የጥንታዊ ሰው የፊት ገጽታ ይፋ ተደረገ

የ 'ዴኒሶቫን' ቅሪተ አካል የተገኘው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2008 ላይ ነበር Image copyright Maayan Harel
አጭር የምስል መግለጫ የ 'ዴኒሶቫን' ቅሪተ አካል የተገኘው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2008 ላይ ነበር

ተመራማሪዎች፤ 'ጥንታዊ ሰዎች ምን ይመስሉ ነበር?' ለሚለው ጥያቄ መልስ አግኝተናል እያሉ ነው።

'ዴኒሶቫን' የሚባለው የሰው ዝርያ ፊቱ ምን እንደሚመስል እንደደረሱበት ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል። የዝርያውን ከአንገት በላይ ያለ ገጽታ የሚያሳይ ምስል ሠርተውም ይፋ አድርገዋል።

የዴኒሶቫን ቅሪተ አካል የተገኘው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2008 ላይ ሲሆን፤ ይህ የሰው ዝርያ ከምድረ ገጽ ከጠፋ 50,000 ዓመታት ተቆጥረዋል።

ተመራማሪዎች ቅሪተ አካሉን ሲያገኙ፤ 'ለመሆኑ ጥንታዊው ሰው ምን ይመስል ነበር?' የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር። የተገኘው ቅሪተ አካል ላይ የጸጉር፣ የቅንድብ፣ የአይን፣ የአፍንጫ፣ የከንፈር እና የጥርስ ምስል በማከል ለጥያቄያቸው መልስ አግኝተዋል።

በአፋር 3.8 ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠረ ሙሉ የራስ ቅል መገኘቱ ተገለጸ

የሉሲ ታላቅ በደቡብ አፍሪካ ተገኘች

የሠላም ተጓዧ ሉሲ (ድንቅነሽ) ምን ደረሰች?

'ዴኒሶቫን' የሚባሉት የሰው ዝርያዎች እነማን ነበሩ?

ከ100,000 ዓመታት በፊት የዘመናዊ ሰው ዝርያ (ኒያንደርታል) ጨምሮ የተለያዩ ዝርያዎች ነበሩ። ከዝርያዎቹ መካከል ዴኒሶቫንም ይጠቀሳል።

'ሂብሩ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ጀሩሳሌም' በተባለ ተቋም ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሊራን ካርሜል እንደሚሉት፤ ዴኒሶቫን እና ኒያንደርታልን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ።

"ዴኒሶቫን በብዙ መንገድ ከኒያንደርታል ጋር ይመሳሰላሉ። በተወሰነ ሁኔታ ከኛ ጋርም ይቀራረባሉ"

ዴኒሶቫን በሳይቤርያ እንዲሁም በምሥራቅ እስያም ይኖሩ እንደነበረ ይታመናል። በቲቤት ተራራማ አካባቢዎች ሲኖሩ፤ ዘመናዊ የሰው ልጅ ከፍታ አካባቢ እንዲኖር የሚያስችል 'ጂን' [የዘር ቅንጣት] እንዳሸጋገሩም ይነገራል።

ከምድር ገጽ የጠፉበት ምክንያት ግን እስካሁን አልታወቀም።

Image copyright Maayan Harel
አጭር የምስል መግለጫ ዴኒሶቫን እና ኒያንደርታልን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ

ዴኒሶቫን ምድር ላይ ኖረው እንደነበረ የታወቀው ከአሥር ዓመት በፊት ሳይቤርያ የሚገኝ ዋሻ ውስጥ የጥርስ፣ የጣትና መንጋጋ ቅሪተ አካላቸው ሲገኝ ነበር።

የተሠራው የፊት ገጽታ ምን ይነግረናል?

ተመራማሪዎች የጥንታዊውን ሰው የፊት ገጽታ መሥራት የቻሉት የዴኒሶቫን፣ የኒያንደርታል፣ የቺምፓንዚ እና የሰው ልጆችን ዘረ-መል ተመርኩዘው ነው።

የዴኒሶቫን የራስ ቅል ከኒያንደርታል ይሰፋል። አገጭም የላቸውም።

ፕሮፌሰር ሊራን ካርሜል ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ይፋ የተደረገው የፊት ገጽታ፤ ዴኒሶቫን ላይ ለሚሠሩ ተጨማሪ ጥናቶች መነሻ ይሆናል።

"ከኛ ጋር በጣም የሚቀራረብ የሰው ዝርያ ነው። ከኛ ጋር ያላቸውን ልዩነትም መረዳት ያስፈልጋል" ሲሉ አብራርተዋል።