ ታደርጋለች።

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊው ማይክ ፖምፔዮ ''የድሮን ጥቃቱ ከየመን ስለመነሳቱ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ የለም። ሁሉም መንግሥታት ኢራን በዓለም የኢንርጂ ምንጭ ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ማውገዝ አለባቸው'' ብለው ነበር።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በበኩላቸው ለጥፋቱ ማን ተጠያቂ እንደሆነ ስለምናውቅ "አቀባብለን" የሳዑዲ መንግሥት ምክረ ሃሰብ ምን እንደሆነ እየጠበቅን ነው በማለት ወታደራዊ አማራጭ ከግምት ውስጥ እንደገባ አመላክተዋል።

ይህ በስም ያልተጠቀሱት የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን ሲናገሩ፤ ዒላማ የተደረጉት 19 ቦታዎች እንደነበሩ እና ጥቃቱ የተሰነዘረው ከምዕራብ እና ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው፤ ጥቃቶቹ የተነሱባቸው ስፍራዎች በየመን የሁቲ አማጺያን የሚቆጣጠሯቸው ቦታዎች አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ ጨምረው እንደተናገሩት የተገኘው መረጃ ጥቃቱ የተሰነዘረው ከኢራን ወይም ኢራቅ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል ብለዋል።

አሜሪካ ይፋ ያደረገቻቸው የሳተላይት ምስሎች በነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማቱ ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳትም አመላክተዋል።

በሳዑዲ ላይ የተሰነዘሩት የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶች መሆናቸውን እና ሁሉም ዒላማቸውን መምታት አለመቻላቸውን የአሜሪካ የደህንነት ቢሮ መረጃ ጠቁሟል።

'ኤቢሲ' ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣኑን ጠቅሶ እንደዘገበው ፕሬዝደንት ትራምፕ ለጥቃቱ ተጠያቂዋ ኢራን መሆኗን አምነዋል።

ይህን ጥቃት ተከትሎ ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭማሪ አሳይቷል።

የሳዑዲ ባለስልጣናት ጥቃቱ በሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም በማለት የድሮን ጥቃቱ ስላደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ቀርተዋል። ነገር ግን ጥቃቱ የሳዑዲ አረቢያ የድፍድፍ ነዳጅ የማምረት አቅምን በግማሽ መቀነሱ ተረጋግጧል።

ሳዑዲ አረቢያ የዓለማችን ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች ስትሆን በየቀኑ ወደ 7 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ውጪ ሃገራት ትልካለች።

የሁቲ አማጺያን እነማን ናቸው?

በኢራን መንግሥት ድጋፍ የሚደረግላቸው የሁቲ አማጽያን የየመንን መንግሥት እና የሳዑዲ መራሹን ኃይል ሲፋለሙ ቆይተዋል።

ፕሬዝደንት አብደራቡህ ማንሱር ከመዲናዋ ሰነዓ በሁቲ አማጽያን ተባረው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ የመን ላለፉት 4 ዓመታት በጦርነት ስትታመስ ቆይታለች።

ሳዑዲ ከመዲናዋ የተባረሩትን ፕሬዝደንት በመደገፍ በሁቲ አማጽያን ላይ በየቀኑ ማለት በሚቻል መልኩ የአየር ጥቃቶችን ትፈጽማለች። የሁቲ አማጽያን በበኩላቸው ሚሳኤሎችን ወደ ሳዑዲ ያስወነጭፋሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ