የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ 300ሺህ ተማሪዎችን ለመመገብ እየተዘጋጀ ነው

ተማሪዎች Image copyright AFP Contributor

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማው ትምህርት ቢሮ በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ300 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመገብ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ።

የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ወደ 300ሺህ የሚጠጉ በመጀመሪያ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎችን ለመመገብ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

“ከተማ አስተዳደሩ የወሲብ ንግድን በህግ ወንጀል የማድረግ ስልጣን የለውም” የህግ ባለሙያ

በአዲስ አበባ ተማሪዎች በዲዛይነሮች የተዘጋጀ የደንብ ልብስ ሊለብሱ ነው

"ከዚህ በፊት 70ሺህ ተማሪዎችን ስንመግብ ነበር። የምገባ ፕሮግራሙ የተማሪዎች የትምህርት ቅበላ አቅምን ከፍ ማድረጉን ስለተመለከትን ቁጥሩን ከፍ አደረግነው እንጂ፤ ምገባው የነበረ ነው።" ሲሉ አቶ ዘላለም ተናግረዋል።

"በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎችን ስንመግብ ቆይተናል፤ አሁን ግን መርሃ ግብሩ በሁሉም ትምህርት ቤት ነው የሚከናወነው'' የሚሉት አቶ ዘላለም፤ የመመገቢያ አዳራሽ እና ማብሰያ ቦታዎች እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ ትምሀርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩት አብዛኛዎቹ የተማሪዎች ወላጆቻቸው አነስተኛ ገቢ ያላቸው መሆኑን ያነሱት አቶ ዘላለም፤ "ልጆቻቸውን መግበው ወደ ትምህርት ቤት መላክ የማይችሉት በርካቶች ናቸው" ይላሉ።

መርሃ ግብሩ የተማሪዎችን የትምህርት መቀበል አቅም ከፍ ከማድረጉ በተጨማሪ፤ በምግብ እጥረት ከትምህርት ቤት ይቀሩ የነበሩ ተማሪዎችን ቁጥር እንደሚቀንስ ይናገራሉ።

360 ብር ለአንድ ሕጻን

በአሁኑ ወቅት በጣም ተፈላጊ የሆኑ የዲጂታል ዘርፍ ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?

የምገባ ፕሮግራሙን ወጪ የከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፍነው የሚናገሩት አቶ ዘላለም፤ ግብዓቶችን በማቅረብ እና በማብሰል ደግሞ የተማሪ ወላጆች ተደራጅተው እንደሚሳተፉ አክለዋል።

"ይህ ፕሮግራም ለወላጆችም የሥራ እድል እየፈጠረ ነው" ሲሉ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ይጠቅሳሉ።

አቶ ዘላለም ጨምረው እንደተናገሩት በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እየተካሄዱ የሚገኙት እድሳቶች ስላላለቁ የዘንድሮ ትምህርት ዘመን የፊታችን ሰኞ ላይጀምር ይችላል ብለዋል።

"እድሳቶቹ ባለመጠናቀቃቸው፤ እስከ ዓርብ ድረስ አይተን ትምህርት የሚጀመርበት ቀን ልናራዝም እንችላለን " ብለዋል።