"ተጨማሪ የፌደራል የሥራ ቋንቋዎች እንዲኖሩ እየተሠራ ነው" ጠ/ሚኒስትር ዐብይ

ዐብይ አህመድ Image copyright Getty Images

ኦሮምኛን ጨምሮ ተጨማሪ ቋንቋዎችን የፌደራል የሥራ ቋንቋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን (ኦቢኤን) ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት ኦሮምኛን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ ሌላ ቋንቋ የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ማድረግ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች ካሉና ያላቸውን አመለካከት የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በሰጡት መልስ "በዚህ ረገድ ምንም ችግር የለውም" ሲሉ በአፅንኦት መልሰዋል።

አሥመራን አየናት፡ እንደነበረች ያለችው አሥመራ

አዲስ ቋንቋ ለመማር አስበዋል? ለመሆኑ እድሜዎ ስንት ነው?

አክለውም "ሁለት፤ ሦስት ቋንቋዎች መጠቀም ሰውን ይጠቅማል እንጂ ምንም ዓይነት ጉዳት የለውም" ሲሉ አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ ተጨማሪ የፌደራል የሥራ ቋንቋዎች ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን ተናግረው፤ ለዚህም ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ ይህ ሊሆን የሚችለው በስሜትና በኩርፊያ ሳይሆን በእውቀትና በተረጋጋ አኳዃን ነው ብለዋል።

ኦሮምኛ የፌዴራል ስራ ቋንቋ የመሆን ጥያቄ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ቀጣዩ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንደሚሆን ተናገሩ

ስለሆነም በቅርብ ጊዜ ሌሎች ቋንቋዎችን የፌደራል የሥራ ቋንቋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንና ጥናቱም ሲጠናቀቅ "ከኦሮምኛ በተጨማሪ ሶማልኛ እና ሌሎች ቋንቋዎች የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ቢሆኑ የምንጎዳው ነገር የለም" ሲሉ ተናግረዋል።

ተጨማሪ ቋንቋዎችን የሚጠቀሙ ሀገራትን እንደ ምሳሌ በማንሳት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ከዚህ ኤርትራ ቢኬድ፣ ኬኒያ ቢኬድ፣ ጅቡቲ ቢኬድ እንዲህ አይነት ነገር የተለመደ ነው" በማለት ችግር እንደማይኖረው አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ስለ መደመር፣ ስለ እሬቻ፣ ሪፎርምና እና ስለ ቤተ መንግሥት እድሳት ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች