የጥበብ እጆች ከዞማ ቤተ መዘክር ወደ ታላቁ ቤተ መንግሥት

ኤሊያስና መስከረም Image copyright Abel Tilahun
አጭር የምስል መግለጫ ኤሊያስና መስከረም

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከገቧቸው ቃልኪዳኖች መካከል አንዱ ታላቁን ቤተ መንግሥት አድሰው ለሕዝብ ክፍት ማድረግ ነበር።

በዚህ መሠረትም በቅርቡ የተለያዩ ግንባታዎች እና እድሳት የተካሄደበትን ቤተ መንግሥት የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየት ራሳቸው መኪና እያሽከረከሩ ሲያስጎበኙ በመገናኛ ብዙሃን ታይተዋል።

እድሳቱ ተጠናቆም ከመስከረም 30/2012 ጀምሮ ለጎብኝዎች ክፍት እንደሚደረግ ተገልጿል።

ባሕልና ተፈጥሮን ያጣመረው ዞማ ቤተ መዘክር

አደጋ የተጋረጠበት የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት

በቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የእድሳት እና የአረንጓዴ መናፈሻውን ሥራ ከሚሠሩት ባለሙያዎች መካከል አንትሮፖሎጂስቷ መስከረም አሰግድና የሥነ ጥበብ ባለሙያው ኤሊያስ ስሜ የሚመራው ቡድን ይጠቀሳል።

የዞማ ቤተ መዘክርን ሃሳብ የጠነሰሱት መስከረም አሰግድ፤ ከሥራ ባልደረባቸው ኤሊያስ ስሜ ጋር በመሆን በርካቶችን ያስደመመውን የቅርጻ ቅርጽና የዞማ አፀድ ሠርተው ለሕዝብ ክፍት አድርገዋል።

አሁንም እሱን የማጠናከር አላማ እንዳላቸው እና ቤተ መዘክሩ "በቅቶታል" የሚባል ደረጃ እንዳልደረሰ ይናገራሉ።

እነዚህ የጥበብ እጆች ታዲያ በዚያው ተወስነው ብቻ አልቀሩም። አሻራቸውን ለማሳረፍ በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጥሪ ወደ ቤተ መንግሥትም አቅንተዋል።

መስከረም ይህንን እድል ያገኙበትን አጋጣሚም "ጠቅላይ ሚንስትሩ ለጉብኝት ወደ ዞማ ቤተ መዘክር ጎራ ባሉበት ጊዜ በሥራችን በመደመማቸው የአዲስ አበባ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤትን ገጽታ እንድንለውጥላቸው ጥያቄ አቅርበውልን ሊያሳዩን ይዘውን ሄዱ።" ሲሉ ያስታውሳሉ።

ከጉብኝታቸው በኋላ ሥራቸውን የጀመሩት ወዲያውኑ ነበር። እሱን በመሥራት ላይ ሳሉም ወደ ቤተ መንግሥቱ ሥራ እንዲሻገሩ በድጋሚ በጠቅላይ ሚንስትሩ ጥያቄ ቀረበላቸው።

የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ እንዳልተጠናቀቀ የሚናገሩት መስከረም "እሱን ካሳመርን በኋላ በቀጥታ ቤተ መንግሥቱን እንድናስውብ ጠየቁን፤ እኛ በማግስቱ ወደ ሥራው ገባን" በማለት ይናገራሉ።

ቤተ መንግሥቱ ካረፈበት 40 ሺህ ካሬ ሜትር፤ 15 ሺህ ካሬ ሜትር የሚሆነው የግቢውን አካል እነ መስከረም እየተጠበቡበት ይገኛሉ።

በእርግጥ መስከረም ለቤተ መንግሥቱ እንግዳ አይደሉም። በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ጊዜ በአውሮፓ ኅብረት አማካኝነት ከሌሎች አምባሳደሮች ጋር ለእራት ግብዣ ወደ ቤተ መንግሥት አቅንተው ነበር።

ይሁን እንጅ የሄዱት በምሽት ስለነበር ግቢው ምን እንደሚመስል የማየት እድል አላገኙም።

"ቀጥታ ወደ እራት ግብዣው ከዚያም ወደ መኪና ነበር" ይላሉ።

ይሁን እንጅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስተዳደር፤ ከሌሎች አርቲስቶች ጋር ተጋብዘው፤ ግቢውን በሙሉ ዞረው ጎብኝተዋል፤ ጠቅላይ ሚንስትሩም ከባለሙያዎቹ አስተያየት እየጠየቁ ሲወያዩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታቸው ነው።

"አንድ መንግሥት ቤተ መንግሥት የሕዝብ ነው ብሎ ለመክፈት ማሰቡ ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር፤ ለዘመናት አጥሩን ነበር እኮ የምናየው" ሲሉ በወቅቱ የተሰማቸውን ደስታ ይገልጻሉ።

በመሆኑም ወደ ሥራው በደስታ እንደገቡ ይናገራሉ።

እንዲያስውቡት የተሰጣቸው ቦታ የሌሎች ግንባታዎች ትራፊ ቁሳቁሶች የሚጣልበት፤ ምንም ያልለማ ተዳፋት መሬት በመሆኑ የመጀመሪያ ሥራቸው ፅዳት እንደነበር ይናገራሉ።

የመጀመሪያ ዲዛይናቸውን የሠሩትም በእነዚሁ ከሌሎች ግንባታዎች በተራረፉና በተጣሉ ድንጋዮች ነበር።

ይሁን እንጅ የቦታው አቀማመጥ ተዳፋት በመሆኑና ወቅቱ ክረምት ስለነበር ሥራቸውን ፈታኝ አድርጎባቸዋል።

የፈረሰው የደጃዝማች ዐምዴ አበራ ቤት ጠባቂ ምን ይላል?

ለአደጋ የተጋለጡ ሦስት የትግራይ ቅርሶች

ቦታው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ እና ለሁሉም ምቹ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

የውሃ ተፋሰሱንና መሬቱን ካስታካከሉ በኋላ ወደ ግንባታ የገቡት ባለሙያዎቹ፤ እያንዳንዱ ድንጋይ በተለያዩ አገር በቀል በሆኑ እፅዋቶች፤ አበባ፣ በቅጠላ ቅጠል እንዲሁም በተለያዩ ቅርፆች አምሳያ እየተጠረቡ እንደተሠሩ ይናገራሉ።

በባለሙያው ኤሊያስ እየተሳሉ፣ በጠራቢዎች እየተጠረቡ ከአገር በቀል እፅዋቶች በተጨማሪ የድንጋይ ቅርጾቹ ግቢውን አስውበውታል።

የድንጋዩ ንጣፍ እንዳይፈነቀልና ለዘመናት እንዲቆይ ድንጋዮቹ እየተበሱና ከሥራቸው በብረት እየተሳሰሩ የተሠሩ ናቸው።

የተለያዩ የዓለም ክፍሎችን የመጎብኘት እድል የነበራቸው መስከረም፤ "ሥራው ከዚህ የተቀዳ ነው፤ አልተቀዳም ብሎ መናገር አይቻልም" ይላሉ። ምናልባት ከአስተዳደጋቸው አሊያም ተዟዙረው ከጎበኟቸው የተከማቸ እውቀት ሊሆን ይችላል በማለት።

"ዋናው የማምንበት ጉዳይ በጥራት በኩል ድርድር እንዳማይደረግ ነው፤ ለዘመናት የቆዩ እንደ ፋሲለደስ ያሉ ሃገራዊ ቅርሶችን ጥቃት ቢደርስባቸውም እስካሁን ድረስ ሊቆዩ የቻሉት ጥራት ስላላቸው ነው" ሲሉ ምሳሌ ያጣቅሳሉ።

Image copyright ARTnews

"ለነገ ተብለው ስለተሠሩ፤ ሲፈርሱ ቢውሉ ምልክታቸውን አልተውም" ሲሉ የሚሠሩት ሥራዎች ጥራት እንዲኖራቸው ያስገነዝባሉ።

አገር በቀል እጽዋቶች ስለተተከሉ፣ አረንጓዴ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ጥበብ በእጅ በመሠራቱ፣ ባለሙያዎቹ አገር ያፈራቸውና ከየገጠሩ የመጡ በመሆናቸው ሥራውን ለየት ያደርገዋል ብለዋል- መስከረም።

"ያ እጅ የተረሳ እጅ ነው፤ ይህ ጥበብ እንዳለው ያልታወቀ ሕዝብ፤ ወደታች ሲታዩ የነበሩ ጠበብቶች ናቸው የሠሩት።" ይላሉ።

ቅማመ ቅመም፣ መድሃኒት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፤ እንደ ግራር፣ ወይራ እና የመሳሰሉት አገር በቀል ዛፎች መኖራቸውም ሌላው ልዩ የሚያደርገው ጉዳይ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በየቀኑ እንደሚጎበኟቸው የሚናገሩት መስከረም "ፍቅር፣ ድጋፍ ይሰጡናል፤ ባላቸው ደቂቃ ተሻምተው ብቅ ብለው ያዩናል፤ ሞራል ይሰጡናል። 'እጃችሁ ይባርክ!' እያሉ ነው የሚሄዱት፤ እኔ ስለ ፖለቲካ የማውቀው ነገር የለም፤ ግን እንደዚህ ዓይነት መሪ አለ እንዴ?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

በመሆኑም ቤተ መንግሥቱ ውስጥ የሚሠሩት ሥራ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን እንደሚተጉ ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ስለ ክፍያ አስበውም፤ ተጨንቀውም አያውቁም "ጥሪ ሲቀርብልን እኔና ኤሊያስ ባንክ ያለንን ገንዘብ አይተን ብቻ ነው የገባነው" ይላሉ።

"ስለ ገንዘቡ ጨርሶውኑ ማሰብ አልፈልግም፤ ሥራውን በጥራት ሠርተን ማስረከብ ብቻ ነው" ብለዋል።

በሥራቸው ከ200- 250 የሚደርሱ ባለሙያዎች እንደተሳተፉ የሚገልፁት መስከረም "ከመንግሥት ክፍያ የሚፈጸመው ለእነርሱ ደመወዝ እንጂ፤ እኛ ሙያችንን በነፃ ነው የሰጠናቸው" ሲሉ ለሙያቸው የሚከፈላቸው ክፍያ እንደሌለ ነግረውናል።

ሥራውን በራሱ እንደ ስጦታ ነው የሚመለከቱት። እስካሁን ሲሶ (1/3ኛው) የሆነው ክፍል እንደተጠናቀቀ እና ለመስከረም መጨረሻ ለጉብኝት ክፍት እንደሚሆን ገልጸዋል።

የእጅ ሥራ በመሆኑና የጥበበኞች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ የማጠናቀቂያ ጊዜውን እንዲህ ነው ብሎ ማስቀመጥ እንደሚያስቸግር ነግረውናል። በጀቱም ቢሆን ሥራው ተጠናቆ ከስሌት በኋላ ካልሆነ በቀር አሁን እንዲህ ነው ማለት ተራ ግምት እንደሚሆን በመግለጽ ከመናገር ተቆጥበዋል።

ባለሙያዎቹ መስከረምና ኤሊያስ ለሠሩት ሥራ በተለያየ ጊዜ ሽልማት አግኝተዋል።

በዞማ ቤተ መዘክር የተባበሩት መንግሥታት ሽልማት አበርክቶላቸዋል። ሌሎችም የሚጠበቁ ሽልማቶች እንዳሉ ገልፀውልናል።

ኤሊያስ ስሜ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ የአፍሪካ አርት አዋርድ ከሁለት አሸናፊዎች አንዱ በመሆን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የስሚዝሶኒያን የአፍሪካ አርት ብሔራዊ ሙዚየም ሽልማት እንደሚበረከትለትም ይጠበቃል።

ቤተመንግሥቱ ለጎብኚዎች ክፍት ሲሆን እያንዳንዱ ሰው 200 ብር እየከፈለ መጎብኘት እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን፣ ሳይጋፉ እንደመጡ መግባት የሚፈልጉ ደግሞ 1,000 ብር እየከፈሉ መጎብኘት እንደሚችሉ ተዘግቧል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ