ኢትዮጵያ በአለም ሻምፒዮና የወንዶች የማራቶን ውድድር ከ18 ዓመታት በኋላ ወርቅ አገኘች

ሌሊሳ Image copyright Sam Barnes

ኢትዮጵያ በአለም ሻምፒዮና የወንዶች የማራቶን ውድድር ከአስራ ስምንት ዓመታት በኋላ በሌሊሳ ዴሲሳ አማካኝነት ወርቋን አግኝታለች።

በካታር ዶሃ እየተካሄደ ባለው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና ቅዳሜ እኩለ ሌሊት በተካሄደው የማራቶን ውድድር ሌሊሳ ዴሲሳ አንደኛ፤ ሞስነት ገረመው ደግሞ ሁለተኛ ሆነው ለኢትዮጵያ ወርቅና ብር አስገኝተዋል።

ኢትዮጵያ በጎርጎሳውያኑ 2001 ካናዳ ኤድመንተን በተካሄደው የማራቶን ውድድር በገዛኸኝ አበራ ወርቅ ማግኘቷ ይታወሳል።

ሌሊሳ 2፡10፡40 በሆነ ሰዓት ውድድሩን ያጠናቀቀ ሲሆን የራሱን የዓመቱን ምርጥ ውጤት አስመዝግቧል።

በአከራካሪው የ3ሺህ ሜትር መሰናክል ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ አገኘች

በዶሃ የሴቶች ማራቶን ሦስት ኢትዮጵያውያን ሯጮች አቋርጠው ወጡ

በዚህ ውድድር ለመሳተፍ ከፍተኛ ዝግጅት እንዳደረገ የሚናገረው ሌሊሳ "ለአራት ወራት ያህል ራሴን ለውድድሩ ሳዘጋጅ ነበር፤ በተለይም አዳማን በመሳሰሉ ሞቃት ቦታዎች ልምምድ አድርጌያለሁ" በማለት ስለ ድሉም "ድሉ የኔ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ ነው"ብሏል።

ሁለተኛ የወጣው ሞስነት ገረመው በአራት ሰከንዶች ተቀድሞ ነው ሁለተኛ የወጣው።

ከውድድሩም በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው ቃል " ወርቅ አገኛለሁ ብዬ ነበር፤ ነገር ግን ከግማሽ ውድድር በኋላ ጎኔ ላይ ህመም እየተሰማኝ የነበረ ቢሆንም ሌሊሳን ብቻውን ላለመተው ስል ነው ውድድሩን ያጠናቀቅኩት" ብሏል።

Image copyright Maja Hitij
አጭር የምስል መግለጫ ኬንያዊው አሞስ ኪፕሩቶና ኢትዮጵያውያኖቹ ሌሊሳ ዴሲሳና ሞስነት ገረመው

በውድድሩ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ በከፍተኛ ሁኔታ በስሜት ተሰቅዛ የቢቢሲ ዘጋቢ የተመለከተ ሲሆን ኢትዮጵያዊያኖቹ በውድድሩ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ደስታዋን በከፍተኛ ሁኔታ ገልፃለች።

በሦስተኛነትም ኬንያዊው አሞስ ኪፕሩቶ የነሐስ ሜዳልያ አግኝቷል።

ከኢትዮጵያዊያኖቹ በተጨማሪ ይህንን ውድድር በመፈራረቅ ሲመሩ የነበሩት ኤርትራዊው ዘረ ሰናይ ታደሰን ጨምሮ ደቡብ አፍሪካዊ፣ ኬንያዊና እንግሊዛዊ ተወዳዳሪዎች ሲሆኑ አንዳቸው ወርቅ ሊያገኙ እንደሚችሉም ተጠብቆ ነበር። ዘረሰናይ ታደሰ ውድድሩን ስድስተኛ ሆኖ አጠናቋል።

''በኳታር የኢትዮጵያ ቡድን በሙቀቱ ተቸግሯል'' የቡድኑ መሪ

ሰባ ሦስት ሯጮች በተሳተፉበት በዚህ ውድድር አስራ ስምንቶቹ አቋርጠው የወጡ ሲሆን ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያዊው ሙሌ ዋሲሁን ይገኝበታል።

ምንም እንኳን ኳታር ውስጥ ያለው ሙቀት ከፍተኛ ቢሆንም የሙቀት መጠኑ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ውድድሮች የተሻለ መሆኑን በዶሃ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ታዝቧል።

ከእኩለ ሌሊት በኋላ በተደረገው በዚህ ውድድር 29 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድና 48 በመቶ ወበቅ (ሂሚዩዲቲ) የነበረ ሲሆን የሴቶች ማራቶን ውድድር በተካሄደበት ወቅት 33 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀትና 80 በመቶ ወበቅ (ሂሚዩዲቲ) ነበር።

በዚህ የዶሃ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር የመጀመሪያ ቀናት ላይ በተካሄደው የሴቶች የማራቶን ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኢትዮጵያ ሴት ሯጮች በአስቸጋሪው የአየር ሁኔታ ምክንያት ውድድሩን ለማቋረጥ መገደዳችው የሚታወስ ነው።

ሌሊሳ ከአንድ ሳምንት በኋላ ኒውዮርክ በሚደረገው የማራቶን ውድድር እንደሚሳተፍ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት ውድድር ማካሄድ ትችላለህ ወይ ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ "ማገገም ከቻልኩ፤ አዎ እሳተፋለሁ" ብሏል።

በዶሃ እየተደረገ ባለው የአትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያ ባገኘቻቸው የሜዳልያ ብዛቶች አሜሪካ፣ ኬንያ፣ ጃማይካና ቻይናን ተከትላም አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። እስካሁን ባሉ ውድድሮችም ሁለት ወርቅ፣ አራት ብርና አንድ ነሃስ በማግኘት በአጠቃላይ ሰባት ሜዳልያዎችን ማግኘት ችላለች።

ተያያዥ ርዕሶች