የዙሉው ንጉሥ ማኮላሸት አስገድዶ መድፈርን ያስቀራል አሉ

ንጉሥ ጉድዊል ዝዌሊቲኒ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ንጉሥ ጉድዊል ዝዌሊቲኒ

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙት የዙሉ ግዛት ንጉሥ ጉድዊል ዝዌሊቲኒ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተይዘው ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠባቸው ግለሰቦች መኮላሸት ይገባቸዋል ማለታቸው ተዘገበ።

አንድ የደቡብ አፍሪካ ድረገጽ ንጉሡ በአንድ ክብረ በዓል ላይ ለሕዝባቸው ያደረጉትን ንግግር ጠቅሶ እንደዘገበው አሳሳቢ የሆነውን አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ለማስቆም ማኮላሸት መፍትሄ ነው ብለዋል።

ንጉሥ ጉድዊል ዝዌሊቲኒ "ማኮላሸት አስገድዶ መድፈርን ያስቆማል። ይህም የዙሉ ግዛት እንዲህ አይነቱን አሳፋሪ ድርጊት ፈጽሞ እንደማይታገሰው ለዓለም በሚያሳይ ሁኔታ መፈጸም አለበት" ማለታቸው ተጠቅሷል።

ደቡብ አፍሪካዊው 32 ሴቶችን በመድፈር 32 የተለያየ የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

በምዕራብ ጎጃም ታራሚ አስገድዶ የደፈረው ፓሊስ የእስራት ጊዜ ተጨመረበት

አክለውም አስገድዶ የወንጀል ድርጊቱን በፈጸሙት ሰዎች ላይ የሚወሰደውን የማኮላሸት ርምጃም "እኛን የመሰሉ ወንዶች ያከናውኑታል" ማለታቸውም ተነግሯል።

ንጉሡ ይህን የተናገሩት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ የሃገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ዋነኛ የዘገባ ርዕስ መሆኑን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ሳምንት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲለሪል ራማፎሳ በፓርላማ ውስጥ ባደረጉት ንግግር ላይ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አሃዝ በጦርነት ውስጥ ካለ ሃገር ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በመግለጽ የጉዳዩን አሳሳቢነት አመልክተዋል።

ከፈረንጆቹ 2018 ሚያዚያ ወር ወዲህ 41 ሺህ ሴቶች ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል። ይህም አሃዝ በየ15 ደቂቃው ከአንዲት ሴት በላይ የጥቃቱ ሰለባ ትሆናለች ማለት ነው።

ተማሪዎች አስገድዶ ስለመድፈር በመቀለዳቸው ታገዱ

ባሏን በስለት የገደለችው ኑራ ሁሴን

የዙሉው ንጉሥ ጉድዊል ዝዌሊቲኒ በተጨማሪም "ግርዛትን እንደምናከናውነው ሁሉ አሁን ከዚህ ከፍ ያለ ቅጣትን መጣል አለብን። ደንብና ሥርዓትን ላስቀመጠው ለቀድሞ ንጉሣችን ሻካና ለማኅበረሰባችን ክብር ስንል ማኮላሸትን ሕጋችን ልናደርገው ይገባል። መከባበርን ወደ ቦታው መመለስ ይገባናል" ብለዋል።

ነገር ግን ለጾታ ፍትህ በሚሰራ አንድ ተቋም ውስጥ ያለ የመብት ተከራካሪ ይህንን ጥሪ ተቃውሞታል። በሴቶች ላይ የሚፈጸምን ጥቃት ለማስቆም "አስከፊ ድርጊትን በፈጻሚዎቹ ላይ ማድረግ ፈጽሞ ለችግሩ መፍትሄ አይሰጥም" ማለቱ ተዘግቧል።

አስገድዶ ደፋሪዎች እንዲኮላሹ ጠንካራ ጥሪ ያቀረቡት ንጉሥ ጉድዊል ዝዌሊቲኒ ምንም እንኳን ፖለቲካዊ ስልጣን ባይኖራቸውም በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ትልቁ በሆነው የዙሉ አባላት ዘንድ ተሰሚነትና ተጽእኖ የመፍጠር አቅም አላቸው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ