የመጀመሪያ ዙር 75 ስደተኞች ሩዋንዳ ገቡ

የመጀመሪያ ስደተኞች በሊቢያ

ሩዋንዳና እና የዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም በገቡት ውል መሠረት 75 ስደተኞች ሊቢያን ለቀው ኪጋሊ ገብተዋል።

ሩዋንዳ ከገቡት ስደተኞች መካከል አብዛኛዎቹ ተንከባካቢ የሌላቸው ሕፃናት እና እርዳታ የሚሹ ናቸው ተብለዋል።

የሩዋንዳ ስደተኞች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቃል-አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ስደተኞቹ ከኪጋሊ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው ቡጌሴራ መንደር ወስጥ ይሰፍራሉ።

ሩዋንዳ ከአፍሪቃ ሕብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ወኪል ጋር በያዝነው ወር መባቻ አዲስ አበባ ላይ በገባችው ቃል መሠረት 500 ስደተኞች ትቀበላለች።

በስምምነቱ መሠረት ስደተኞቹ ሩዋንዳ ውስጥ የመኖር መብት እንዲሰጣቸው ይደረጋል፤ ፈቃደኛ ከሆኑ ደግሞ ወደ ገዛ ሃገራቸው እንዲመለሱ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

የሜዲትራኒያንን ባሕርን ቀዝፈው ወደ አውሮጳ ለመግባት በማሰብ የተሰደዱ 4500 ገደማ ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይነገራል።

አብዛኛዎቹ ከአፍሪቃ ቀንድ እንደመጡም ተዘግቧል።

ሊቢያን ረግጠው አውሮጳ መድረስ ያልቻሉ አፍሪቃውያን ስደተኞች ትሪፖሊ ውስጥ በደላሎች ከፍተኛ ግፍ እየተፈፀመባቸው እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

አንዳንድ ስደተኞች እንደ ባሪያ እየተሸጡ እንዳሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ወጥቶ ዓለምን ጉድ እንዳሰኘ አይዘነጋም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ