ኤርትራ፡ እንቅስቃሴ አልባዋ የወደብ ከተማ -ምጽዋ

ምጽዋ

ከሦስት ሳምንታት በፊት የቢቢሲ ጋዜጠኞች በኤርትራ አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበረውን ከ15 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድርን እንድንዘግብ ፍቃድ ተሰጥቶን ወደ ኤርትራ እቅንተን ነበር።

በኤርትራ በነበርን ቆይታ ያየነውን እና የሰማነውን በሶስት ክፍሎች አሰናድተናል።

አራተኛው እና የመጨረሻው ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል። ከዚህ በፊት የነበሩ ጽሑፎችን ለመመልከት ከዚህ በታች ያሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጫኑ።

ማሳሰቢያ፡ በኤርትራ በነበረን ቆይታ የዘገባ ርዕሶቻችን እና እንቅስቃሴዎቻችን የተገደቡ ነበሩ።

በጽሁፉ ውስጥ የተጠቀሱት ዓመታት እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር ነው።

የኤርትራ ወጣቶችና ምኞታቸው

የዛሬዋን ኤርትራ የሚገልጹ አስደናቂ እውነታዎች

አሥመራን አየናት፡ እንደነበረች ያለችው አሥመራ


አጭር የምስል መግለጫ ከአሥመራ ወደ መጽዋ ሲያቀኑ አስደናቂ እይታን የሚፈጥረውን ተራራማውን እና ጠመዝማዛውን መንገድ ያቆራርጣሉ።

ምጽዋ ወይም በኤርትራዊያን አጠራር ምጽዋዕ ከመዲናዋ አሥመራ በስተምራቅ በኩል 115 ኪ.ሜትሮችን ርቃ ትገኛለች። ከአሥመራ ወደ ምጽዋ ሲያቀኑ አስደናቂ እይታን የሚፈጥረውን ተራራማውን እና ጠመዝማዛውን መንገድ ያቆራርጣሉ።

በወራሪው ጣሊያን የተሰራው ይህ መንገድ ድንጋያማ ተራሮችን እያቆራረጠ ያልፋል።

ሐምሌ 2010 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በፕሬዝደንት ኢሳያስ ግብዣ ወደ አሥመራ ባቀኑበት ወቅት በለስ የተመገቡበትን አካባቢ አልፈው ነው ምጽዋ የሚደርሱት።

አጭር የምስል መግለጫ ሃሊማ ሞሐመድ አንድ ፍሬ በለስ በአንድ ናቅፋ ትሸጣለች።

ሁለቱ መሪዎች በለሱን የተመገቡበት አካባቢ ''ድርፎ'' ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ በቦታው ብዙ በለስ የሚሸጡ ወጣት ሴቶች ይገኛሉ።

በእዚህ ስፍራ አንድ ፍሬ በለስ በአንድ ናቅፋ ይሸጣል። በስፍራው በለስ ስትሸጥ ያገኘናት ሃሊማ ሞሐመድ ሁለቱ መሪዎች ይህን አካባቢ ከጎበኙ በኋላ ቦታው የበለስ ንግድ የሚዘወተርበት ቦታ እንደሆነ ነግራናለች።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወደ ስፍራው ባቀኑበት ወቅት ነበር በሁለቱ ሃገራት ኤምባሲዎች እንዲከፈቱ፣ አየር መንገዶች በረራ እንዲጀምሩ እና ወደቦችም ሥራ እንዲጀምሩ የተስማሙት።

"ተጨማሪ የፌደራል የሥራ ቋንቋዎች እንዲኖሩ እየተሠራ ነው" ጠ/ሚኒስትር ዐብይ

አጭር የምስል መግለጫ በጣሊያ የቅኝ ግዛት ወቅት ተዘርግቶ የነበረውን እና ግዙፍ ድንጋያማ ተራራን አቆራርጦ ያልፍ የነበረው ባቡር አሁን ላይ ቅሪተ አካሉ ብቻ ነው የቀረው።

ጉዞውን በምስራቅ አቅጣጫ ወደ ምጽዋ ባደረጉ ቁጥር የባህር ወለል ከፍታ እየቀነሰ፤ ሙቀቱም እየጨመረ ይሄዳል። በጉዞው ላይ በጣሊያን የቅኝ ግዛት ወቅት ተዘርግቶ የነበረውን እና ግዙፍ ድንጋያማ ተራራን አቆራርጦ የሚያልፈውን የባቡር መስመር ማስተዋልዎ አይቀርም።

ከበርካታ አስረተ ዓመታት በፊት የተዘረጋው የባቡር መስመር የሚያልፈበትን መልከዓ ምድር ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህን የባቡር ሃዲድ ለመዘርጋት ምን ያክል ትልቅ ድካም እና ገንዘብ ፈሰስ እንደተደረገበት መገንዘብ ይቻላል።

አሁን ላይ ጭው ባለው በረሃ መካከል ቅሪተ አካሉ ብቻ የቀረው የባቡር አካል እና ሃዲድ በዛ በደጉ ዘመን ሰው እና ሸቀጦችን ከወደብ ከተማዋ ምጽዋ ወደ አሥመራ፣ ከረን እና ኡደት ወደሚሰኙ ከተሞች ያመላልስ ነበር።

''የሙት ከተማዋ ምጽዋዕ''

በወደብ ከተማዋ ምጸዋ ሲደርሱ የባህር ወለል ከፍታው ዜሮ መሆኑን ያስታውላሉ። በዚህ ወቅት ላይ የሙቀት መጠኑ እስከ 52 ዲግሪ ሴንቲገሬድ ሊሆን ይችላል። በስፍራው በነበርንበት ወቅት እኩለ ቀን ላይ የሙቀት መጠኑ 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነበር።

አጭር የምስል መግለጫ ምጽዋዕ በአንድ ወቅት ላይ ቅንጡ በነበሩ አሁን ላይ ግን ፈራርሰው ብቻቸውን በተተዉ ህንጻዎች ተሞልታለች።

ከቀይ ባህር ዳርቻ ላይ የምትገኛዋን ጥንታዊ ከተማ ሁኔታዋ የወደብ ከተማ አይነት አይደለም። ምጽዋን "እንቅስቀሴ የማይስተዋልባት የሙት ከተማ" ብሎ መግለጽ ማጋነን ላይሆን ይችላል።

ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በአንድ ወቅት ላይ ቅንጡ በነበሩ አሁን ላይ ግን ፈራርሰው ብቻቸውን በተተዉ ህንጻዎች ተሞልታለች።

በወደብ ከተሞች ላይ ፈጣን የሆነ የሰዎች እና የከባድ መኪኖች እንቅስቃሴዎችን ማስተዋል የተለመደ ነው። ይህ ግን በምጽዋ የለም። በአንድ ስፍራ ተሰባስበው ከቆሙ ጥቂት የደረቅ ጭነት መኪኖች ውጪ ለጥ ባለው ጎዳና ላይ የሚሸከረከር መኪና አይታይም።

አጭር የምስል መግለጫ ከተማዋ እንዲህ በጸጥታ መንፈስ የተመታችበት ሁኔታ ጤናማ አይመስልም።

በጣት በሚቆጠሩት ምግብ ቤቶች ውስጥ እንኳ ሰው አይታይም። ወደ አንዱ ሬስቶራንት ዘልቀው ቢገቡ ከአናትዎ በላይ የሚሽከረከረው የአየር ማቀዝቀዣ ድምጽን ብቻ ነው የሚሰሙት።

ወደ ሥፍራው ይዞን እንዲሄድ የተላከው ሰው፤ "አሁን ሙቀት ስለሆነ ነው። ማታ ላይ ሰዎች ከቤታቸው ይወጣሉ" ብሎናል።

እሱ ይህን ይበል እንጂ ከተማዋ እንዲህ በጸጥታ መንፈስ የተመታችበት ሁኔታ ጤናማ አይመስልም።

አጭር የምስል መግለጫ ምጽዋ ወደብ

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከደረሱት የሰላም ስምምንት በኋላ ለምጽዋ ወደብ አንዳንድ ለውጦች እንደተደረጉለት ሰምተናል። ይሁን እንጂ እኛ ወደ ሥፍራው በሄድንበት ወቅት ወደ ወደቡ መጠጋት እስከሚቻለው ስፍራ ድረስ ቀርበን እንደተመለከትነው በወደቡ ዙሪያ የተመለከትነው እንቅስቃሴ የለም።

ግዙፍ መርከቦች ቆመዋል። ክሬኖችም እንዲሁ። የመጫን እና የማውረድ ሥራዎች ግን የሉም።

አጭር የምስል መግለጫ በምጽዋ ወደብ ግዙፍ መርከቦች ክሬኖችም ይታያሉ የመጫን እና የማውረድ እንቅስቃሴዎች ግን አይታዩም

ቀይ ባህር ከኤርትራም አልፎ ለጎረቤት ሃገራት ትልቅ የተፈጥሮ ጸጋ ነው። የቀይ ባህር ዳርቻ በዛ ሞቃታማ ስፍራ በዋና ራስን ቀዝቀዝ እና ዘና ለማድረግ ምቹ ስፍራ ነው።

ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ ሰዎች ከባህር ዳርቸው ሰፍራ ላይ ይዝናናሉ። የቀይ ባህር ዳርቻን ሲዋኙ የተመለከትናቸው ሰዎች ቁጥር በከተማዋ ካስተዋልናቸው ሰዎች ቁጥር በላይ ስለመሆናቸው ጥርጥር የለውም።

ባህር ዳርቻው ላይ የሚገኙት ጥቂት ሆቴሎች አስርት ዓመታትን ያስቆጠሩ ናቸው።

አጭር የምስል መግለጫ ቀይ ባህር ላይ የሚዝናኑ ሰዎች

ሌተናል ኮሎኔል ጌታቸው መርሃ ጽዮን (ኢንጅነር) የፕሬዝደንቱ አማካሪ እና የመረጃ እና ካርታ ኃላፊ ናቸው። ኃላፊው በወደብ ከተማዋ ምጽዋ የሚፈለገው አይነት የንግድ እንቅስቃሴ እንደሌለ ይስማማሉ።

የመይሳው ካሳ የልጅ ልጆች

"እንደ ጦርነት የከፋ ነገር የለም። ከልማት ይልቅ ሉዓላዊነታችንን የማስከበር ሥራ ላይ ተጠምደን ነው የቆየነው። አሁን ሁሉም ነገር ተቀይሯል" ይላሉ።

ኃላፊው ከዚህ በተጨማሪ ኤርትራ ማዕቀብ ተጥሎባት የቆየች ሃገር መሆኗን በማስታወስ በወደብ ከተሞች የወጪ ገቢ እንቅስቃሴ በስፋት የማይስተዋልበትን ምክንያት ይህ መሆኑን ያስረዳሉ።

ኤርትራ መቀመጫውን ሶማሊያ ላደረገው አል-ሸባብ የቁሳቁስና የስልጠና ድጋፍ ታደርጋለች በሚል እአአ በ2009 ላይ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ተጥሎባት ነበር።

ማዕቀቡ የጦር መሳሪያ ዝውውርን እና ንብረት ማንቀሳቀስ እገዳን ጨምሮ የባለስልጣናት ጉዞ ላይ ጭምር አሉታዊ ተጽእኖን ፈጥሮ ቆይቷል።

ከአል-ሸባብ ጋር ምንም አይነት ግነኙነት እንደሌላት በተደጋጋሚ ስታስተባብል የቆየችው ኤርትራ፤ ተጥሎበት የቆየው ማዕቀብ ላደረሰባት የምጣኔ ሃብት ቀውስ ካሳ እንደምትጠይቅ መሪዎቿ ተናግረው ነበር።

ኤርትራ ካሳ ጠየቀች

እንደ የመረጃ እና ካርታ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ጌታቸው ከሆነ፤ ከዓመት በፊት ማዕቀቡ መነሳቱ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጋር የሰላም ስምምነት መደረሱን ተከትሎ ኤርትራ በምጽዋ ብዙ የልማት መረሃ-ግብሮች እንደተያዙ እና ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ በረከቶችን ይዘው እንደሚመጡ ተስፋ ሰንቀዋል።

ተስፋ ከተጣለባቸው ፕሮጅከቶች መካከል ደግሞ አንዱ ደግሞ ከ20-30 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው የጸሃይ ኃይል ማመንጫ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ