የማላዊ ሴተኛ አዳሪዎች ህይወታችን ተቀይሯል እያሉ ነው

ሁለት ሴቶች Image copyright Isabel Corthier

ማላዊ በዓለማችን ከፍተኛ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት ካለባቸው ሃገራት መከከል አንዷ ስትሆን በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩት ደግሞ በበሽታው የመያዛቸው እድላቸው በጣሙን ከፍ ያለ ነው።

ከዚህ ባለፈ ያልተፈለገ እርግዝና እና ሌሎች በሽታዎችም አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ተስፋፍተዋል።

እ.አ.አ. ከ2014 ጀምሮ 'ዶክተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ' የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከማላዊ ጤና ሚኒስትር መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር ለሴተኛ አዳሪዎች የተሻለ የጤና አገልግሎትና 'ፒአርፒ' የተባለ በኤችአይቪ የመያዝ እድልን የሚቀንስ መድሃኒት ሲያቀርብ ነበር።

“ከተማ አስተዳደሩ የወሲብ ንግድን በህግ ወንጀል የማድረግ ስልጣን የለውም” የህግ ባለሙያ

የሂትለር ወጥ ቀማሾች አስደናቂ ታሪክ

በአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት የጥቂቶቹን ታሪክ ልናካፍላችሁ ወደድን።

በርናዴት፡ ሴተኛ አዳሪ

በርናዴት የተገኘችው 11 ልጆች ካሉት ቤተሰብ ነው። ገና የ7 ዓመት ህጻን እያለች ቤተሰቦቿን በሞት የተነጠቀች ሲሆን ያደገችው በታላቅ እህቶቿ እና በአያቶቿ ተንከባካቢነት ነበር።

ቤተሰቡ በነበረበት ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ምክንያት ትምህርት ቤት ስትሄድ በባዶ ሆዷ ነበር። ትንሽ ከፍ ስትል ግን ምግብ፣ መጽሃፍትና ሌሎች መገልገያዎችን እንደ ክፍያ በመቀበል ከተለያዩ ሰዎች ጋር ግብረስጋ ግንኙነት መፈጸም ጀመረች።

18 ዓመት ሲሞላት ባላሰበችው ሁኔታ አርግዛ ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገደደች።

በአሁኑ ሰአት የስድስት ልጆች እናት ስትሆን ባለቤቷ በተደጋጋሚ ጥቃት ይፈጽምባት እንደነበር ትናገራለች። ድብደባው ሲበዛባት እ.አ.አ. በ2018 ፊቷን ወደ ሴተኛ አዳሪነት አዞረች።

Image copyright Isabel Corthier

"ድርጅቱ ስለሚሰጠው አገልግሎት ስሰማ በጣም ደስ አለኝ። ብዙ የማላውቃቸውን ነገሮች ነው ያስተማሩኝ። ጤናዬን እንዴት መጠበቅ እንዳለብኝ፤ ስለ ኤችአይቪ ኤድስ ምርመራ እንዲሁም ሌሎች።''

''ሌላው ቢቀር አሁን ኮንዶም እንዴት መጠቀም እንዳለብኝ አውቄያለሁ። ከዚህ በፊት መከላከያ ስለመጠቀም ብዙም እውቀት አልነበረኝም። አሁን ከደንበኞቼ ጋር ያለ ኮንዶም ምንም አይነት ግንኙነት እንደማላደርግ እንግራቸዋለሁ።''

ማሪያ፤ ሴተኛ አዳሪ

ማሪያ የ36 ዓመት ሴት ስትሆን ለ11 ዓመታት በትዳር ቆይታለች። ባለቤቷ የሚያመርታቸውን የግብርና ምርቶች በመሸጥ ነበር የምትተዳደረው። በድንገት የ11 ዓመት ባለቤቷ ጥሏት ሲሄድ ትንሽ ሴት ልጇን ይዛ መግቢያ አጣች።

በስፔን የሴቶችን የተጋለጠ አካል ያለፈቃዳቸው በቪዲዮ የቀረፀው ተከሰሰ

በመጨረሻም ወደ ሴተኛ አዳሪነት ገባች።

''ስራው በጣም ከባድ። አንዳንድ ደንበኞች አንከፍልም ይላሉ።''

''በሌላ ጊዜ ደግሞ ሆነ ብሎ ኮንዶሙን የቀደደ ደንበኛ አጋጥሞኛል። ለምን ብዬ ስጠይቅ ተበሳጭቶ በቦክስ መታኝ። ሁለት የፊት ጥርሶቼን አወለቀና እንደውም አልከፍልሽም ብሎኝ ሄደ።''

Image copyright Isabel Corthier

"ይህ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት ጥቃት ሲደርስብን ፖሊስ ጋር መሄድ አንችልም ነበር። ብንሄድም ያባሩናል። ተገቢውን ጤና አገልግሎት ማግኘትም የማይታሰብ ነገር ነው።''

''አሁን ግን የፈለግነውን አይነት ህክምና ከተለያዩ የጤና ምክሮች ጋር እያገኘን ነው'' ብላለች።

አደሊን፡ የማህበረሰብ ጤና ሰራተኛ

አደሊን የማህበረሰብ ጤና ሰራተኛ ሆና መስራት የጀመረችው እ.አ.አ. 2015 ላይ ነበር።

''የማህበረሰቡን ጤና ከመጠበቄ በፊት የራሴን ጤና መጠበቅ መቻል አለብኝ።'' ስለጤና እውቀት አለኝ ማለት በማንኛውም ሰዓት ወደ ሆስፒታል ሄጄ ህክምና ማግኘት እችላለሁ ማለት ነው'' ትላለች።

አደሊን ከ2005 ጀምሮ በሴተኛ አዳሪነት ህይወቷን ትመራ ነበር። ከዛ በፊት ደግሞ ትዳር መስርታ የሁለት ልጆች እናት ነበረች፤ ትዳሯ ሲፈርስ ግን ልጆቿን የምታስተዳድርበት የገቢ ምንጯ ተቋረጠ።

ብልትን መታጠን ጉዳት እንዳለው ባለሙያዎች አስጠነቀቁ

በሴተኛ አዳሪነት ገንዘብ ማግኘትም የነገረችኝ ጓደኛዬ ነበረች የምትለው አደሊን አማራጭ ስላልነበራት ወደ ስራው ገብታለች።

በ2015 ከሴተኛ አዳሪነት ወጥታ ቋሚ ስራ ማግኘት የቻለችው አደሊን ህይወቷ ባላሰበችው መንገድ እንደተቀየር ትናገራለች። ከሴቶቹ ጋር የማሳልፈው ጊዜ በጣም ነው የሚያስደስተኝ የምትለው አደሊን ''የበፊት ህይወቴ ምን ይመስል እንደነበር ስለሚያሳየኝ የማዝንበት ጊዜም አለ።''

''ምናልባት ከውጭ ሆነን ስንመለከታቸው እነሱ ላይ ለመፍረድ ቀላል ሊሆን ይችላል። እኔ ግን ስላለፍኩበት ችግሩን በደንብ ነው የማውቀው። አማራጭ ቢኖራቸው እነዚህ ሴቶች ያለምንም ጥርጥር ይህንን ስራ ትተው ይወጣሉ።''

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ