ጂም ኢስቲል፡ 300 የሶሪያ ስደተኞችን የታደገው ካናዳዊ ባለሃብት

ጂም ኢስቲል Image copyright Jim Estill
አጭር የምስል መግለጫ ጂም ኢስቲል ከ300 በላይ ሶሪያዊያን ስደተኞች በካናዳ አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩ ረድተዋቸዋል።

ካናዳዊው ባለሃብትና በጎ አድራጊ ከ300 በላይ የሶሪያ ስደተኞችን ሕይወት መለወጥ ችለዋል።

በሥራቸው ውጤታማ የሆኑት ካናዳዊው የንግድ ሰው በሶሪያ የሚካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት በቴሌቪዥን ሲመለከቱ እነርሱን ለመርዳት አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው መወሰናቸውን ይናገራሉ።

በመሆኑም የሶሪያ ስደተኞች በካናዳ ውስጥ እንዲቋቋሙና ሕይወታቸውን በተስተካከለ መልኩ እንዲመሩ አስችለዋል። "ትክክለኛውን ነገር ነው ያደረኩት" ይላሉ ጂም።

ይህንን ያደረጉት በጎርጎሮሳዊያኑ 2015 ሲሆን፣ በወቅቱ ምንም እንኳን የካናዳ መንግሥት ጦርነትን ሸሽተው የተሰደዱ ሶሪያውያንን ለመቀበል የሚያስችለውን ይፋዊ አሰራር እያስተካከለ የነበረ ቢሆንም ጂም የነበረው የሂደቶች መንቀራፈፍ እጅግ ያሰጋቸው ነበር።

"በሶሪያ እየሆነ ያለውን ቀውስ አያለሁ፤ የምዕራባዊያን አገራት መንግሥታት አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣሉ የሚል እምነት አልነበረኝም" ሲሉ የ62 ዓመቱ ባለሃብት ያስታውሳሉ።

በመሆኑም ችግሩን በትንሹም ቢሆን ለመፍታት የሚችላቸውን ሁሉ ለማድረግ ወሰኑ። 1.1 ሚሊየን ዶላር ከራሳቸው ኪስ በማውጣት ከመካከለኛው ምስራቅ የሶሪያ ስደተኞችን ወደ ሚኖሩበት ካናዳ፣ ኦንታሪዎ መውሰድ ችለዋል።

ጂም ይህንን ለማድረግ 'ፕራይቬት ስፖንሰርሽፕ' [የግል ድጋፍ አድራጊ] የስደተኞች ፕሮግራም በመፈቀዱ የካናዳን መንግሥት ያመሰግናሉ። በካናዳ ይህ አሠራር የተዋወቀው ከ41 ዓመታት በፊት ሲሆን በቪየትናም ጦርነት ጊዜ የካናዳ ዜጎች፣ ስደተኞችን ለመቀበልና በአገሪቷ እንዲቋቋሙ ለመደገፍ ትፈቅድላቸው ነበር።

ድጋፍ አድራጊው ግለሰብ ለሚወስደው ስደተኛ የሚያስፈልገውን ወጭ ሁሉ ለአንድ ዓመት እንዲሸፍን ሕጉ ያስገድዳል።

ጂም ይህንን እድል በመጠቀም ለ50 ሶሪያዊያን ስደተኞች የሚጠበቀውን አሟልተው 135 ሺህ የሕዝብ ብዛት ወደ የሚኖርባት ጎልፍ ወስደዋቸዋል።

የተወሰኑትን በራሳቸው መኖሪያ ቤት ያስቀመጧቸው ሲሆን በከተማዋ ካለ የቤተ ክርስቲያን ቡድን 800 በጎ ፈቃደኞችን በማደራጀት እና በአካባቢው ካሉ የሙስሊም ማህበረሰብ ጋር በቅርበት በመሥራት ለመርዳትም ይሞክሩም ነበር።

በጦርነት የተጎሳቆሉ ስደተኞች መዳረሻቸው የት ነው?

የበጎ ሰው ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራዎችን ሊሸልም ነው

የአገሪቷ ነዋሪዎችም የማረፊያ ክፍሎችን በመስጠት፣ ክፍት የሆኑ የመኖሪያ ቤቶችን በማፈላለግ፣ አልባሳትን በመሰብሰብና ድጋፍ በማድረግ በወቅቱ የነበረውን ቅዝቃዜ በብርድ ሳይገረፉ እንዲያሳልፉ ረድተዋቸዋል።

ልጆቻቸው እንዲማሩ እና ወላጆቻቸው ሥራ እንዲሰሩ በሚል ለእያንዳንዱ ሶሪያዊያን ቤተሰቦች እንግሊዝኛና አረብኛ ቋንቋ አስተማሪ ቀጥረውላቸዋል።

ጂም ይህ ብቻ ሳይሆን 28 ለሚሆኑት ሶሪያውያን ስደተኞች ራሳቸው በሚመሩት የግል ድርጅታቸው የሙሉ ሰዓት ሥራ ሰጥተዋቸዋል።

ለሌሎቹ ሶሪያዊያን ደግሞ በከተማዋ በግላቸው የንግድ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ፤ ሱቅ እንዲከፍቱ የሚያስችላቸውን የገንዘብ ድጋፍ አድርገውላቸዋል።

በአሁኑ ሰዓት ጂም በአጠቃላይ ቁጥራቸው ከሦስት መቶ የሚበልጡ 89 ሶሪያውያን ቤተሰቦችን ይደግፋሉ። "ይህንን የማደርገው እነዚህን መልካም ሰዎች እንዲቋቋሙ ለመርዳትና በክፉ ጊዜ ከጎናቸው ለመቆም ነው" ብለዋል።

በካናዳ ገልፍ ከሚኖሩት ስደተኞች አንዱ የሆኑት አሕመድ አቤድ በጎርጎሮሳዊያኑ 2016 በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ አገራቸውን ጥለው እንደተሰደዱ ይናገራሉ። "ባለሃብቱንና የአገሪቷን 'የስፖንሰርሽፕ ፕሮግራም' አመሰግናለሁ፤ ጎልፍ አሁን አዲሱ አገሬ ሆኗል" ይላሉ ባለቤታቸው ከተማ ውስጥ ሱቅ በመክፍት መሥራት እንደጀመረች በመናገር።

Image copyright Jim Estill
አጭር የምስል መግለጫ ጂም ሶሪያዊያኑ ሥራ እንዲያገኙ ጥረት ያደረጉ ሲሆን 28ቱን በራሳቸው ድርጅት ውስጥ ቀጥረዋቸዋል

በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 1980 ከካናዳ ዋተርሉ ኦንታሪዮ ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና የመጀመሪ ዲግሪያቸውን ያገኙት ጂም፤ ሥራ የጀመሩት በኮምፒዩተር ኢንዱስትሪ ነበር።

ይሁን እንጅ ተቀጥሮ ከመስራት ይልቅ በመኪና እየተዘዋወሩ ኮምፒዩተሮችን በመሸጥ ወደ ንግዱ ዓለም ተቀላቀሉ።

የቢዝነስ ድርጅቱ ኢ ኤም ጀ ዳታ ሲስተም በጎርጎሮሳዊያኑ 2004 በአሜሪካዊያኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ቡድን 'ሰይኔክስ' በ56 ሚሊየን ዶላር ከመገዛቱ በፊት በነበሩት በ24 ዓመታት ውስጥ ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ነበር።

ከብላክቤሪ ሞባይል ጀርባ ላለው የካናዳ ድርጅት 'ሪሰርች ኢን ሞሽን' መሥራች የቦርድ አባል ሆነው እንዲሁም በሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ላይ አገልግለዋል።

በ2015 በዳንቢይ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኑ። ድርጅቱ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖችን፣ ማቀዝቀዣዎችን፣ የመመገቢያ እቃዎች ማጠቢያ ማሽን እና የአየር ሁኔታ ምቹ ማድረጊያ እቃዎችን ያመርታል።

"እንደ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሳደርግ የነበረው፤ አሰራር መዘርጋት ነበር፤ ለስደተኞችም ያደረኩት ይኼው ነው፤ እቃዎቹን አላመርትም ወይም ራሴ ተዟዙሬ አልሸጥም። የማደርገው እያንዳንዱ ነገር እንዴት በተገቢው መንገድ እንደሚከናወን ማመቻቸት ነው። ሌሎችም ሥራ እንዲያገኙ ለመርዳት የምችለውን ነው ያደረኩት" ይላሉ።

ጂም ባደረጉት በጎ ተግባር በዚህ ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ የካናዳ መንግሥት በአገሪቷ በሁለተኛ ደረጃ ክብር የሚሰጠውን ሽልማት አበርክቶላቸዋል። ንግሥት ኤልሳቤጥ ሁለተኛን የወከሉት የካናዳ አስተዳዳሪ ጀኔራል ጁሌ ፓይቴ "የሚገርም ስኬት፣ ለማህበረሰቡ ያለውን ኃላፊነት እና ለአገሪቱ የሰጠውን አገልግሎት አሳይቶናል" ብለዋል።

የገልፍ ከንቲባ ካም ጉትሬም ለቢቢሲ "እውነተኛ፣ ትሁት፣ ደግ እና ጨዋ መሪ ናቸው" ሲሉ ለጂም ያላቸውን ክብር ገልፀዋል።

ለ20 ዓመታት ዴንማርካዊት እህቱን የፈለገው ኢትዮጵያዊ ሀኪም

"ለቀጠሯቸው ሠራተኞቻቸው እና ለሚኖሩበት ማህበረሰብ ይጨነቃሉ፤ ከካናዳ ውጭ የሚኖሩ ሌሎች ሰዎችን ወደ ገልፍ አምጥተዋል፤ ከምቾት ቀጠናቸው ወጥተው ከከተማቸው በዘለለ በዓለም ምን እየተከናወነ እንደሆነ ለማየት ዐይናቸውን ከፍተዋል" ሲሉ አክለዋል።

ጂም እንደሚሉት ከሶሪያ ስደተኞች የሰሙት ታሪክ አሁንም ድረስ ከውስጣቸው አይጠፋም። ወደ ፈራረሰው ቤታቸው የተመለሱት ሰዎች ታሪክ፣ ከሞት አፋፍ ካሉ ወንድሞቻቸው ጋር በስልክ የሚያደርጉት ልውውጥ ከህሊናቸው አይወጣም።

"እነዚህ ቤተሰቦች እንደማንኛውም ሰው ደስተኛ መሆን ይፈልጋሉ፤ ከጥቃትና ከስጋት ነፃ የሆነን ወደፊት ይመኛሉ። 99.9 በመቶ የሚሆኑት ካናዳዊያን ከሌላ አገር የመጡ ስደተኞች ቢሆኑም እንኳን አሁንም መቀበል አለብን" ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ