እስር ላይ የሚገኙት የ'ቡድን 15' የቀድሞ የኤርትራ ባለስልጣናት እነማን ናቸው?

በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ ባልና ሚስት ማህመድ አህመድ ሸሪፎና አስቴር ፍስሐጽዮን
አጭር የምስል መግለጫ በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ ባልና ሚስት ማህመድ አህመድ ሸሪፎና አስቴር ፍስሐጽዮን

ኤርትራ እንደ ነጻ አገር ከተመሰረተች በኋላ አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ያሉት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ ፖለቲካዊ ለውጦችን እንዲያካሂዱ በይፋ ጥያቄ ያቀረቡት ከፍተኛ ባለስልጣናት 15 ነበሩ።

በነጻነት ትግሉ ውስጥና በኋላም በነበሩት ዓመታት በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ከነበሩት አመራሮች መካከል የሆኑት እነዚህ 15 ባለስልጣናት፤ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምርጫ እንዲካሄዱ፣ አገሪቱም በሕገ መንግሥት እንድትተዳደር የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ 1994 ዓ. ም. ጽፈው አሰራጭተው ነበር።

ኤርትራ ፖለቲከኞችን እና ጋዜጠኞችን እንድትለቅ ተጠየቀ

ፕሬዝዳንቱ ለውጥ እንዲያደርጉ በደብዳቤ ጥያቄ ካቀረቡት መካከል 11ዱ በኤርትራ የጸጥታ ኃይሎች ወዲያዉኑ ሲያዙ፤ አራቱ ግን ሳይያዙ ቀርተዋል።

በግልጽ ደብዳቤው ላይ የፖለቲካና የአስተዳደር መሻሻል እንዲደረግ ጥያቄ በማቅረባቸው ለእስር የተዳረጉት ባለስልጣናት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ፣ የት እንዳሉ በይፋ ሳይገለጽ እነሆ 18 ዓመት ሆናቸው። አራቱ እስር ሸሽተው እስካሁን ድረስ በስደት ላይ ይገኛሉ።

በእስር ላይ የሚገኙት ባለስልጣናት ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ምንጮች ከሚወጡ መረጃዎች በስተቀር ምንም አይነት አስተማማኝ ነገር የለም።

ጄነራል ስብሐት ኤፍሬም ወደ ኤርትራ ተመለሱ

ታሳሪዎቹ ባለፉት 18 የእስር ዓመታት ውስጥ ስላሉበት ሁኔታ የቤተሰብ አባሎቻቸውም ይሁኑ ሌሎች ወገኖች የሚያውቁት ነገር ስለሌለ የደህንነታቸው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።

እነዚህ 'ቡድን 15' ተብለው የሚታወቁት ግለሰቦች እነማን ናቸው?

ኡቁባይ አብረሐ፡ የጦር ሠራዊት ጀነራል የነበሩ ሲሆን፤ ቀደም ሲል የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር እንዲሁም የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል። ግለሰቡ እጅግ የከፋ የአስም ህመም እንዳለባቸው ይነገራል።

አጭር የምስል መግለጫ ኡቁባይ አብረሐ

አስቴር ፍስሐጽዮን፡ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ዳይሬክተር፣ የኤርትራ ብሔራዊ የሴቶች ማህበር ሥራ አስፈጻሚ አባል፣ ከ1977 (እአአ) ጀምሮ የኤርትራ ሕዝብ ነጸነት ግንባር ባለስልጣን፣ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩትና አሁን በእስር ላይ የሚገኙት ማህመድ አህመድ ሸሪፎ የቀድሞ ባለቤት ሲሆኑ፤ የሆድ እቃ አልሰር እንዳለባቸው ይነገራል።

አጭር የምስል መግለጫ አስቴር ፍስሐጽዮን

ብርሐነ ገብረእግዚአብሔር፡ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ የሜጀር ጄነራልነት ማዕረግ የነበራቸው ሲሆን፤ የአገሪቱ ተጠባባቂ ሠራዊት ዋና ኃላፊና ከ1977 (እአአ) ጀምሮ የኤርትራ ሕዝብ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ ቢሮ አባል ነበሩ።

ኤርትራ፡"እያስተማሩን ሳይሆን ባሪያ እያደረጉን ነው"

ባራኺ ገብረሥላሤ፡ እስከ ግንቦት 2001 (እአአ) ድረስ በጀርመን የኤርትራ አምባሳደር የነበሩ ሲሆን፤ ቀደም ሲል ደግሞ የትምህርት እንዲሁም የማስታወቂያና ባህል ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል።

አጭር የምስል መግለጫ ባራኺ ገብረሥላሤ፡

ሐማድ ሐሚድ ሐማድ፡ በኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የመካከለኛው ምሥራቅ ክፍል ኃላፊ እንዲሆም በሱዳን የኤርትራ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል።

ማህመድ አህመድ ሸሪፎ፡ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የአገር ውስጥ አስተዳደር ሚኒስትር፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በተጨማሪ የኤርትራ ሕዝብ ነጸነት ግንባርን ከመሰረቱት አንዱ ናቸው።

አጭር የምስል መግለጫ ማህመድ አህመድ ሸሪፎ

ሳሌህ ኬኪያ፡ የትራንስፖርትና ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እንዲሁም የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል።

ጴጥሮስ ሰለሞን፡ የባሕር ኃብት ሚኒስትር፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የኤርትራ ሕዝብ ነጸነት ግንባር ሠራዊት አዛዥና የደህንነት ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፤ ከ1977 (እአአ) ጀምሮም የግንባሩ ፖለቲካ ቢሮ አባል ነበሩ።

አጭር የምስል መግለጫ ጴጥሮስ ሰለሞን

እስጢፋኖስ ስዩም፡ በሠራዊቱ ውስጥ እያሉ የብርጋዲዬር ጀነራልነት ማዕረግ የነበራቸው ሲሆን፤ እስከታሰሩበት ጊዜ ድረስ ደግሞ የአገር ውስጥ ገቢ አገልግሎት ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል።

ኃይሌ ወልደተንሳይ፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ በድንበር ጦርነቱ ወቅት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የገንዘብ ሚኒስትር እንዲሁም የኤርትራ ሕዝብ ነጸነት ግንባር የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊና ከ1977 (እአአ) ጀምሮም የግንባሩ ፖለቲካ ቢሮ አባል ነበሩ። የስኳር ህምም እንዳለባቸው ይነገራል።

አጭር የምስል መግለጫ ኃይሌ ወልደተንሳይ፡

ጀርማኖ ናቲ፡ የክልል አስተዳዳሪ።

እነዚህ ሁለት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ያሉበት ሁኔታ ሳይገለጽ ኤርትራ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ የቀድሞ የኤርትራ ሕዝብ ነጸነት ግንባርና የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ናቸው።

በተለያዩ አገራት በስደት ላይ የሚገኙት የ'ቡድን 15' አባላት ደግሞ መስፍን ሐጎስ፣ አድሐኖም ገብረማሪያም፣ መሐመድ ብርሐን እና ኃይለ መንቆሪዮስ ናቸው።

የኤርትራ መንግሥት ምን ይላል?

በጥር 1995 ዓ. ም. የአገሪቱ ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ እነዚህ 'ቡድን 15' ተብለው የሚታወቁትን ፖለቲከኞች "ከዳተኞች እና ከፋፋዮች" ሲል ገልጿቸው ነበር።

"ፕረዝዳንቱን በኃይል ከስልጣን ለማስወገድ ሞክረዋል" ሲልም ከሷቸዋል።

"አሁን ያገኘነው ሰላም ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው"- ዘማሪ ሳሙኤል ተስፋሚካኤል

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ግን ስለ 'ቡድን 15'ም ሆነ በእስር ላይ ስለሚገኙት የቡድኑ አባላት በየትኛው አጋጣሚ ከመናገር ይቆጠባሉ።

ከዘጠኝ ዓመት በፊት በአንድ የኳታር ጋዜጠኛ ሰለእነዚህ እስረኞች የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ፤ "ስለጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም፤ ይህ ጉዳይ ቢረሳ ይበጃል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በተመሳሳይም ይኸው ጥያቄ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ በአልጀዚራ ጋዜጠኛ ቀርቦላቸው፤ "የታሰሩ አልነበሩም፣ የታሰሩ የሉም፤ የተሳሳተ መረጃ ነው ያለህ" ብለው ፈርጠም ያለ ምላሽ ሰጥተው ነበር።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ