ግሬግ ስኩፍ ፡ ሕገ ወጥ ስብሰባ አካሂደዋል የተባሉት አሜሪካዊ ፓስተር ከሩዋንዳ ተባረሩ

ግሬግ ስኩፍ በኪጋሊ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ
አጭር የምስል መግለጫ ግሬግ ስኩፍ [በቀኝ በኩል] የታሰሩት በኪጋሊ ከጋዜጠኞች ጋር እያወሩ በነበረበት ወቅት ነው

ሰኞ ዕለት ከጋዜጠኞች ጋር 'ሕገ-ወጥ' ስብሰባ በማድረጋቸው በኪጋሊ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት አወዛጋቢው አሜሪካዊው ፓስተር ከሩዋንዳ ተባረሩ።

ወንጌላዊ ግሬግ ስኩፍ ትናንት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከጋዜጠኞች ጋር ሕገ ወጥ ስብሰባ በማካሄዳቸው እንደሆነ ፖሊስ አስታውቆ ነበር።

ፓስተሩ የራዲዮ ጣቢያቸውና ቤተክርስትያናቸው በመዘጋቱ የሩዋንዳን መንግሥትን ተችተዋል።

ሩዋንዳ 700 አብያተ ክርስትያናትን ዘጋች

የአእምሮ ጤና ሰባኪው ፓስተር ራሱን አጠፋ

'ዘ አሜዚንግ ግሬስ' የተባለው የራዲዮ ጣቢያቸው ሴቶችን እንደ 'ሰይጣን' አድርጎ የሳለ ሰባኪን ማቅረቡን ተከትሎ ከሥርጭት የታገደው ባሳለፍነው ዓመት ነበር።

በአገሪቷ ካሉ እና በድምፅ ብክለት፣ እንዲሁም ሕግ ባለማክበራቸው ከተዘጉ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ቤተ ክርስትያናት መካከል የእርሳቸውም አንዱ ነበር።

ግንቦት ወር ላይ የራዲዮ ጣቢያቸውን ለማስከፈት የአገሪቷ መንግሥት ሚዲያዎች ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በመቃወም ያቀረቡት ክስ ውድቅ ተደርጎባቸዋል።

"ግሬግን በቁጥጥር ሥር አውለን፤ ለሩዋንዳ የምርመራ ቢሮ አሳልፈን ሰጥተናቸዋል" ሲሉ የፖሊስ ቃል አቀባዩ ጆን ቦስኮ ካቤራ፣ ለኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ተናግረው ነበር።

የሃገሪቱ የኢሚግሬሽን መምሪያ ዳይሬክተር፤ ወንጌላዊው በሩዋንዳ ለመስራት የሚያስችላቸው የሥራ ፍቃድ ጊዜው ካለፈ ወራት መቆጠሩን ጠቅሶ፤ ግለሰቡ የመኖሪያ ፍቃድ ስለሌላቸው ከሩዋንዳ እንዲባረሩ ተደርገዋል ብሏል።

ቃል አቀባዩ አክለውም "ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በሕዝብ መገልገያ ቦታ ከጋዜጠኞች ጋር ሕገ ወጥ ስብሰባ በማካሄዳቸው ነው፤ በአገሪቷ ሕግ በሕዝብ መገልገያ ቦታ ያለ ፍቃድ ስብሰባ ማካሄድ የተከለከለ ነው" ሲሉ የታሰሩበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

ግሬግ ሰኞ ዕለት ከመታሰራቸው በፊት ለሚዲያ በሰጡት የፅሁፍ መግለጫ ላይ የሩዋንዳ መንግሥት በሚፈፅማቸው የአህዛብ ድርጊቶች 'ከፈጣሪ ጋር በተቃርኖ ቆሟል' ብለዋል።

"የክርስቲያን ራዲዮ ጣቢያዎች በሕገ ወጥ መንገድ እየተዘጉ ነው፤ 7 ሺህ ቤተክርስትያናት በሕገ ወጥ መንገድ ተዘግተዋል፤ ኮንዶም በትምህርት ቤት ውስጥ ለህፃናት ይተዋወቃል፤ ርኩሰትን ያበረታታል" ይላል መግለጫው።

ቀብር አስፈጻሚዎች ከሞት አስነሳሁ ያለውን ፓስተር ሊከሱ ነው

አክለውም በትምህርት ቤት ውስጥ ስለ ሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ አመጣጥ የሚሰጠውን ትምህርት፤ የፅንስ ማቋረጥ ሕግን ማቅለል በተመለከተም የሩዋንዳን መንግሥት ይተቻሉ። "መንግሥት ሕዝቡን ገሃነም ሊያስገባው ነው እንዴ?" ሲሉም ይጠይቃሉ።

ፓስተር ግሬግ ከዚህ ቀደምም በሩዋንዳ ያለውን ሃሳብን በነፃነት መግለፅን በተመለከተ አበክረው ይጠይቁ ነበር።

ባለፈው ዓመት በራዲዮ ጣቢያቸው በተላለፈው ዝግጅት ላይ አንድ የአገሪቷ ፓስተር "ሴቶች የሰይጣን አደገኛ ፍጥረቶች ናቸው፤ ሁል ጊዜም ከፈጣሪ እቅድ በተቃርኖ ይሄዳሉ" ማለታቸውን ተከትሎ "በአገሪቷ ውስጥ መከፋፋልን ይሰብካል" በሚል በመንግሥት ተከሰው ነበር።

ፓስተር ግሬግ እና ቤተሰቦቻቸው ከጎርጎሮሳዊያኑ 2003 አንስቶ ኑሯቸውን በሩዋንዳ ማድረጋቸውን ድረ ገፃቸው ላይ የሰፈረው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ