በተያዘው ዓመት ለሁለት የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፍቃድ ይሰጣል ተባለ

የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ባልቻ ሬባ።
አጭር የምስል መግለጫ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ባልቻ ሬባ።

የኢትዮጵያ የኮሚኒኬሽን ባለስልጣን በያዝነው አዲሱ 2012 ዓመት ለሁለት የቴሌኮም ተቋማት ፍቃድ እንደሚሰጥ አስታወቀ።

ይህን ያሉት በቅርቡ በጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕምድ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ተደርገው የተሾሙት አቶ ባልቻ ሬባ ናቸው።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባጸደቀው አዋጅ ቁጥር 1148/2011 መሰረት፤ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን የቴሌኮም ዘርፉን በመቆጣጠር በዘርፉ ለሚሰማሩ የግል ተቋማት የውድድር ገብያውን ምቹ ለማድረግ የተቋቋመ ነው።

የኢትዮ ቴሌኮም 49 በመቶ ድርሻ ለሽያጭ ይቀርባል ተባለ

የውጪ ሀገር ጥሪዎች ለምን በኢትዮጵያ ቁጥር ይወጣሉ?

አቶ ባልቻ ሬባም ተቋሙን ከያዝነው አዲስ ዓመት ጀምሮ በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ ተሹመዋል።

"ይህ ተቋም በዚህ ዓመት ለመፈጸም ካቀዳቸው ዋና ተልዕኮዎች መካከል፤ ለሁለት በቴሌ-ኮሚዩኒኬሽን ኦፐሬሽን ለሚሰሩ ተቋማት ፍቃድ መስጠት ነው" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መንግሥት ከዚህ በፊት 51 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ በእራሱ ሥር አቆይቶ 49 በመቶውን ደግሞ ወደ ግል ለማዘዋወር ፍላጎት እንዳለው ማስታወቁ ይታወሳል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መንግሥት የቴሌኮም ዘረፉ ለግል ድርጅቶች ክፍት እንደሚደረግ ይፋ ካደረገ በኋላ በርካታ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ገብያ ላይ ፍላጎት ሲያሳድሩ ቆይተዋል።

አየር መንገድንና ቴሌን ለሽያጭ ለማቅረብ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው?

"ከስድስት ወራት በኋላ ፍቃድ ወደመስጠቱ ሥራ እንገባለን" የሚሉት አቶ ባልቻ የአውሮፓውያኑ 2019 ከመጠናቀቁ በፊት የቴሌኮሚኒኬሽን ኦፕሬሽን ፍቃድ ይሰጣል ተብሎ ነበር ይላሉ።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ከሆነ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን ፍላጎት ያላቸው ተቋማት የንግድ ሃሳባቸውን እንዲያስገቡ ጥሪ ሲያቀርብ በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ተቋማት ጥሪውን መሰረት አድርገው ገቢ ያደርጋሉ። እስከዛው ግን የንገድ ሃሳብ ገቢ ማድረግ እንደማይቻል ይናገራሉ።

''የቴሌኮሚዩኒኬሽን ኦፐሬሽን ፍቃድ የሚሰጣቸው ተቋማት የውጪ ሃገር፣ የሃገር ውስጥ ወይም በሽርክና የሚሰሩ ሊሆኑ ይችላሉ" ብለዋል።

ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሆነው ይህ ባለስልጣን ያልተገቡ የገበያ ውድድሮችን ከመቆጣጠር እስከ የቴሌኮም አገልግሎት ፍቃድ እስከመሰጠት ስልጣን ተሰጥቶታል።

"ለቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፍቃድ ይሰጣል፣ የቴሌኮሚዩኒኬሽን እና ፖስታ አገልግሎት ላይ መሰማራት ለሚፈልጉም ፍቃድ ይሰጣል፤ እንዲሁም ኦፐሬተሮች ለህዝብ የሚሰጡት የአገልግሎት ደረጃን ይወስናል" ይላሉ።

ፍቃድ የተሰጣቸው የቴሌኮም ኦፐሬተሮች አገልግሎት የሚሰጡበትን ታሪፍ ለባለስልጣኑ ካቀረቡ በኋላ ባለስልጣኑ የመጨረሻውን ውሳኔ እንደሚሰጥበትም ተናግረዋል።

መንግሥት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝለትን ኢትዮ ቴሌኮምን የ49 በመቶ ድረሻ ለግል ለማዘዋወር ክፍት ማድረጉ ስህተት ነው የሚሉም አልታጡም።

አቶ ባልቻ ግን መንግሥት በብቸኝነት ከኢትዮ ቴሌኮም ሲያገኝ ከነበረው በላይ ገቢ እንደሚያገኝ ይናገራሉ። ይህም የሚሆነው ከግብር እና ከፍሪኩዌንሲ ከሚገኝ ገቢ እንደሆነ ይናገራሉ።

"ለሞባይል ኦፐሬተሮች ፍቃድ የምንሰጥበት ፍሪኩዌንሲ ከፍተኛ ገቢ የሚያመጣ ነው" ብለዋል።

እስካሁን ኢትዮ ቴሌኮም ፍሪኩዌንሲ በነጻ እየተጠቀመ ነበር ማለት ይቻላል የሚሉት አቶ ባልቻ፤ ከአሁን በኋላ የሚመጡት ተቋማት ግን ብዙ ገንዘብ እንደሚከፍሉ ያስረዳሉ።

በተጨማሪም፤ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸው የቴሌኮም ኢንቨስትመንትን ያስፋፋል፣ የጥራት አገልግሎት ያሳድጋል፣ የቴሌኮም አገልግሎት ወጪን ይቀንሳል እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎትን ያሻሽላል በማለት ጠቀሜታውን ያስረዳሉ።

አቶ ባልቻ ሬባ ማናቸው?

አቶ ባልቻ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተርነት ባሉ በሃላፊነቶች አገልግለዋል።

ለ7 ዓመታት በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር የስታንዳርድና ቁጥጥር ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል።

አቶ ባልቻ የኢትዮጵያ የኮሚኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴሌ-ኮም፣ ፖስታ እና ኮሚዩኒኬሽን የስታንዳርድና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆንም አገልግለዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ