"ምን ያህል ጊዜ ጥቁር ቀለም እንደተቀባሁ አላስታውስም" የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ

ጀስቲን ትሩዶ ፊታቸውን ጥቁር ቀለም ተቀብተው የሚያሳዩ ፎቶግራፎች Image copyright Globe and Mail, Global News, Time Magazine
አጭር የምስል መግለጫ ጀስቲን ትሩዶ ፊታቸውን ጥቁር ቀለም ተቀብተው የሚያሳዩ ፎቶግራፎች

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ ወጣት ሳሉ ምን ያህል ጊዜ ፊታቸውን ጥቁር ቀለም እንደተቀቡ እንደማያስታውሱ መግለጻቸው እያነጋገረ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከዓመታት በፊት በአንድ የግል ትምህርት ቤት ድግስ ላይ ፊታቸውን እና እጃቸውን ጥቁር ቀለም ተቀብተው የሚያሳይ ፎቶግራፍ ይፋ ከተደረገ በኋላ በርካቶች እየወቀሷቸው ይገኛሉ።

ይህ ፎቶ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጥቁር ቀለም ተቀብተው የሚያሳዩ ሌሎች ፎቶግራፎችም እየወጡ ነው።

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ በዘረኛ ፎቶግራፋቸው እየተተቹ ነው

ሴቶችን እያነቀ የገደለው ኮሪያዊ ከ30 ዓመታት በኋላ ተገኘ

"ዛሚ አልተሸጠም፤ በትብብር እየሠራን ነው" ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ

በግል ትምህርት ቤት ድግስ ላይ ጥቁር ቀለም ተቀብተው የተነሱት ፎቶግራፍ ለሕዝብ ይፋ መሆኑን ተከትሎ፤ ጋዜጠኞች ጠቅላይ ሚንስትሩ ሌሎች ተመሳሳይ ፎቶዎች ተነስተው እንደሆነ ጠይቀዋቸው ነበር። ጀስቲን ከዛ ፎቶ ውጪ፤ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳሉ በተሰጥኦ ውድድር ላይ ጥቁር ቀለም መቀባታቸውን ተናግረው ነበር።

ከነዚህ ውጪ በሌላ ወቅት ተመሳሳይ ድርጊት ስለመፈጸማቸው አልተናገሩም ነበር። አሁን ተጨማሪ ቪድዮና ፎቶ ሲወጣ፤ ምን ያህል ጊዜ ጥቁር ቀለም እንደተቀቡ እንደማያስታውሱ ገልጸዋል።

የፊታችን ጥቅምት ካናዳ አገራዊ ምርጫ ታካሂዳለች። ለሁለተኛ ጊዜ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉት ጀስቲን በዘረኛ ፎቶዎቻቸው ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸውን ይሥሉ የነበረው የማኅበራዊ ፍትህ አቀንቃኝ፣ ተራማጅና ልዩነትን የሚያከብሩ እንደሆኑ ነበር። ሆኖም ለሕዝብ ይፋ የተደረጉት ፎቶዎች የጀስቲንን ገጽታ እንዳጠለሹት ተገልጿል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1990ዎቹ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ነጭ ካናቴራ ለብሰው፣ ፊታቸውን እና ክንዳቸውን ጥቁር ቀለም (ሜክ-አፕ) ተቀብተው የሚያሳይ ቪድዮ ተለቋል። በቪድዮው ላይ ጀስቲን እጃቸውን እያወናጨፉ ምላሳቸውን ሲያወጡ ይታያል።

ይህ ቪድዮ የተቀረጸው ጠቅላይ ሚንስትሩ በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሳሉ ነበር። የግል ትምህርት ቤት ድግስ ላይ ጥቁር ቀለም ተቀብተው የተነሱት ፎቶ የተወሰደው በ29 ዓመታቸው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተሰጥኦ ውድድር ላይ ጥቁር ቀለም ተቀብተውም ዘፍነዋል። ጀስቲን፤ "ማድረግ የማይገባኝን አድርጌ ብዙዎችን አስቀይሜያለሁ" ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል።

የአገሪቱ መከላከያ ሚንስትር ሀሪጂት ሳጃን፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ስህተት መሥራታቸውን ለካናዳ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ልዩነትን የሚያከብር ፓሊሲ እንዳላቸው ሳይጠቅሱ ግን አላለፉም።

የተቀናቃኙ 'ኮንሰርቫቲቭ' (ወግ አጥባቂ) ፓርቲ መሪ አንድሪው ሺር የጠቅላይ ሚንስትሩን 'ይቅርታ' አጣጥለው "ይቅርታው የውሸት ነው" ብለዋል።