ላይቤሪያ የጦር ፍርድ ቤት ለማቋቋም ዓለም አቀፉን ተቋም እያማከረች ነው

ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ Image copyright AFP

የላይቤሪያው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ በሃገራቸው ለማቋቋም ስላሰቡት የጦርና የኢኮኖሚ ወንጀሎች ፍርድ ቤት ጉዳይ ለመምከር ለዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትን ጋበዙ።

ይቋቋማል የተባለው ችሎት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1989-1996 እና 1999-2003 በተካሄዱትና የ250 ሺህ ዜጎችን ህይወት ከቀጠፉት ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንዲመለከት የታለመ ነው።

በእርስ በርስ ጦርነቶቹ ወቅት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በስለት የመቆራርጥና ተገደው የመደፈር ጥቃት አደንዛዥ እፅ በሚጠቀሙ ህጻናት ወታደሮችን በሰማሩ ጨካኝ የጦር አበጋዞች ተፈጽሟል። ጦርነቱንም ለማስቆም ከአካባቢው ሃገራት የተወጣጡ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ሁለት ጊዜ ተሰማርተው ነበር።

የምዕራብ ኦሮሚያ ነዋሪዎች ስጋትና ሰቆቃ

በአባይ ግድብ ላይ ለዓመታት የተካሄድው ውይይት ውጤት አላመጣም፡ ግብጽ

የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ምክትል የፕሬስ ኃላፊ ስሚዝ ቶቢ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፕሬዝዳንት ዊሃ ከዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጋር ናይጄሪያ ውስጥ ለአጭር ጊዜ ተወያይተው ነበር።

"የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንትን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው" ሲሉ ሚስተር ቶቢ ተናግረዋል።

ባሕላዊ መሪዎችንና ሽማግሌዎችን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች ፍርድ ቤቱ እንዲቋቋም ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ፕሬዝዳንት ዊሃም በፍርድ ቤቱ መመስረት ጉዳይ ላይ የሃገሪቱ ምክር ቤት ያለውን ሃሳብ እንዲያካፍል በደብዳቤ ጠይቀዋል።

የደቡብ ኮርያ ፖለቲከኞች ለምን ጸጉራቸውን በአደባባይ ይላጫሉ?

በምክር ቤቱ የተቃዋሚው ሊበርቲ ፓርቲ አባል የሆኑት አብረሃም ዳሪየስ ዲሎን "በሃገራችን ወንጀል ሰርቶ ሳይጠየቁ መቅረትን ልማድ ለማስወገድ ጊዜው አሁን ነው" ሲሉ ፍርድ ቤቱን የማቋቋሙን ሃሳብ በመደገፍ በአንድ ሬዲዮ ላይ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ነገር ግን አንዳንዶች ፕሬዝዳንት ዊሃ ፍርድ ቤቱን ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ለምክር ቤቱ ከማቅረብ ይልቅ ምክር መጠየቃቸውን ተችተውታል። በዚህም አንዳንዶች የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር የፍርድ ቤቱ መመስረት ላይ ጽኑ ፍላጎት ስለሌለው ጉዳዩን የማጓተት ዘዴን እየተጠቀመ ነው ሲሉ ይጠራጠራሉ።

ሄንሪ ኮስታ የተባለው ታዋቂ የሬዲዮ ውይይት ፕሮግራም አስተናጋጅም "ሰውዬው [ፕሬዝዳንቱ] ጨዋታ የያዘ ይመስላል" ሲል ተችቷል።