ኢትዮጵያ በዚህ ወር ልታመጥቀው የነበረውን ሳተላይት ወደ ታህሳስ ማዘዋወሯ ተነገረ

የእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል Image copyright ZACHARIAS ABUBEKER

ኢትየጵያ በዚህ ወር ልታመጥቀው የነበረው ሳተላይት ወደ ታህሳስ 17 ቀን 2012 ዓ. ም. መዘዋወሩን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት (Earth Observation Satellite) በዚህ ዓመት መባቻ ላይ ከቻይና ለማምጠቅ እቅድ ይዛ እንደነበረ ይታወሳል።

ዶ/ር ሰለሞን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ሳተላይቱን የምትቆጣጠርበት እና የምታዝበትን ጣቢያ (ግራውንድ ስቴሽን) በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት መሞከር ስላልተቻለ፤ ሳተላይቱ የሚመጥቅበት ቀን ተሸጋግሯል።

ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቅ ለምን አስፈለጋት?

በሳተላይቶች ዙሪያ ሰባት አስደናቂ እውነታዎች

ኬንያ ሳተላይት ልታመጥቅ ነው

የሳተላይት ግንባታው በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቁን ገልጸው፤ መቆጣጠሪያ ጣቢያው በአግባቡ ሳይሞከር ሳተላይቱን ማምጠቅ ስለማይቻል፤ ከቻይና አጋሮቻቸው ጋር በመመካከር ወደ ታህሳስ ለማዘዋወር መወሰናቸውን አስረድተዋል።

"የጣቢያው ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፤ የሚቀረን መሞከር ነው። ታህሳስ ላይ መቶ በመቶ ይመጥቃል" ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

ይህ ሳተላይት ከምድር ወደ ህዋ ከተመነጠቀ በኋላ መሬትን እየቃኘ መረጃዎችን በፎቶ ይመዘግባል። እንደያስፈላጊነቱም መረጃውን ወደ ምድር ይልካል።

አፍሪካ ውስጥ እስካሁን ሳተላይቱን ያመጠቁ በጣት የሚቆጠሩ አገሮች ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያም የአምጣቂዎቹን ቡድን ለመቀላቀል ከሦስት ዓመት በፊት መሰናዶ መጀመሯ ይታወሳል።

ዓለም ላይ ሳተላይት ማምጠቂያ (ላውንቸር) ያላቸው ጥቂት አገሮች ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ባደረገችው ስምምነት መሰረት፤ ሳተላይቱ ከቻይና የሚመጥቅ ይሆናል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ሳተላይቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት አስቀድሞ ለመተንበይ፣ ደህንነትን ለመጠበቅ ወዘተርፈ ይውላል። የደን ቁጥር፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎችም መረጃዎች ከተሰበቡ በኋላ እንደ ጎርፍ ያሉ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት መተንበይ እና መከላከል ይቻላል።

ዶ/ር ሰለሞን ስለ ሳተላይቱ ሲያብራሩ፤ አንድ የግብርና አካባቢን የሚያሳይ ፎቶግራፍ ስለ እርሻ መሬቱ፣ ስለ ውሀው፣ ስለ አፈሩ ዝርዘር መረጃ ይሰጣል ይላሉ። መረጃዎቹን በመጠቀም ምርታማ የሆኑ አካባቢዎችን መለየት፣ የምርት መጠንን በትክክል ማወቅም ይቻላል።

ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ በመጡባት ኢትዮጵያ፤ ፋብሪካዎች የት መገንባት አለባቸው? ለሚለው ጥያቄ የሳተላይቱ መረጃ መልስ ሊሰጥ ይችላል።

ሕዝብ መቁጠር ሲያስፈልግ ከዘልማዳዊው መንገድ ሳተላይቱን መጠቀም ይመረጣል። ትክክለኛ መረጃ ከማግኘት፣ ገንዘብና የሰው ሀይል ከማዳን አንጻርም የተሻለው አማራጭ ነው።

ኢትዮጵያ እነዚህን መረጃዎች ሳተላይት አምጥቀው ፎቶ ከሚያስነሱ አገሮች ትሸምት እንደነበርም ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።

የሳተላይቱ ግንባታ የተጀመረው ከቻይና በተገኘ 6 ሚሊየን ዶላር ሲሆን፤ ቻይናውያን ኢንጂነሮች ኢዮጵያውያንን እያሰለጠኑ ሳተላይቱ ቻይና ውስጥ እንዲሁም በከፊል ኢትዮጵያ ውስጥ ተገንብቷል።