ከምድር በታች ተደብቆ የሚገኘው የአሜሪካ መጠባበቂያ ነዳጅ

ሉዊዚያና ውስጥ የሚገኘው የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዋሻ Image copyright Getty Images

በሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ የአሜሪካ ባለስልጣናት በተለያዩ ቦታዎች ለመጠባበቂያ በሚል የተደበቀው ነዳጅ ጥቅም ላይ ስለሚውልበት ሁኔታ ማውራት ጀምረዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት ''የነዳጅ ገበያውን ፍላጎት ለማሟላት መጠባበቂያውን ልንጠቀም እንችላለን'' ብለዋል።

ትራምፕ የሚያወሩለት መጠባበቂያ ነዳጅ ከ640 ሚሊየን በርሜል በላይ የሚሆን ነዳጅ ሲሆን በቴክሳስና ሉዊዚያና ግዛቶች ከጨው በተሰራ ዋሻ ውስጥ ከምድር በታች ተደብቆ የሚገኝ ነው።

ይህ ነዳጅን ደብቆ የማከማቸው ልምድ እ.አ.አ. ከ1970ዎቹ ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል።

ኬንያ የነዳጅ ድፍድፍ ወደ ውጭ መላክ ጀመረች

"ልዩ ነዳጅ መኖሩን አልደረስንበትም" የማዕድን፣ የፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር

ሁሉም የዓለማቀፉ ኤነርጂ ኤጀንሲ አባል ሃገራት ለሶስት ወራት የሚሆን መጠባበቂያ ነዳጅ ማስቀመት እንዳለባቸው የተስማሙ ሲሆን አሜሪካ ደግሞ ከሁሉም በላይ ብዙ መጠባበቂያ እንዳስቀመጠች ይነገራል።

በአሜሪካ ብዙ የነዳጅ ጥርቅም ማስቀመጥ የተጀመረው እ.አ.አ. በ1973 በተካሄደው የአረብ እስራኤል ጦርነት ወቅት አሜሪካ ለእስራኤል ስትወግን ነዳጅ አምራች አረብ ሃገራት ማለትም ኢራን፣ ኩዌት፣ኳታርና ሳዑዲ አረቢያ ወደ አሜሪካ ነዳጅ አንልክም ማለታቸውን ተከትሎ ነበር።

ምንም እንኳን ጦርነቱ ለሶስት ሳምንታት ብቻ ቢቆይም ነዳጅ አምራች ሃገራቱ እገዳውን እስከ 1974 ድረስ በማስቀጠላቸው የነዳጅ ዋጋ በመላው ዓለም በአራት አጥፍ ጨምሮ በወቅቱ 3 ዶላር ይሸጥ የነበረው አንድ በርሜል ነዳጅ ወደ 12 ዶላር ከፍ ብሎ ነበር።

በአሜሪካ በአሁኑ ሰአት አራት የነዳጅ ማጠራቀሚያ ማዕከላት ሲኖሩ የሚገኙትም በቴክሳስ ፍሪፖርት፣ ዊኒ እና ቻርልስ ሃይቅ ወጣ ብሎ እንዲሁም በሉዊዚያና ባቶን ራፍ በሚባል አካባቢ ነው።

እያንዳንዱ መጠባበቂያ እስከ አንድ ኪሎሜትር ጥልቀት ያለው የጨው ዋሻ ሲሆን ነዳጁን በታንከሮች ከማስቀመጥ በዋጋም ሆነ ከደህንነት አንጻር የተሻለ እንደሆነ ይነገርለታል።

በጣም ትልቁ የሚባለውና ፍሪፖርት አካባቢ የሚገኘው ማጠራቀሚያ እስከ 254 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ መያዝ እንደሚችል ይነገርለታል። የመጠባበቂያ ማዕከላቱን የሚከታተለው ተቋም እንዳስታወቀው በአሁኑ ሰአት አሜሪካ በአራቱ መጠባበቂያዎች ውስጥ 644.8 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ አላት።

የአሜሪካው የኃይል መረጃ አስተዳደር ባወጣው መረጃ መሰረት እ.አ.አ. በ2018 አሜሪካውያን በቀን 20.5 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ ይጠቀማሉ። በዚሁ አጠቃቀማቸው የሚቀጥሉ ከሆነ መጠባበቂያው አሜሪካውያንን ለ31 ቀናት ብቻ ማቆየት ይችላል።

በ1975 በወጣው ህግ መሰረት ከባድ የሆነ የነዳጅ እጥረት በአሜሪካ ካጋጠመ መጠባበቂያው ጥቅም ላይ እንዲውል ማዘዝ የሚችሉት ፕሬዝዳንቱ ብቻ ናቸው።

ናይጀሪያ በሙስናዊ ስምምነት 6 ቢሊዮን ዶላር ከነዳጅ አጣች

የምዕራብ ኦሮሚያ ነዋሪዎች ስጋትና ሰቆቃ

ነዳጁ ከሚቀመጥበት ቦታ አስቸጋሪነት የተነሳ ነዳጁን በፕሬዝዳንቱ ትእዛዝ አጓጎዞ ለገበያ ለማቅረብ በትንሹ ሁለት ሳምንት ይፈጃል። ከዚህ በተጨማሪ ነዳጁ ያልተጣራ ስለሆነ በማቀነባበሪያዎች ገብቶ ለመኪና፣ ለአውሮፕላን እና ለመርከብ እንዲሆን ተደርጎ እስኪሰራ ድረስ ብዙ ቀናት መፍጀቱ አይቀርም።

ይህ መጠባበቂያ ነዳጅ ለገበያ የቀረበባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ። ፕሬዝደንት ጆርጅ ቡሽ አንደኛ በ1991ዱ የገልፍ ጦርነት ወቅት ጥቂት የማይባል ነዳጅ ከመጠባበቂያው ሸጠዋል።

ልጃቸው ጆርጅ ቡሽ ሁለተኛ ደግሞ ካትሪና የተባለው አውሎ ነፋስ አሜሪካን ባጠቃ ጊዜ 11 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ ለገበያ አቅርበው ነበር።

ፕሬዝደንት ክሊንተን ደግሞ በ1997 አጋጥሞ የነበረውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ በማሰበ 28 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ሸጠዋል።