ጤፍ ከእንጀራ አልፎ አሜሪካ ውስጥ ቢራ ሆነ

የጤፍ ቢራ Image copyright NEGUS BREWERY FACEBOOK

ከጤፍ የተሠራው "አዲስ ጤፍ አምበር ኤል" የሚል ስያሜ የተሰጠው ቢራ ሰኞ ዕለት በአሜሪካ ለገበያ መቅረቡን የአምራች ኩባንያው ንጉሥ ቢራ የሥራ ተወካይ አቶ ሚካኤል አለሙ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በዕለቱም በሦስት የአሜሪካ ግዛቶች ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ ውስጥ ለተደረገው ሥርጭት 20 ሺህ ጠርሙሶች ከጤፍ የተመረተ ቢራ ቀርቧል።

በኢትዮጵያዊያንና በኤርትራዊያን ዘንድ ዋነኛ ምግብ የሆነውን የጤፍ እህልን ወደ ቢራነት መቀየሩ አዲስ ሃሳብ ከመሆኑ አንፃር 'አዲስ የሚል ስያሜ የተሰጠበትን ምክንያት አቶ ሚካኤል ያስረዳሉ።

ጤፍን ሰዳ የምታሳድደው ኢትዮጵያ

ቢራው ከሠርገኛ ጤፍ የተሰራ ሲሆን የአልኮል መጠኑም 5.4 በመቶ ነው። ለጊዜው አንድ አይነት ቢራ ብቻ የቀረበ ሲሆን ከነጭ ጤፍ የተሰራውም በቅርቡ ለገበያ እንደሚውል እቅድ ተይዟል።

የጤፍ እህል እጥረትም ሆነ ስጋት እንዳይፈጠር፤ የጤፍ ምርታቸውን ከአሜሪካ ከሚገኙ ገበሬዎች የሚያገኙ ሲሆን አሜሪካ ለሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ተጠቃሚዎችን ፍላጎት በማይነካ መልኩ እየሠሩ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

ጤፏን ለማስመለስ እየተውተረተረች ያለችው ኢትዮጵያ

"ጤፍን ለቢራነት ስንጠቀም ሊወደድብን ይሆን የሚል ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል" የሚሉት አቶ ሚካኤል እሱ እንደማይፈጠርም ያስረዳሉ።

ለወደፊቱም ጤፍ ዘርተውና አብቅለው ቢራውን የማምረት እቅድንም ይዘዋል።

ቢራ ከጤፍ ለምን?

ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ የተለያዩ አዝርዕቶችና መገኛ ብትሆንም የሕዝቡም ሆነ የአገሪቷ ተጠቃሚነት በጣም ዝቅተኛ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሚካኤል፤ የጤፍ ምርትንም እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ።

የጤፍ ምርትን በባለቤትነት ለማስመዝገብ የሚደረገው እሽቅድድም የሚጠቀስ ሲሆን ከዚህ በፊትም ማሽላን ኢትዮጵያ ማስመዝገብ ባለመቻሏ በአንድ የካናዳ ኩባንያ መነጠቋ የሚታወስ ነው።

ዓለም አቀፍ የኦንላይን መገበያያ በሆነው አማዞን ላይ የአሜሪካ ገበሬዎች ከጤፍ የተለያዩ ምርቶችን፤ ለምሳሌ የጤፍ ፓስታና ከግሉተን ነፃ የሆነ ዳቦ በማምረት ይሸጣሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በጤፍ ላይ የተደረጉ የምርምር ውጤቶች እንደሚያሳዩት በንጥረ ነገሩ የተሻለ ይዘት ያለውና 'ቀጣዩ ልዕለ ምግብ' (ዘ ኔክስት ሱፐር ፉድ) እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሚካኤል ይህም ምርት ከዚህም አንፃር ኢትዮጵያዊያን ተጠቃሚ ለማድረግ አልሞ ተነስቷል ይላሉ።

ፍርድ ቤት የቀረበው የጤፍ ባለቤትነት ጉዳይ

"እኛም የሃገራችን ምርት ላይ ቀድመን አንድ ነገር አናደርግም፤ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ የእኛ ነበር ማለት እንጂ፤ እኛ ምንም ነገር አድርገን አናልፍም የሚለው ነገር ነው ለዚህ ያነሳሳን" ይላሉ።

ንጉሥ ቢራ ከጤፍ ቢራን ለማምረት ሃሳቡን ከጠነሰሰ ስምንት ዓመታትን ያህል ያስቆጠረ ሲሆን፤ ከሦስት ዓመት ወዲህ ፈቃዱን አውጥቶ ወደ ሥራ ገብቷል።

ኩባንያው እስካሁን ድረስ የሚታወቅበት ፕሪምየም ክራፍት ላገር ሲሆን በዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ ግዛቶች (ዲኤምቪ) ግዛቶች በተጨማሪ በኒውዮርክ ፈቃዳቸውን የጨረሱ ሲሆን በቦስተን፣ ሚኒሶታና ጆርጂያም እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው።

ለዘመናት ቢራ የሚመረተው ከገብስ ብቻ የነበረ ሲሆን ጊዜያት በኋላ የፍራፍሬ ጣዕም ያላቸው ቢራዎች በመምጣታቸውና የቤልጂየም ቢራዎች ወደ ገበያው ሰብረው መግባታቸው መነሻ እንደሆናቸውም ይጠቅሳሉ።

በተለይም የቤልጂየም ምርት የሆነውና ስንዴን ጨምሮ፣ ከብርቱካን ልጣጭ እንዲሁም ከአጃ የሚሰራው የብሉ ሙን ቢራ መምጣት ገበያውን እንደቀየረው ይናገራሉ። ባደረጉት ጥናትም ብሉ ሙን በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተወዳጅ መሆኑ መነሻ ሆኗቸዋል።

ከዚህም በመነሳት በጤፍ ላይ ምርምር ቢያደርጉ እንዲሁም ከጤፍ ቢራ ቢሰሩ ሃገሪቷንም ሆነ ጤፍን የማሳወቅ እድል እንደሚፈጥር ተስፋ በማድረግም እንዳመረቱት ያስረዳሉ።

ነገር ግን ማምረቱ ቀላል እንዳልነበር የሚናገሩት አቶ ሚካኤል ጤፍ ባለው የተለየ ባህሪ ምክንያት ከከፍተኛ ምርምርና ሙከራ በኋላም ተሳክቷል።

"ጤፍ በባህሪው ይተኛል፤ እንዲሁም ይዘቅጣል እሱ እንዳይሆን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ንቁ በሆነ መንገድ እንዲብላላ (ፈርመንት) እንዲያደርግ ብዙ ሥራ ሰርተናል" ይላሉ።

የጤፍ ቢራ ጣም ምን አይነት ይሆን?

የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በመጠቀም እንደተፈለገው አይነት ጣዕም ማምጣት እንደሚቻል የሚናገሩት አቶ ሚካኤል ቢራ ወፈር (ጠንከር) ሲል ሰው ስለማይመርጠው አሁን ገበያ ላይ የዋለው ቢራ ቀላል እንደሆነ ገልፀዋል።

ሠላሳ ሦስት ዶላርም ለመሸጥ የታቀደው ይህ ቢራ ጤፍ ያለውን የራሱን ይዘት እንዳያጣ አድርገው፤ ከቢራም ጣዕም ራቅ እንዳይል ተደርጎ እንደተቀመመም ጨምረው አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ምርቶቹ የሚሸጡት አሜሪካ ሲሆን በያዙትም እቅድ መሰረት ከሦስት ዓመታት በኋላ ወደ ወደ ኢትዮጵያ የመላክ እንዲሁም በከፊል ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው የቢራ ፋብሪካ የመጀመርም እቅድ እንዳለም ጨምረው ገልፀዋል።

ንጉሥ ቢራ ኩባንያ የተቋቋመው በሶስት በትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቢሆንም ባለቤትነቱ አሜሪካ የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የማድረግ እቅድና ሁሉም የሚሳተፍበት የማድረግ አላማ አላቸው።

"ልዩ ነዳጅ መኖሩን አልደረስንበትም" የማዕድን፣ የፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ዲያስፖራ የሚሳተፉበት ትልቅ ፋብሪካ የማቋቋም፣ ከጀርባው መዝናኛዎችና ብሪው ፐብ (መቅመሻዎችን) የማቋቋም እቅድ ያላቸው ሲሆን ለወደፊትም ጠጅና ጠላን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነቱን በጠበቀ መልኩ ለማምጣትም አስበዋል።

"እዚህ አገር ላይ ያለን ኢትዮጵያዊኖችና ኤርትራዊያን ተባብረን መስራት ከቻልን አሁን እዚህ አገር ላይ እንዳሉት ሌይማርት፣ ኤችማርት እንዲሁም ሌሎች በቻይኖችና በኮርያዎች የተቋቋሙ አክስዮኖች አንድ ላይ በመስራታቸው ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይቻላል" ይላሉ።

ተያያዥ ርዕሶች