አሜሪካ የአባይ ወንዝ አጠቃቀምን በተመለከተ መግለጫ አወጣች

ኋይት ሐውስ Image copyright Raymond Boyd

በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ የመሙላት ሂደትንና አጠቃቀም ላይ ትብብር፣ ዘላቂነትና የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥን በተመለከተ እየተደረገ ያለውን ድርድር እንደምትደግፈው አሜሪካ አስታወቀች።

ይህ የተገለጸው ከኋይት የፕሬስ ጽህፈት ቤት ሐውስ በወጣና ዝርዝር ጉዳዮችን በማይጠቅሰው አጭር መግለጫ ላይ ሲሆን፤ መግለጫው የወጣበት ምክንያትም አልተገለጸም።

በዚህ አጭር መግለጫ ላይ "ሁሉም የአባይ ተፋሰስ አገራት በምጣኔ ሃብት የመልማትና የመበልጸግ መብት አላቸው" ይልና ሲቀጥል "አስተዳደሩ [የአሜሪካ] ሁሉም አገራት እነዚህን መብቶች ሊያስከብር የሚችልና የእያንዳንዳቸውን የውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያስከብር በጎ ፈቃደኝነትን የተላበሰ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ ያቀርባል" ይላል።

በአባይ ግድብ ላይ ለዓመታት የተካሄድው ውይይት ውጤት አላመጣም፡ ግብጽ

''የሚፈርስ የግድቡ አካል የለም'' የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ

የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ክፍል ይህንን መግለጫ ከምን ተነስቶ እንዳወጣ የገለጸው ነገር የሌለ ሲሆን ተጨማሪ የሰጠው ማብራሪያም የለም።

ይህ መግለጫ ምናልባትም ዛሬና ነገ ካርቱም ውስጥ የሦስቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ያደርጉታል ተብሎ ከሚጠበቀው ቀጣይ የሦስትዮሽ ውይይት ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ይገመታል።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ኒውዮርክ ላይ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችውን ግድብን በተመለከተ የሚደረገው ድርድር ውጤት ላይ አለመድረሱ በአካባቢው ላይ አለመረጋጋትን ሊያስከትል እንደሚችል መናገራቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያዋ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚያው መድረክ ላይ ለግብጹ ፕሬዝዳንት ንግግር ምላሽ በሚመስል ሁኔታ "የአባይ ወንዝ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት እንጂ የጥርጣሬና የውድድር ምንጭ ሊሆን አይገባም" በማለት ሃገራቱ የወንዙን ውሃ በጋራ መጠቀም እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንቷ አክለውም የተፋሰሱ ሃገራት "የአባይን ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለመጠቀምም በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ" በንግግራቸው ላይ አንስተዋል።

ባለፈው መስከረም 3 እና 4/2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን ባለስልጣናት ካይሮ ላይ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ በተከታታይ እያደረጉት ያለው የሦስትዮሽ ውይይት መካከል አንዱ የሆነው ካይሮ ላይ የተካሄደ ቢሆንም ያለስምምነት መጠናቀቁ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከካይሮው ድርድር በኋላ አዲስ አበባ ላይ በሰጡት መግለጫ ግብጽ በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ አዲስ ሃሳብ እንዳቀረበችና ኢትዮጵያ ሃሳቡን ውድቅ እንዳደረገች ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ግብጽ ያቀረበችው ሃሰብ፤ የግድቡ የውሃ የሚሞላው በሰባት ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊየን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንድትለቅና የአስዋን ግድብ የውሃ መጠኑ ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ ግድቡ በዋናነት ውሃ እንዲለቅ የሚጠይቅ ነው።

ኢትዮጵያም ይህ የግብጽ ሃሳብ ቀደም ሲል በሦስቱ ዋነኛ የተፋሰሱ አገራት መካከል የተፈረመውን የአባይ ወንዝ ውሃን አጠቃቀም የተመለከተውን "የመርህ ስምምነት የጣሰና ጎጂ ግዴታን የሚያስቀምጥ ነው" በማለት እንደማትቀበለው አሳውቃለች።

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ መዘግየት ምን አይነት መፍትሔዎች እየተሰጡ ነው?

ሚኒስትሩ በተጨማሪም ይህ የቀረበው ሃሳብ "ግብጽ የወንዙ ዓመታዊ የውሃ ፍሰት 40 ቢልየን ሜትር ኪዩብ እንዲሆን ያቀረበችው ጥያቄ፤ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን እንዳትጠቀም የሚከለክል በመሆኑ አልተቀበለችውም" ብለዋል።

በግድቡ የውሃ አሞላልና የመልቀቅ ሂደት ዙሪያ ያሉትን ሁኔታዎች እንዲያጠና የተቋቋመው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሦስትዮሽ ብሔራዊ ገለልተኛ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድን 5ኛ ስብስባውን ካርቱም ሱዳን ውስጥ ሰኞ እለት አካሂዶ የነበረ ሲሆን፤ ቡድኑ ዛሬ መስከረም 23 እና 24/2012 ዓ.ም እዚያው ካርቱም በሚካሄደው የሦስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።