ሲራክ አስፋው፡ ለ21 ዓመታት በባዕድ አገር የኢትዮጵያን ቅርስ ደብቀው ያቆዩት ኢትዮጵያዊ

አቶ ሲራክ አስፋው
የምስሉ መግለጫ,

አቶ ሲራክ አስፋው

አቶ ሲራክ አስፋው ላለፉት 41 ዓመታት ኔዘርላንድስ ውስጥ ከመኖራቸው በላይ የአገሪቱ ዜጋ ናቸው። ነገር ግን አሁንም ድረስ ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና ታማኝነት ባለበት እንዳለ ይናገራሉ።

አቶ ሲራክ በደርግ ዘመን የነበረውን ቀይ ሽብር ሸሽተው ስለተሰደዱ፤ ሰዎች በስደት ወቅት የሚገጥማቸውን ችግርና ፈተና በደንብ ይረዳሉ። ስለዚህም የአገራቸው ዜጋም ሆነ ሌላ ስደተኛ ተቸግሮ ሲገጥማቸው ባላቸው አቅም ከመርዳት ወደኋላ እንደማይሉ ይናገራሉ።

በዚህ ሂደት በርካታ ሰዎች ወደ ቤታቸው ሄደው ይጠለሉ እንዲሁም ያሏቸውን እቃዎች ያስቀምጡ እንደነበር ያስታውሳሉ። አንዳንዶች የጥገኝነት ጥያቄና ሌላም ጉዳያቸው ተጠናቆ ወደ ሌላ ቦታ እስኪሄዱ ድረስ የግል ሰነዶቻቸውን ጨምሮ ሌሎችም እቃዎች አቶ ሲራክ ቤት በአደራ ያስቀምጣሉ።

ከአራት መቶ ዓመታት በላይ እድሜ ያለው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርስ ወደ ቤታቸው እንዲሄድ ያደረገውም መሰል አጋጣሚ ነው። ቤታቸው ይመላለሱ ከነበሩ ሰዎች አንዱ፤ ቅርሱን እርሳቸው ቤት ትተውት እንደሄዱ ይናገራሉ።

ቅርሱ ወደ አገር ቤት እሰኪመለስ ድረስ ዝርዝር ሁኔታውን ለመግለጽ ያለፈለጉት አቶ ሲራክ ቅርሱ፤ "ጥንታዊ የአገር ሀብት" መሆኑን በአጽንት ያስረዳሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ በ1626 ዓ. ም. በአጼ ፋሲለደስ እንደተሠራ የሚነገርለት ዘውድ፤ አቶ ሲራክ እጅ የገባው ከ21 ዓመታት በፊት ነበር። ዘውዱን ካገኙ በኋላ ወደመጣበት የመመለስ ፍላጎት ቢኖራቸውም በወቅቱ በነበሩት የአገሪቱ ባለስልጣናት ላይ "እምነት ስላልነበረኝም ከእጄ እንዲወጣ አልፈኩም ነበር" ይላሉ።

"ከቅርሱ ከአገር መውጣት ጋር በተያያዘ በዚያን ጊዜ ከነበሩት ባለስልጣናት መካከል አንዳንዶቹ እጃቸው እንደነበረበት አምን ነበር" የሚሉት አቶ ሲራክ፤ በወቅቱ ቢመልሱት ኖሮ "እንደፈለጋችሁ አድርጉት ብሎ በመተው ቅርሱ ተመልሶ ከአገር እንዲወጣ ዕድል መፍጠር ነው" ብለው በማሰብ ለማንም ሳይነግሩ እጃቸው ላይ ለማቆየት ወሰኑ።

የቅርሱ ደህንት ያሳስባቸው ስለነበር፤ በወቅቱ አዲስ የመገናኛ ዘዴ የነበረውን ኢንተርኔት በመጠቀም፤ ከሰዎች ጋር በመወያየት ሃሳብ እንዲሰጧቸው ቢጠይቁም፤ የጠበቁትን ያህል ምላሽ ስላላገኙ፤ አመቺ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ቅርሱን ለመጠበቅ የደረሱበትን ውሳኔ አጠናከሩት።

የዚህ ጥንታዊ ዘውድ ጠባቂ በመሆን ከሁለት አሠርታት በላይ ያቆዩት ሲሆን፤ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ውሳኔ ላይ የደረሱትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ስልጣን በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ይናገራሉ።

ስጋት

አቶ ሲራክ ድንገት እጃቸው ላይ የወደቀው ቅርስ ወደ አገር ቤት እስኪመለስ ድረስ አንዳች ጉዳት እንዳይደርስበት ዘወትር ይሰጉ፣ ይጨነቁም ነበር።

አንድ ነገር ቢገጥመኝና ሌላ ሰው እጅ ቢገባ ምን ይሆናል? የሚለው የዘወትር ፍርሃታቸው "ሰውነትን ይጎዳል" የሚሉት አቶ ሲራክ፤ ማንንም ማመን ስላልቻሉ ቅርሱ መኖሩንና የት እንዳለ የሚያውቁት እርሳቸው ብቻ ነበሩ።

ስለጉዳዩ ማንም ስለማያውቅ ያሳስባቸው የነበረው "ድንገት እሳት ቢነሳስ" የሚለው ስለነበረ፤ ቤታቸው ውስጥ በርከት ያለ የእሳት ማጥፊያና የእሳት መከሰትን የሚጠቁም መሣሪያን አዘጋጅተው ዘወትር ቅርሱን ይጠብቁ እንደነበር ይናገራሉ።

"እኔ ይህንን ቅርስ ከሌላ ሰው አግኝቼ ወደ መጣበት ከመመለሴ በፊት አንድ ጉዳት ቢደርስበትና ቢጠፋ ምን ብዬ ነው የምናገረው የሚለው ሃሳብ ዘወትር ያሳስበኝ ነበር" ይላሉ።

ኑዛዜ

አቶ ሲራክ አስፋው ለቅርሱ ደህንነት ሲሉ ምንም ነገር ትንፍሽ ሳይሉ ለ21 ዓመታት ሲቆዩ፤ "ለቅርሱ ደህንነት እምነት የምጥልበት ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ በአጭር ጊዜ ይመጣል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር" ይላሉ።

ቅርሱን ለባለቤቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማስረከባቸው በፊት፤ "ሰው ነኝና ከዚህ ዓለም በአንዳች አጋጣሚ ባልፍ፤ ያለበት ሳይታወቅ ቀርቶ እንደወጣ እንዳይቀር አንድ ውሳኔ ላይ ደረስኩ" በማለት ኑዛዜ ማስቀመጣቸውን ይናገራሉ።

በኑዛዜያቸው ይህ ቅርስ የት እንደሚገኝ፣ ለማን መሰጠት እንዳለበትና መደረግ ስላለበት ነገር በዝርዝር አስፍረው ቅርሱ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን ንብረት መሆኑን አመልክተው ነበር።

ዘውድ

የኢትዮጵያ ነገሥታት ዘውዶቻቸውን ለተለያዩ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት በስጦታ ያበረክቱ እንደነበር የሚጠቅሱት አቶ ሲራክ፤ በእጃቸው ያለው ዘውድም ለቤተክርስቲያን የተሰጠ እንደሆነ ያምናሉ።

ዘውዱን በተመለከተ እዚያው ኔዘርላንድስ ውስጥ የሚገኙ ሁለት የሙዚየም ዳይሬክተሮችን ለማማከር እንደሞከሩ የሚያስታውሱት አቶ ሲራክ፤ ወስደው እንዲያሳዩዋቸው እንደጠየቋቸውና ፈቃደኛ ሳይሆኑ እንደቀሩ ይናገራሉ።

ባለሙያዎቹም ቅርሱ ከተወሰነ ዓመታት በኋላ በእጃቸው ከቆየ ባለቤትነቱ የእርሳቸው እንደሚሆን ነግረዋቸው ነበር። እሳቸው ግን "የእኔ ፍላጎት የአገሬን ንብረት የራሴ ማድረግ ሳይሆን ወደመጣበት እንዲመለስ ማድረግ ነው" ብለው ከባለሙያዎቹ ጋር መለያየታቸውን ይናገራሉ።

በመጨረሻም ከአንድ ዓመት በፊት ቅርሱ ወደ አገር ቤት ሊመለስ ይችላል የሚል ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን የሚናገሩት አቶ ሲራክ፤ ወዲያውኑ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት ጋር በመነጋገር ሂደቱን መጀመራቸውን ያስረዳሉ።

አሁንም የቅርሱ ደህንነት እንዲጠበቅ የኔዘርላንድስ ቅርሶች በሚጠበቁበት ተቋም ውስጥ መቀመጡንና "ከእኔ በስተቀር የተቀመጠበትን ካዝና ማንም መክፈት ስለማይችል ምንም የሚያሳስበኝ ነገር የለም" ብለዋል።

የአገራቸው ቅርስ በባዕድ እጅ እንዳይወድቅ ሲጠብቁ ምን ይከሰት ይሆን? በሚል ስጋት ውስጥ ሁለት አሠርት ዓመታትን ያሳለፉት አቶ ሲራክ፤ አሁን ሸክማቸው እንደቀለለ ይናገራሉ።

"እፎይ ብዬ ያለ ሃሳብና ያለ ስጋት ሰላማዊ እንቅልፍን የማገኘው ደግሞ ታሪካዊው ዘውድ የኢትዮጵያን መሬት ሲረግጥ ነው" በማለት 400 ዓመታት ያስቆጠረው፣ በድንገት እጃቸው የገባውንና በአደራ እንዳገኙት የሚያምኑት ቅርስ ኢትዮጵያ የሚገባበትን ዕለት በጉጉት እየጠበቁ እንደሆነ ይገልጻሉ።