ቱኒዚያዊያን ሁለተኛ ነጻ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫቸውን አከናወኑ

መራጮች Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ከመራጮች አብዛኛዎቹ ጎልማሶችና እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ነበሩ

በቱኒዚያ እ.አ.አ. በ2011 በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ፕሬዝዳንት ቤን አሊ ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ነጻ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተካሂዷል።

በምርጫው 26 ተፎካካሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።

ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ በግላቸው የሚወዳደሩት ካይስ ሳይድ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ የተሻለ ድምጽ ሳያገኙ እንዳልቀረ ተገምቷል። የመራጮች ቁጥር ግን በእጅጉ ዝቅተኛ መሆኑም ታውቋል።

የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት በ92 ዓመታቸው አረፉ

የቱኒዚያው ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በ11 ህፃናት ሞት ምክንያት ስልጣን ለቀቁ

ከአጠቃላይ የቱኒዚያ ህዝብ 45 በመቶ ብቻ የሚሆነው ለምርጫው የወጣ ሲሆን፤ ምንም እንኳን ወጣቶች በምርጫው እንዲሳተፉ ቅስቀሳዎች ሲደረጉ ቢቆዩም አብዛኛዎቹ ጎልማሶችና እድሜያቸው የገፋ ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።

በቱኒዚያ ታሪክ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከአምስት ዓመት በፊት የተመረጡት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቤጂ ኬይድ ኢሴብሲ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ነው ሃገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ ደፋ ቀና ስትል የነበረው።

ቤጂ ኬይድ ኢሴብሲ በ92 ዓመታቸው ሲሆን ህይወታቸው ያለፈው የዓለማችን በእድሜ የገፉ በስልጣን ያሉ ፕሬዝዳንት ነበሩ።

ነገር ግን ወጣቱ ማህበረሰብ በምርጫው ላይ በብዛት አለመሳተፉ ሌላ ፈተና ሊሆን እንደሚችል እየተገለጸ ነው።

"ወጣቶቹ የት ሄደው ነው? ሃገሪቱ እኮ የእነሱ ናት። የወደፊቱ ተረካቢዎች እነሱ ናቸው'' ሲል አንድ ለምርጫ የወጡ የ60 ዓመት አዛውንት ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

የቱኒዚያ የጤና ሚንስትር ከሩጫ በኋላ ህይወታቸው አለፈ

ይፋዊ የሆነው የምርጫ ውጤት ማክሰኞ ዕለት እንደሚገለጽ የሚጠበቅ ሲሆን ማን ያሸንፋል የሚለው ጥያቄ እጅግ ከባድና ለመገመት አስቸጋሪ መሆኑ እየተዘገበ ነው።

በምርጫው አብላጫ ድምጽ ያገኘ ተወዳዳሪ የሚያሸንፍ ይሆናል። ነገር ግን የትኛውም ተወዳዳሪ አብላጫ ድምጽ ማግኘት ካልቻለ ካሉት ተወዳዳሪዎች ከፍተኛውን ድምጽ ማግኘት የቻሉት ሁለት ተወዳዳሪዎች በቀጣዩ ዙር ይፎካከራሉ።

አሸናፊው ተወዳዳሪ ደግሞ ለአምስት ዓመታት ሃገሪቱን የሚያስተዳድር ይሆናል።

ተያያዥ ርዕሶች